>

ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ ተራ ወንጀል ውስጥ የሚገቡ ሰው አይደሉም!!! (የቀድሞ ባለቤታቸው ወይዘሮ አልማዝ አስፋው) 

ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ ተራ ወንጀል ውስጥ የሚገቡ ሰው አይደሉም!!!
የቀድሞ ባለቤታቸው ወይዘሮ አልማዝ አስፋው 
 (ኢትዮ 360 – ሰኔ 1/2011)
ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ ተራ ወንጀል ውስጥ የሚገቡ ሰው አለመሆናቸውን ጠንቅቀው እንደሚያውቁ የቀድሞ ባለቤታቸው ወይዘሮ አልማዝ አስፋው ገለጹ።
 ወይዘሮ አልማዝ ከኢትዮ 360 ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ከብርጋደር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ ጋር ከእስር ቤት ከወጡ በኋላ ፍቺ ፈጽመው ቢለያዩም ከ1992 ጀምሮ በትዳር ተሳስረው ሶስት ልጆች አፍርተው አብረዋቸው ስለኖሩት ስለ ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ማንነት ግን አሁንም ቢሆን መመስከር እንደሚችሉ ነው የተናገሩት።
 እሳቸው እንደሚሉት ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ለሕዝባቸው፣ለወገናቸውና ለሃገራቸው በታማኝነት ቆመው ስለ እውነት ያለፉ ሰው ናቸው።
 ሰሞኑን በባህርዳር በተፈጸመው ግድያ እጃቸው አለበት ይህን ያደረጉትም ብርጋዴር ጄኔራሉ ስልጣን ፈልገው ነው በሚል ከተለያዩ ምንጮች የሚወጡ መረጃዎች ከእውነት የራቁና በፍጹም እሳቸውን የማይገልጹ የውሸት መረጃዎች መሆናቸውን በግልጽ መናገር እፈልጋለሁም ብለዋል።
 ከመታሰራቸው በፊት የነበራቸው ስልጣን ትልቅና ከበቂ በላይ ነበር የሚሉት ወይዘሮ አልማዝ ምናልባትም ሃገሬና ሕዝቤን ባይሉ ኖሮ ትልቅ ቦታ ይደርሱ ነበር ይላሉ።
 ወይዘሮ አልማዝ እንደሚሉት የብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ሞትና ጄኔራሉ እየተገለጹበት ያለው የውሸት አካሄድ እንዳለ ሆኖ በየጊዜው ትፈለጊያለሽ በሚል ወደ ፖሊስ ጣቢያ የመመላለሱ ጉዳይ ግን አነጋጋሪ ነው ብለዋል።
 የጄኔራሉን መገደል ቤታቸው ሆነው በቴሌቪዥን እንደሰሙ የሚናገሩት ወይዘሮ አልማዝ ቀብር ለመሄድ በመዘጋጀት ላይ እያሉም ወደ 15 የሚሆኑ የፖሊስ ልብስና ሲቪል የለበሱ፣ ሁሉም የተለያየ መሳሪያ የታጠቁ ሰዎች ለጥያቄ እንደሚፈለጉ ነግረው ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንደወሰዷቸው ይናገራሉ።-ምናልባትም እቅዱ ቀብር ላይ እንዳልገኝ የታሰበም ሳይሆን አይቀርም ሲሉም ያክላሉ።
 አንድ ቀን በፖሊስ ጣቢያ ውስጥ እንዲያድሩ ከተደረገ በኋላም ምንም አይነት ጥያቄ ሳይጠየቁ ቀብሩ እንደተጠናቀቀ ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ተደረገ፣ከሁለት ሳምንት በኋላ በድጋሚ በላሊበላው ሃዘን ላይ ቆይተው ቅዳሜ ማታ ወደቤታቸው ሲመለስ ዳግም በእነዛው ሰዎች ይፈለጋሉ በሚል ወደ ፖሊስ ጣቢያ መወሰዳቸውን ነው የገለጹት።
 ምንድን ነው ጉዳዬ፣ምን አጥፍቼ ነው፣ከእኔ ጋ ያላችሁን ጉዳይ አልጨረሳችሁ ወይ የሚል ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ ከእኛ ጋር ያለዎትን ጉዳይ ጨርሰዋል አሁን ትዕዛዙ የመጣው ከበላይ አካል ነው ስለዚህ እነሱ መተው ጥያቄ እስኪያቀርቡ ይታገሱ የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ነው የገለጹት።
ከሁለት ሰአት በላይ ቢቀመጡም እንዲያዙ ትዕዛዝ ሰቷል የተባለው አካል ባለመምጣቱ ለጥያቄ ሲፈለጉ ይመጣሉ በሚል ወደቤታቸው እንዲመለሱ ተደርጓል።
ወይዘሮ አልማዝ አባባል ከሆነ ነገሮች እየሄዱበት ያለው ርቀት ያሳዝናል፣ስለ እውነት የቆመ ሰው ድምጹ የማይሰማበትና ከሞተም በኋላ አዳዲስ ታሪኮች እየተፈጠሩ ስምን ለማጠልሸት የሚኬድበት ርቀት ለማንም አይጠቅምም ይላሉ።-ዛሬም ላይ ሆነው ስለእውነት የሚመሰክሩ ሰዎች መኖራቸውን በመጠቆም።
ከብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ ጋ አብረን እያለን ሁለት ቤቶች ነበሩን፣አሁንም አሉ ብለውል።–ያውም ህጋዊ መሰረት ያላቸው ሲሉ ያክላሉ
አንደኛውም በህጋዊ መንገድ በመጀመሪያ ዙር ተመዝግበን በእኔ ስም እጣ የወጣልንና ብርጭቆ ፋብሪካ አካባቢ የደረሰን ኮንዶሚኒየም ቤታችን ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በአዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ሰበታ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በህጋዊ መንገድ ከግለሰብ የገዛንው ቤት ነው ብለዋል።
ሁለቱም ቤቶች ካርታ ያላቸውና ለመንግስት ግብር የሚከፈልባቸው ቤቶች ናቸው ይላሉ።
ስለዚህ ፣ምርመራ አደረኩ በሚለው ቡድን እየወጡ ያሉ መረጃዎች በደንብ ቢታዩና ይሄንን ስራ በበላይነት የሚመራው አካልም ከነገ ተጠያቂነት ራሱን ቢያድን ጥሩ ነው ሲሉ ይመክራሉ።
እሳቸው በግላቸው ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ ስለ እውነትና ስለዜጎች ነጻነት ብሎም ስለሃገር የቆመ እውነተኛ ሰው እንደነበር መመስከር እንደሚችሉ ተናግረዋል።
ልጆቼ ትምህርታቸውን እንደጨረሱ ክረምቱን ከአባታቸው ጋር በባህርዳር ሊያሳልፉ ቀጠሮ ይዘው ነበር ይላሉ።–ቀጠሮውን ያስያዟቸውና ባህርዳር ሲመጡ ራሳቸው እንደሚቀበሏቸው ቃል የገቡላቸው አባታቸው ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው መሆናቸውንም ይናገራሉ።
ከቅዳሜና ከእሁድ በአንዱ ቀን የሚመጡትን ልጆቻቸውን ለመቀበል ዝግጅት ሲያደርጉ እንደነበርም አውቃለው ብለዋል።
አባታቸው ጋ ለመሄድ ሐሙስ ትምህርታቸውን አጠናቀውና ሻንጣቸውን አዘጋጅተው በጉጉት ሲጠብቁ የነበሩት ልጆቻቸው ቅዳሜ እለት አባታቸው መገደሉን  በቴሌቪዥን መስኮት ተረዱ ሲሉ በሃዘን ይገልጻሉ።
 ነገሮች በዚህ መልኩ የተጠናቀቁ ቢመስሉም ይላሉ ወይዘሮ አልማዝ ነገሮች አሁን ባሉበት ሳይሆን ህግና ስርአት ተከብሮ፣ እውነት በአደባባይ ተገልጣ በከንቱ የፈሰሰው የንጹሃን ወገኖቻችን ደም ሲመለስ ማየት የኔና የልጄቼ ምኞት ነው ብለዋል።
Filed in: Amharic