>
10:06 am - Monday August 15, 2022

ብሔርተኛነት፣ ፌዴራሊዝምና ዲሞክራሲ  በኢትዮጵያ !!! (አቻምየለህ ታምሩ)

ብሔርተኛነት፣ ፌዴራሊዝምና ዲሞክራሲ  በኢትዮጵያ !!!
አቻምየለህ ታምሩ
ባጭሩ ኦሮምያ የሚባለው ክልል ማንነቶች የታፈኑበት፣ ከኦሮሞ ውጭ ያለው ራሱን በራሱ ማስተዳደር ፈጽሞ የማይችልበትና በዋለልኝ ቋንቋ ክልሉ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እስር ቤት ነው ማለት ይቻላል!!!
ባገራችን ውስጥ ዘጠኝ ሉዓላዊ ክልሎች ሲኖሩ ሁሉም ሉዓላዊ ክልሎች የተዋቀሩት ራስን በራስ ማስተዳደር በሚል  መርኅ ነው። ራስን በራስ ማስተዳደር በሚለው እሳቤ ውስጥ “ራስ” የሚለው ነገድ ወይንም ብሔር፣ ብሔረሰብን እንጂ የአንድ አካባቢን ኗሪ ሁሉ የሚወክል አይደለም። ነዋሪውን ሁሉ ሳይሆን አንድ ወይንም የተወሰኑ ነገዶችን ማዕከል በማድረግ ራስን በራስ ማስተዳደር በሚለው እሳቤ ኢትዮጵያ ውስጥ  ሁለት  አይነት የክልል አደረጃጀቶች አሉ።
የመጀመሪያ አይነት አደረጃጀት በክልሉ ከሚኖሩት ኗሪዎች መካከል  ሌላውን አግልሎ ለአንደኛው ነገድ ብቻ  የሚሆን ፍጹም አሐዳዊ፣ የተማከለና የአፓርታይድ መርህን በመከተል «ለአንድ ነገድ  አንድ መንግሥት» ወይንም (One-nation one state)  በሚል የተቋቋሙ ክልሎች ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ  ኗሪዎችን መጤ፣ ሰፋሪና ነባር  በሚል በመክፈል ነባር ለተባሉት  ብሔር፣ ብሔረሰቦች ብቻ አንድ የጋራ መንግሥት የተመሰረተባቸው የክልል አደረጃጀቶች ናቸው። ሁለቱም አይነት የክልል አደረጃጀቶች  የፌዴራል አደረጃጀቶች ሳይሆኑ እጅግ አግላይ፣ ፍሑም አሕዳዊና የአፓርታይድ እሳቤ የወለዳቸው ማጎሪያዎች ናቸው።
ኦሮምያ፣ ሶማሌ፣ ትግራይና አፋር ክልሎች በክልሎቹ ከሚኖረው ሕዝብ ወይንም በዘመኑ ቋንቋ ብሔር፣ ብሔረሰብ መካከል  ሌላውን ሁሉ አግልሎ ለአንዱ ነገድ ወይንም ብሔር የተመሰረቱ ክልሎች ናቸው። እነዚህ ክልሎች ራስን በራስ ማስተዳደር በሚለው መርኅ  መሰረት የአንድ ነገድ መንግሥት  ወይንም [One nation one-state] ናቸው። እነዚህ ክልሎች  የፌዴራል አደረጃቸቶች ሳይሆኑ  ከአንዱ ነገድ ውጭ  ያለውን  ማናቸውን የማንነት ስብስብ እንደ ሁለተኛ ዜጋ፣ የማይፈለግና ያለቦታው የተገኘ ባይተዋር  የሚያደርጉ የአፓርታይድ ካምፖች ናቸው።  ይህንን በምሳሌ ለማስረዳት በኦነግና በሕወሓ ፕሮግራሞች መሰረት  በተዋቀረችው  ኢትዮጵያ ውስጥ  የፌዴራል መንግሥቱን እንደመሰረተና  ትልቁ የኢትዮጵያ ክልል እንደሆነ የሚነገርለት ኦሮምያ የሚባለውን ክልል ወስደን እንመልከት።
ኦሮምያ የሚባለው በኦሮሞ ብሔርተኞች የሚተዳደረው ክልል ውስጥ በአስርት ሚሊዮኖች የሚቆጠር አማራ፣ በሚሊዮኖች፣ በመቶ ሺዎችና በአስር ሺዎች የሚቆጠር ጉራጌ፣ አርጎባ፣ ትግሬ፣ ዝይ፣ ዳዋሮ፣ ጌዲዮ፣ ሐድያ፣ ካፊቾ፣ ከምባታ፣ ኮንሶ፣ ማኦ፣ ሲዳማ፣ ሲልጢ፣ ሶማሌ፣ ዎላይታ፣ የም፣ ወዘተ ይኖራል። ራስን በራስ ማስተዳደር በሚለው የብሔርተኞች የፌዴራሊዝም መርኅ  የተቋቋመው ይህ ክልል እንደ ብሔርተኞቹ  የፌዴራሊዝም ትርጉምና መስፈርት መሰረት በክልል ውስጥ የሚገኙ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማንነታቸው እውቅና ተሰጥቶት ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር ነበረባቸው።
ሆኖም ግን  በክልሉ ሕገ መንግሥትም እንደተቀመጠው መንግሥቱ የኦሮሞ ሲሆን  ከክልል እስከ ታች ቀበሌ ድረስ ባሉ እደረጃጀቶች ከኦሮሞ በስተቀር ማንነቱ የታወቀና ራሱን በራሱ የሚያስተዳድር አንድም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ የለም!  ባጭሩ ኦሮምያ የሚባለው ክልል ማንነቶች የታፈኑበት፣ ከኦሮሞ ውጭ ያለው ራሱን በራሱ ማስተዳደር ፈጽሞ የማይችልበትና በዋለልኝ ቋንቋ ክልሉ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እስር ቤት ነው ማለት ይቻላል።
ከኦሮሞ በስተቀር  በክልሉ  ለሚኖሩ  የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ ማንነት እውቅና ያልሰጠው፣  በክልሉ የሚኖሩ ብሔር ብሔረሰብ የተባሉት የራሳቸውን ፓርላማ እንዲያደራጁ ያልፈቀደው፣ እንደ ኦሮሞ ሁሉ ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድዱ ያላደረገው፣ ቋንቋችን በሚሉት እንዲማሩ፣ እንዲዳኙ ያልፈወደው፤    ቋንቋቸውን የስራ ቋንቋ እንዳይሆን በሕግ ያገደው ክልል የፌዴራል ክልል ሳይሆን እጅግ አሐዳዊ፣ የተማከለና የአፓርታይድ ዞን ነው።  በመሆኑም ራስ በራስ ማስተዳደር በሚለው የብሔርተኞች  እሳቤ ከኦሮሞ ውጭ ያሉትን ከአስት ሚሊዮኖች በላይ ኢትዮጵያውያን  ከመንግሥት ስራና ከአስተዳደር  በሕግ  ያገለለው ኦሮምያ የሚባለው ክልል ዲሞክራሲያዊም፣ ፌዴራላዊም ሳይሆን ከኦሮሞ ውጭ ያሉ ሁሉ  ሁለተኛ ዜጋ የሆኑበት፣  ፌዴራሊዝምና ዴሞክራሲ ከኦሮሞ ውጭ ላለው አይመለከተውም ካልተባለ በስተቀር  ፌዴራላዊም ዲሞክራሲያዊም  ያልሆነ የአፓርታይድ ግዛት ነው።
ሁለተኛው አይነት የኢትዮጵያ የፌዴራል አደረጃጀት  የክልሉን ኗሪዎች መጤ፣ ሰፋሪና ነባር  በሚል በመክፈል  ነባር ለተባሉት  ብሔር፣ ብሔረሰቦች ብቻ አንድ የጋራ መንግሥት የተመሰረቱበት አደረጃጀት ነው። በዚህ አደረጃጀት ውስጥ ጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል ጉሙም፣ ደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሐረሪ የሚባሉትን ክልሎች እናገኛለን። በብሔርተኞቹ  የፌዴራሊዝም ትርጉምና መስፈርት መሰረት በክልል ውስጥ የሚገኙ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች  ሁሉ ማንነታቸው እውቅና ተሰጥቶት ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር ነበረባቸው። ሆኖም ግን ቁጥራቸው ነባር ከተባሉት የሚልቅ ነባር አይደሉም የተባሉ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እንኳ ቢኖሩ ማንነታቸው  ታውቆ፣ የመንግሥቱ አካል ሆነው   ራሳቸውን  በራሳቸው እንዳያስተዳድሩ በሕግ ተከልክለዋል። በመሆኑም እነዚህም ክልሎች  ዲሞክራሲያዊና  ፌዴራላዊ ሳይሆኑ  ነባር ከተባሉት ውጭ ያሉት  ሁሉ  ሁለተኛ ዜጋ የሆኑበት፣  ፌዴራሊዝምና ዴሞክራሲ ነባር ከተባሉት የሰው ልጆች  ውጭ አይመለከተውም ካልተባለ በስተቀር  ፌዴራላዊም ዲሞክራሲያዊም  ያልሆነ የአፓርታይድ ግዛቶች ናቸው።
በተሳሳተ መነሻ ላይ የተመሰረተው የብሔርተኞች ራስን በራስ የማስተዳደር እሳቤ  በፈለገው ቋንቋ ቢሽሞነሞን  የአፓርታይድ ግዛቶችን ከመመስረትና ክልሎችን የመናጢ ድሀ መፈልፈያ ከማድረግ  ውጭ ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ አድርጎ  ሁሉን አካታች የራስ ገዝ አካባቢ መመስረትና የበለጸገ ማኅበረሰብ ሊፈጥር አይችልም። በመሰረቱ የብሔርተኛነት እሳቤ የቅሚያና ዘረፋ  እንጂ የልማት እሳቤ የለበትም። ልማትና ብልጽግና የሚመጣው ገበያን በማቀናጀት (through integration of markets) እንጂ  ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል መንቀሳቀስ   ከአንድ አገር አቋርጦ ወደ ሌላ አገር ከመሄድ በላይ በሚከብድበት በእንደ ኢትዮጵያ አይነት የአፓርታይድ ግዛቶች አደረጃጀት አይደለም።
በኦነግና በወያኔ ፕሮግራሞች  መሰረት የተቋቋሙት  የአፓርታይድ ግዛቶች [ክልሎች ለማለት ነው] የአፓርታይድ ገመና እንዳይሰማንና እንዳይታየን  ፌዴራላዊም ዲሞክራሲያዊም ባልሆነው የአፓርታይድ እስር ቤት ውስጥ የሚገኙት  ብሔር፣ ብሔረሰቦች ለሚባሉት  ሕገ መንግሥት ተብዮው ከጭቆና ስላላቀቃቸው እንዲጠብቁት  ሌት ተቀን በመንግሥትነት በተሰየሙት ቡድኖች ሲሰበክ ሀያ ሰባት ዓመታት ሆኖታል። በኔ እምነት የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦች የሚባሉት ከጭቆና ከባርነት የተላቀቁት የወያኔና የኦነግ ፕሮግራም ሲታወጅ ሳይሆን ዳግማዊ ምኒልክና ረዳቶቻቸው ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የተባሉትን እንደ ግል ንብረታቸው ይሸጡ ይለውጧቸው ከነበሩ የየአካባቢ ገዢዎች ቀንበር ነጻ አውጥተው ድሀው በፈለገው ይኑር ብለው ሲያውጁ ነው። በዚህ ረገድ ዳግማዊ ምኒልክ ለጅማ ንጉሥ ለአባ ጅፋርና ለሁሉም የአካባቢ ገዢዎች ያወጡትን ደንብ  ማየት በቂ ነው።
 _________
ይድረስ ካባ ጅፋር፣ 
ይህንን የደንብ ወረቀት ጽፈንልሃል፤ 
ከጃንጃሮ ወዳንተ አገር የመጣውን ጋላ  እንግዲህ ከእጄ ከገባልኝ ብለህ ጭቡ አድርገህ ባርያዬ ነህና አንተንም ልበድልህ፣ልጅህንም አምጣና እንደከብት ልሽጠው ፣ልለውጠው አትበል። ይህን ያህል ዘመን አባቶቻቸው ከአባቶችህ፣ልጆቹ ካንተ ጋር አብረው ኑረው ባሪያ ሊባሉ አይገባም። ባደባባይም ባርያዬ ነው እያልክ አትሟገት። የሰው ባርያ የለውም። ሁላችንም የእግዚአብሔር ባርያዎች ነን። እግዚአብሔር መርጦ፣ከሰው አልቆ ሲያስገዛ ጊዜ በሰው መጨከን አይገባም። ለሰው ቢያዝኑ ዕድሜ ይሰጣል።
ደግሞ እንደወደደበት እተመኘው ቦታ ላይ ይቀመጥ እንጂ፣ካንተ አገር ተነስቶ ወደ ጃንጃሮ ቢሄድ፣ወደ ሌላም ወደ ወደደው አገር ቢሄድ የኔ ዜጋ ነው ብለህ ልትይዝ አይገባም። የጃንጃሮው ሰው ፣የሌላም አገር ሰው አንተን ወዶ ወደ አንተ አገር ቢገባ፣ የጃንጃሮም ገዥ ሌላውም ገዥ ሁሉ የኔ ዜጋ ነው ብሎ አይያዝ።  ደሀው እወደደው እተመቸው ቦታ ይደር።
የካቲት 8 ቀን 1902 ዓ.ም. አዲስ አበባ ከተማ ተጻፈ። 
––––––––––
የኦነግና ወያኔ ፕሮግራሞች በወለዱት ሕገ መንግሥት ከጭቆና ተላቀው ዋለልኝ መኮንን ከፈረጠር እስር ቤት ወጥተዋል የተባሉት  ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች  በፈለጉት ቦታ መኖር ቀርቶ ውሎና አዳራቸው እጅግ አስጊ ደረጃ ላይ ወድቋል። በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ  ሁኔታ ከሶስት ሚሊዮን  በላይ ኢትዮጵያውያን ክልላችሁ አይደለም ውጡ ሲባረሩና ዲሞግራፊ  የመቀየሩን ፕሮጀክት  ብዙ ሰው ሕገ መንግሥት  ተብዮ የተጣሰ ይመስለዋል። ሆኖም ግን ሕገ መንግሥት ተብዮው እየተተገበረ እንጂ እየተጣሰ አይደለም። ሕገ መንግሥት ተብዮው ክልልህ አይደለም ለተባለ ማንኛውንም ኢትዮጵያዊ  የሕገ ከለላ፣ የንብረት ባለቤትነት መብት፣  በየትም ቦታ የመወከልና የመወከል መብትና   የየመመረጥ መብት የለውም። ኦሮሞ ያልሆነው ያልሆነው በቡራዩ፣ በለገጣፎ፣ በጉጂ፤ ሶማሌ ያልሆነው በጅግጅጋ፤ ሲዳማ ያልሆነው በአዋሳ  ወዘተ. . .  እየተፈናቀለ ያለው ኦሮምያ፣ ሶማሌ፣ ሲዳማ ወዘተ በሚባሉት ክልሎች  ውስጥ ኦሮሞ ፣ ሶማሌና ሲዳማ ያልሆነ የንብረ ባለቤትነትና የኅልውና መብት ስለሌለው ነው።
ባጭሩ  አፓርታይድን ሕጋዊ ያደረገው  ሕገ መንግሥትና የአፓርታይዱ አገዛዙ የተቋቋመበት ሕገ ወጥ ደንብ ተወግዶ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ ለሁሉም የሚሆን ሕገመንግሥታዊነቱ የተሟላ ተቋማዊ የሆነ ሕገ መንግሥት የማርቀቅ ሒደት እስካልተጀመረ ድረስ የጊዜ ጉዳይ እንጂ  በቡራዩ፣ በለገጣፎ፣ በጉጂ፤ ሶማሌ  በጅግጅጋና  በአዋሳ ክልልህ አይደለም የተባለው ተለይቶ  መገደሉና  ቤቱ ፈርሶ ሜዳ ላይ መውደቁና  በሁሉም አዲስ አበባን  ጨምሮ በሁሉም ክልሎች  መቀጠሉ አይቀሬ ነው።  “ደሀው እወደደው እተመቸው ቦታ ይደር” ተብሎ ከታወጀበት ተነስተን  «ክልላችሁ አይደለምና ውጡ» ወደሚል አፓርታይድ የደረስነው ከተሳሳተ መነሻ ተነስተን ነው። የተነሳነው ከትክክለኛ መነሻ ቢሆን ኖሮ የዛሬው መዳረሻችን ትክክለኛ ይሆን ነበር። አልተማሩም የተባሉት እነ ጎበናና ምኒልክ ወደ ፊት እያዩ እንደገና ያቋቋማትን አገር ተማሩ የተባሉት ወደ ኋላ እያዩ  ዛሬ ባላችበት መስቀለኛ መንገድ ላይ አድርሰዋታል።
Filed in: Amharic