>

ቆይ! ከመጠጣትዎ በፊት !!  ካልተረገሙት ጦማሪዎች አንዱ - አሌክስ አብርሃም

ቆይ! ከመጠጣትዎ በፊት !! 
ካልተረገሙት ጦማሪዎች አንዱ –  አሌክስ አብርሃም
   ዶ/ር ዓብይ በትላንቱ የፓርላማ ንግግሩ ቅጥል እርር እንዳለ ያስታውቃል ! በእውነት ዓብይ ካሁን ካሁን ከጠረጴዛው ስር በቀይ ቀለም የተሞላ ጠርሙዝ አውጥቶ ‹‹የፌስቡክ ጦማሪያን ፣አክቲቪስቶች ባላደራዎች ሟርተኞች ኦነጎች አብኖች  ይውደሙ!! ብሎ ›› ከፊት የተቀመጡት የ((እንግጭላ)) ህዝብ ተወካይ ግንባር ላይ  ሊከሰክሰው ነው ፣ በቃ ይሄ ህዝብ ገፍቶ ገፍቶ ሰውየውን ‹‹ቀይ ሽብር›› ሊያሳውጀው ነው እያልኩ ስጨነቅ …ዓብይ ግን ክፉ አሳቢውን ሁሉ ‹‹ለእግዚአብሔር ሰጥቶ›› ፓርላማውን ደም ሳይሆን እንባ አራጨው !!ከጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ህልፈት ወዲህ ፓርላማ እንዲህ ተላቅሶ አያውቅም ነው የሚባለው ! ያኔም አለቃቀሱ በወረቀት  ተፅፎ እያንዳንዱ የህዝብ ተወካይ በወከለው  ህዝብ ባህል መሰረት እንዲያለቅስ ታዞ ነው የሚሉ ምቀኞች አሉ ( በለቅሶ ይቀናል?)
    በነገራችን ላይ …ዶ/ር ዓብይ በዚያ አነጋገሩና አካሄዱ ለፓርላማው ‹‹በቃ በዚች አገር ላይ በማንኛውም  የዩቲዩብ ተጧሪና የፌስቡክ ጦማሪ ላይ ነፃ እርምጃ እንዲወሰድ እንወስን›› ቢል ያ ሁሉ የተመሰጠ ‹‹የህዝብ ተወካይ ›› እጁን አውጥቶ ባስበላን ነበር ! ይሄን ለማወቅ ከፈለክ  ዶ/ር ዓብይ ‹‹እስክርቢቶ ጥለን ክላሽ ማንሳት እንችላለን ሲሉ ››ፓርላማው እንዴት እንዳጨበጨበ  ተመልከት!የሆነ ሁኖ …ያ አቶ መለስ ‹‹እንበለው ›› ሲሉ ‹‹በለው›› የሚል ፓርላማ ፣ ያ አቶ ሐይለማሪያም መርጦ የላካችሁ የወከላችሁት ህዝብ  ላይ እርምጃ እንዲወሰድ አዝዣለሁ ሲሉ አጨብጭቦ ለእብደታቸው ድንጋይ ያቀበለ ፓርላማ ዛሬ ‹‹እንባውን ረጭቶ ሽብርተኛውን ሁሉ ለግዜር ሰጥቶ ወጥቷል›› ሆደ ቡቡ ፓርላማ !
    የሆነ ሁኖ የኔ ትኩረት ፖለቲካውም ሃይማኖቱም  ላይ አልነበረም! የደህንነት መስሪያ ቤታችን እንዲህ ተዳክሞ  የክልል ፕሬዝዳንት እንዲሁም የአገር መከላከያ ሰራዊት መሪ እንደቀልድ በሚቀጠፉባት  አገር የጠ/ሚንስትራችን ደህንነት መጠበቅ የእያንዳንዱ ዜጋ ሃላፊነት ነው በሚል ለጠቅላያችን ውሃ የምትቀዳውን ልጅ በአይነቁራኛ ስመለከታት ነበር ! የሚቀርበው ውሃ በየጓዳው የሚመረት ጥራቱ ያልተጠበቀ ውሃ ሆኖ የአገር መሪን ያክል ነገር  ታይፎይድ ታይፈስ ምናምን ቢያዝ ለዓለም መሳቂያ መሆናችን አይደለም ወይ ?  ይሄ ጉዳይ ትኩረት ይሰጠው ለማለት ነው !
Filed in: Amharic