ብርሀኑ ተክለአረጋይ
* ወንድሞቼን ከጨለማ ቤት አውጧቸው!!!
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሲገነባ በቢሮዎቹ ህንፃ ምድር ቤት ለልዩ ምርመራ የተዘጋጁ ጠባብ፣ቀዝቃዛና ተዘግተው የሚውሉ 10 ክፍሎች ተዘጋጅተዋል እነዚህ 10ክፍሎች ውስጥ የታሰረ እስረኛ በቀንም በሌሊትም ከባድ ምርመራ እንደሚደረግበት በማወቅ ይዘጋጃል ከዚህም በላይ ሁሉም ወደ እነዚህ ክፍሎች የገባ እስረኛ ለብቻው በተቆለፈበት ክፍል ውስጥ ሆኖ መርማሪዎቹ መጥተው ለምርመራ እስከሚወስዱት ድረስ በቁዘማ መጠበቅ እንጂ ከቤተሰብ ጋር መገናኘት ተብሎ ነገር አይታሰብም።
ለመጀመሪያ ጊዜ እነዚህን ክፍሎች ያወቅኳቸው ህዳር 27/2007 ሰማያዊ ፓርቲ የ24 ሰአት ሰልፍ ባዘጋጀ ጊዜ ነበር ከተያዝንው ከ30 በላይ የምንሆን ሰዎች ኢ/ር ይልቃል፣ስለሺ ፈይሳ፣ወረታው ዋሴ፣ኤርጫፎ ኤርዴሎ፣በጨለማ ቤቱእስርና በድብደባው ምክንያት ከእስር እንደተፈታን ህይወቱ ያለፈው አቶ ወንድሙ፣ሰሎሞን ተሰማ፣ኢያስጴድ ተስፋዬ፣ሳሙኤል አበበ፣መርከቡ ሀይሌና እኔ ተመርጠን ለእነዚህ ክፍሎች ተደለደልን ክፍሎቹ የሚገኙት የህንፃው ምድር ቤት ውስጥ ሲሆን ወደ ክፍሎቹ የሚያስገባው ግዙፍ በር 000 ቁጥር ተፅፎበታል የክፍሉ በር የሚከፈተው ክፍሉ በር ላይ የምትገኘው የጥበቃዎች ቢሮ ውስጥ ባለው መቆጣጠሪያ ኮምፒውተር ነው በሩን አልፎ ሲገባ እያንዳንዳቸው በተመሳሳይ ሁኔታ በአውቶማቲክ የሚከፈቱና ድምፅ ወደ ውጪ የማያሳልፉ ወፋፍራም በሮች ያሏቸው 10ክፍሎች ይገኛሉ 5ቱ በቀኝ 5ቱ ደግሞ በግራ ወደ አንድ ክፍል አንድ ሰው ይመደባል አንዳንዴም 2 ሰዎች የሚመደቡበት ጊዜ አለ የክፍሎቹ ስፋት ሁለት በሁለት ሲሆን ቁመታቸው ደግሞ 3 ሜትር ይሆናል በክፍሎቹ የላይኛው ጥግ ላይ መርማሪዎች የታሳሪዎቹን ሁኔታ የሚከታተሉበት ካሜራ ተሰቅሏል።
የክፍሉ ቅዝቃዜ አያድርስ ነው እዚህ ክፍል የሚገቡ ሰዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለመገናኘት ባለመቻላቸው ደግሞ የሚሞቅ ልብስ፣ፍራሽ፣ ወዘተ ለማስገባት አይመቻቸውም ምግብም እንዲሁ እስር ቤቱ ከሚያቀርብላቸውና ፖሊስ ከቤተሰብ ተቀብሎ ከሚያደርስላቸው ውጪ “ይህን አምጡልኝ ይህ ከህመሜ ጋር አይሄድም” ወዘተ ማለት አይታሰብም ያኔ ወደዚህ ቤት ከገባነው 10ሰዎች ጠንካራው መርከቡ ነበር ቅዝቃዜውን ተቋቁሞ ፑሽአፕ ይሰራል ለ30 ደቂቃ በምትፈቀድልን የአየር ሰአት ደግሞ ሁላችንንም ያበረታታል።አቶ ወንድሙ ስንያዝ የደረሰበት ድብደባና የቤቱ ቅዝቃዜ ከነበረበት የስኳር ህመም ጋር ተደማምሮ ከእስር በተፈታን በጥቂት ቀናት ውስጥ ለሞት አብቅቶታል አቶ ኤርጫፎም ተጎድቶ ነበር።ክፍሏን ለሁለተኛ ጊዜ የጎበኘኋት “ለውጡ” መጥቶ እኛም ከእስር ተፈተን በመስከረሙ የኦነግ አቀባበል ጊዜ በተነሳው ግርግር በድጋሚ ለእስር በተዳረኩበት ወቅት ነው ያኔም የገባሁት እዚህችው ክፍል ውስጥ ነው ለዚያውም በጠባቧ ክፍል የአእምሮ ህመም ያለበት በህዝብ ላይ ፈንጂ መወርወሩን በኩራት የሚናገር ግለሰብ በአኗኗሪነት ተመድቦልኝ 7 ቀን ቆይቼባታለሁ። በአጠቃላይ የክፍሏ ትዝታ በአካልም በአእምሮም የማይረሳ ነገር ጥሎ የሚያልፍ ነው።
በነገራችን ላይ በመስከረሙ እስር ጊዜ ከመፈታቴ ጥቂት ሰአታት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ወደ ቤተ መንግስት አስጠርተው ባነጋገሩኝ ጊዜ ስለ ምድር ቤቱ በአግባቡ አስረድቻቸዋለሁ እርሳቸውም “እንዲህ አይነት ቦታ መዘጋት አለበት” ብለው ቃል ገብተው ነበር። ይሁንና ክፍሏ ዛሬም ለመንግስት አገልግሎት በመስጠት ላይ ነች።የሚያስገርመው ሌላ ጉዳይ ይህንን ለፍርድ ቤቶች በምናስረዳበት ወቅት የፖሊሶቹ መልስ ነው ሁሌም እዚህ ክፍል የታሰረ ሰው ለፍርድ ቤት “የታሰርኩት ከእስረኞች ተነጥዬ ጨለማ ቤት ነው “ይላል የፖሊስ መልስ ደሞ የተለመደ ነው”ጨለማ ቤት የለንም ፍርድ ቤቱ ሰው ልኮ ማረጋገጥ ይችላል” ይህ በቀረብኩበት ችሎት ሁሉ የታዘብኩት መልስ ነው። ፖሊስ ነገም ለፍርድ ቤት የሚሰጠው መልስ ከዚህ የተለየ እንደማይሆን እረዳለሁ ይሁንና ፍርድ ቤቱም ሰው አይልክም ቢልክም ፖሊስ የፈቀደውን ክፍል ብቻ ጎብኝቶ ይመለሳል።
የምድር ቤቱን ክፍልም የሰብአዊ መብት ተቋማት የፍትህ አካላት ሚዲያ ተቋማትና በተለያዩ ስያሜዎች የተቋቋሙ የእርቅና የሰላም ኮሚቴዎች ሊጎበኙት የምናውቃቸውም የማናውቃቸውም ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች ሊነጋገሩበትና በይፋ ሊዘጋ ይገባል ያለዚያ ነገሩ “ድመት መንኩሳ…….” መሆኑ ነው።
ወንድሞቼን ከጨለማ ቤት አውጧቸው!!!