>
10:19 am - Tuesday July 5, 2022

የጄነራሎቹ ግድያ ለአማራ  ሕዝብ ትልቅ ምስክር ነው!!! (ጌታቸው ሽፈራው)

የጄነራሎቹ ግድያ ለአማራ  ሕዝብ ትልቅ ምስክር ነው!!!
ጌታቸው ሽፈራው
የእነ ጄነራል ሳዓረ ግድያ የተሰማው የባሕርዳሩን “መፈንቅለ መንግስት” ተቆጣጥረነዋል ካሉ በኋላ ነው። የባሕርዳሩ የተፈፀመው ገና በጊዜ ነበር። የፌደራል መንግስቱ ታዲያ “ከአንድ ሰዓት በላይ ያልቆየ ነው” ብሎት ነበር። የእነ ጄነራል ሳዓረ ግድያ የተሰማው ግን ከሰዓታት በኋላ “መፈንቅለ መንግስቱን ተቆጣጥረነዋል” ካሉም በኋላም ነው። የፌደራል መንግስቱ “መፈንቅለ መንግስቱን አክሽፈነዋል” ካለ ከሰዓታት በኋላ እንደ ዋዛ ተገደሉ የተባሉት ኢታማዡር ሹሙ መሆናቸው ትልቁ እንቆቅልሽ ነው።
ጄነራል ሳዓረ መኮንን  መገደላቸው የተገለፀው “መፈንቅለ መንግስቱን ለማክሸፍ እየሰሩ” ተብሎ ነው። ይህኛውን ተጨማሪ እንቆቅልሽ የሚያደርገው ተገደሉ የተባሉበት ሰዓት “መፈንቅለ መንግስት” የተባለው ከሸፈ ከተባለ በኋላ መሆኑ ነው። ከዚህ ሲበስ ደግሞ “መፈንቅለ መንግስቱን ለማክሸፍ እየሰሩ” ነበር የተባሉት ኢታማዡር ሹሙ ስራ ላይ ነበሩ የተባሉት ቤታቸው ውስጥ ነው።  “መፈንቅለ መንግስት” ለአንድ የጦር አዛዥ ትልቁ አደጋ መሆኑን ማንም አያጣውም። ጄ/ል ሰዓረ የተገደሉት ጓደኛቸው ጄ/ል ገዛኢ አበራ ጋር  መኖርያ ቤታቸው ግቢ ውስጥ በመዝናናት ላይ እያሉ እንደነበር እየተነገረ ነው። የተገደሉት ከሰራዊቱ በጡረታ ከተሰናበተ ጓደኛቸው ጋር እየተጫወቱ በነበረበት ወቅት እንጅ መፈንቅለ መንግስት የሚባልን ትልቅ አደጋ ለማክሸፍ ከሚችሉት ኃላፊነት ላይ ያሉ ሰዎችና መፈንቅለ መንግስት የሚባልን ለማክሸፍ ከሚችሉበት ቦታ ሆነው አይደለም።  ኢታማዡር ሹም የሚያክል ትልቅ ኃላፊነት   ያለበት አካል መፈንቅለ መንግስትን ቀርቶ ሌላን መለስተኛ ችግር እንኳ ተፈጠረ ሲባል ቤቱ ቁጭ ብሎ ይፈታዋል ተብሎ አይታሰብም። ይህ ትልቅ ግዳጅ ቤት ሆነው የሚፈቱት አይደለም። እውነታው ደግሞ በጡረታ ከተሰናበተው ጓደኛቸው ጋር እየተዝናኑ ነበር።
ሌላኛውና ትልቁ እንቆቅልሽ ገዳይ ተብሎ መግለጫ የተሰጠበት ሰው ጉዳይ ነው። ገዳይ የተባለው ሰው ጠባቂያቸው የነበረ ነው። ይህ ሰው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የተመሰረተው የሪፐብሊክ ጦር አባል ነው። ለአንድ የጦሩ ቁንጮ የሆነ ሰው ቀርቶ ለሌላ ሰው የሚመደብ ጠባቂ እንኳ በደንብ ተጣርቶ፣ እንቅስቃሴው በደንብ የሚጠና ሰው እንደሚመደብ የሚታወቅ ነው። የግንኙነትና ሌሎች መስመሮቹም ቢሆን ውስንና በቁጥጥር የሚያልፉ ናቸው።  በእርግጥ ገዳይ ነው ስለተባለው ሰው የተነገረው መግለጫ መንግስታዊ ቀልዱን በደንብ የሚያስረዳ ነው። ገዳይ ነው በተባለው ሰው ጉዳይ ብዙ መግለጫዎች ቀርበዋል። እርምጃ ተወስዶበታል ብለው መግለጫ ሰጥተዋል። የፖሊስ ኮምሽነሩ ሕይወቱ አልፏል ብለው መግለጫ ሰጥተዋል። የፖሊስ ኮምሽነሩ የወንጀል ምርመራ ስራውን በዋነኝነት የሚቆጣጠሩ ሰው ናቸው ተብሎ ይታሰባል። ሆኖም የፖሊስ ኮምሽነሩ የሰዓረ ጠባቂ ሕይወቱ አልፏል ብለው መግለጫ ከሰጡ ከሰዓታት በኋላ ጠባቂው በሕክምና ላይ መሆኑን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። የኢታማዡር ሹሙ ጠባቂ ላይ የተሰጠው የተለያየ መግለጫ በጄነራሎቹ ግድያ ብዙ ሴራ እንዳለ ማሳያ ነው።  የፌደራል መንግስት በመግለጫው የጠባቂውን ስም እስከአያቱ እየጠራ ገዳዩ አማራ ነው ለማለት ጥረት ያደረገበትን አስነዋሪ መግለጫም ሰምተናል።
የጄነራሎቹ አስከሬን ሲሸኝ አንድ ትልቅ ፍንጭ ወጥቷል። የጄ/ል ሳዓረ መኮንን የቅርብ ጓደኛ የነበረውና ላለፉት አመታት የቁም እስረኛ እንደሆነ የሚነገርለት ጄ/ል አበባው ታደሰ በጄ/ል ሳዓረ ላይ ይደርስ የነበረውን ውግዘት እንባ እየተናነቀው ተናግሯል። ትህነግ/ሕወሓት በጄ/ል ሳዓረ ላይ የነበረውን አቋም ፍንትው የሚያደርግ  ሚስጥር ብቅ አድርጓል። ጄ/ል ሳዓረ በትህነግ/ሕወሓት ውግዘት ይደርስበት እንደነበር “ሀቁ ይፍረጥ” ብሎ ተናግሮታል። ጄ/ል ሳዓረ ከትህነግ/ሕወሓት ብቻ አይደለም ግፊት ሲደርስበት የነበረው። በይፋም ባይሆን ቦታውን ለብርሃኑ ጁላ ከለቀቀ ቆይቷል። ሀገር ውስጥ ቢቆይ ስለሚጠረጠር ይመስላል በውጭ ጉብኝቶች መሪዎች  እንደ ወታደራዊ መሪ  ሳይሆን እንደ ዲፕሎማት ይዘውት ሲዞሩ ታዝበናል።  ከጄነራሎቹ ሞት በኋላም የሁለቱን ኃይሎች ትብብር በግልፅ አይተናል። የአማራ ጥላቻውን  መሸፋፈን የማይችለው ጄ/ል ጌታቸው ጉዲና መቀሌ ላይም በአማራ ሕዝብ ላይ ሲደነፋ ሰምተናል። በትህነግ/ሕወሓት በኩልም እነ ደብረፅዮን የሚጠሉትን ጄነራል ግድያ አስታክከው አማራው ላይ ሲደነፉ ሰንብተዋል።
የጄነራሎቹ ግድያ የባሕርዳሩን ክስተት መፈንቅለ መንግስት ለማስመሰል በፌደራል መንግስቱ ዘንድ ብዙ ፕሮፖጋንዳ ተሰርቶበታል። እውነታው ግን የጄነራሎቹ ግድያ በእንቆቅልሾች የተሞላ ከምንም በላይ በአማራ ሕዝብ ላይ ሲነዛ የሰነበተውን ፕሮፖጋንዳ የሚያከሽፍ ነው። የጄነራሎቹ ግድያ በአማራው ላይ ሴራ ሲጎነጎን እንደሰነበተም አንድ ትልቅ ማስረጃ መሆን የሚችል ነው። በጄነራሎቹ ግድያ ላይ የባጥ የቆጡን ሲቀባጥር የሰነበተው የፌደራል መንግስቱ የባሕርዳሩ ጉዳይ ላይ በመንተራስ የተሰራ ሴራ ላይ እጁ እንዳለበት ማሳያ ነው። በተለይ በአዴፓ መሪዎች መካከል የነበረውን ክፍተት በማስፋትና ወደለየለት አሳዛኝ ጉዳይ በመመምራትም እጁ ንፁህ አለመሆኑን የጄነራሎችን ግድያ ከባሕርዳሩ ክስተት ጋር ለማያያዝ ያደረገው መፍጨርጨር ያሳብቅበታል። የጄነራሎቹ ግድያ በዚህም በዛም እየተገፋፋ ወደ አሳዛኝ ክስተትነት የተቀየረው የባሕርዳሩ ክስተት ሲፈጠር ሆን ተብሎ የተፈፀመና ለማያያዝ የተሞከረ መሆኑን መገመት ይቻላል። ይሁንና ባሕርዳር የነበረውን ክፍተት ሲጠባበቁ የነበሩ አካላት የጄነራል ሳዓረ መኮንንን ጉዳይ ማዳመቂያ ለማድረግ ቀድመው ያቀዱት ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል። የባሕርዳሩን ወደለየለት እንዲያመራ ሲጠባበቁ በሰነበቱት መሰረት ለማዳመቂያነት የተዘጋጁለትን የጄነራል ሳሞራን ጉዳይም ፈፅመውታል። ይህ በእንቆቅልሽ የተሞላና የባሕርዳሩ ሲፈፀም ለማዳመቂያነት የተፈፀመው የጄነራሎቹ ግድያ ለአማራ ሕዝብ ትልቅ ምስክር የሚሆን ተግባር ነው። የባሕርዳሩ ክስተት ገዥዎቹ በሴራ ገመድ ያገናኙት እንጅ እነሱ ለድርሰት እንደፈለጉት፣ በሚዲያ ወጥተው እንደሚናገሩት አማራውን በቀጥታ የማይመለከት ጉዳይ መሆኑን ራሳቸው ከሚሰጡት በእንቆቅልሽ የተሞላ መግለጫ በላይ ምስክር የለም! የጄነራሎቹ ግድያ ሁለቱ አማራ ጠል ኃይሎች  የተስማሙበት አማራው ላይ ለመለጠፍ አጋጣሚ ስላገኙ ነው። የኦሮሞው ኃይል አማራና ትግራይን ወደጦርነት እንዲያመሩ፣ ወደጦርነት ባያመሩ እንኳ የለየለት የጥላቻ ግንብ ተገንብቶላቸው ሲናቆሩ እንዲኖሩ ይፈልጋል። ይህን በማድረግ ሁለቱም በተለይ በፌደራል መንግስቱ ላይ በርካታ አስጨናቂ ጥያቄዎችን እያቀረበ ያለው አማራው በሌላ ጉዳይ እንዲወጠር፣ ከአዲስ አበባ ጉዳይም እንዲርቅ ይፈልጋል። ትግራይ ውስጥ ከመቸውም በከፋ ተቃውሞ እየገጠመው የሚገኘው ትህነግ/ሕወሓት በበኩሉ አማራው ላይ በማላከክ የውስጥ አንድነቱን መጠበቅ ይፈልጋል። የጄነራሎቹ ግድያም ሆነ የባሕርዳሩ ክስተት ማዶና ማዶ ለተቀመጡት አማራ ጠል ኃይሎች አንድ ያደረገ ጉዳይ ነው። የሚጠሉት ሕዝብ ላይ ከተፈፀመው አሳዛኝ ጉዳይ ባሻገር የሚጠሉትን ጄ/ል በማስገደል ይኸውን ጉዳይ ለሚጠሉት የአማራ ሕዝብ በአበሳነት ለማሸከም የሄዱበት መንገድ ግን ራሳቸውን የሚያጋልጥና ለአማራው ንፅህና የሚመሰክር መሆኑን እየታዘብን ነው!
Filed in: Amharic