>
9:14 am - Wednesday December 7, 2022

ይሉኝታ የላቸው፤ ጨዋነት የላቸው፤ እዝነት የላቸው ያገኙትን ሁሉ እበት መቀባት ብቻ !?!"  (አሰፋ ሃይሉ)

ይሉኝታ የላቸው፤ ጨዋነት የላቸው፤ እዝነት የላቸው ያገኙትን ሁሉ እበት መቀባት ብቻ !?!” 
አሰፋ ሃይሉ
በዚህች ከንቱ ዕድሜዬ መንግሥታት ሲቀያየሩ አይቼያለሁ። ክቡር የሰው ልጅ በደቦ ፍርድ ባደባባይ ሲረሸን ተመልክቼያለሁ። የወያኔንም የደርግንም ግፎችና በረከቶች መሐልም ዳርም ሆኜ አሳልፌያለሁ። ከታሪክም ብዙ ተምሬያለሁ።
ባሳለፍኳት አጭር ዕድሜ “እጄን ለግፈኛ መንግሥት አልሰጥም” ብሎ በታንክ ቤቱ ተደረማምሶ በግፍ የተገደለ እንደ አማን ሚካኤል አንዶም ያለ የጦር ጄነራልንም ታሪክ አውቃለሁ። ከሠማይ ከምድር ተዋክቦ የሶማሌን ወራሪ ጠላት ያርበደበደ ጀግና እንደ አልባሌ አሮጌ ዕቃ በተሸሸገበት ቆርቆሮ ሥር “እጄን አትይዟትም” ብሎ ተታኩሶ ክብር በሌለው ሥፍራ የጀግና ሞትን የሞተ እንደ ፋንታ በላይ ያለ የጦር ጄነራልንም አውቃለሁ። ሁሉንም በያይነቱ አይቼያለሁ። አይተናልም። ሰምተናልም። ከግፉም ከበረከቱም ከሁሉም እያወራረድነው ኖረናል። ኖረነዋል። እየኖርነውም ነው።
ነገር ግን – ነገር ግን – እውነት እውነት እላችኋለሁ – የእውነት አምላክ ሐሰተኛ ቃል ከአፌ ካወጣሁ ከምላሴ ፀጉር ይነቀል – እውነት እውነት እላችኋለሁ – በህይወቴ ሙሉ – እንዳሁኑ እንደ ኦነግ-መራሹ መንግሥት ያለ – የፈሪ ፈሪ – እና የአንድን የተከበረ – በአንድ ወቅት ለዚህች ሀገር አንገቱን ሰጥቶ – የወራሪን ጠላት ምሽግ እየሰባበረ የሀገሩን ባንዲራ በጠላት መሬት ላይ ተክሎ – በክብር ከፍ አድርጎ ያውለበለበን – ኢትዮጵያን በወሬና በቀረርቶ ሳይሆን – በደሙና በነፍሱ ተወራርዶ ያከበረን አንድን የሕዝብ ጀግና – እንዲህ እንደ አሁኑ ባለ ሁኔታ – በጠራራ ፀሐይ በአደባባይ ያለፍርድ በግፍ መግደሉ አንሶ – ከሞቱም በኋላ ራሱ – የሟቹን ስም በቴሌቪዥኑ፣ በሬዲዮው፣ በጋዜጣው፣ በመግለጫው – እንደ ሥድ አደግ ነገረኛ መንደረኛ ሴት – ያለ አንዳች ኢትዮጵያዊ ይሉኝታ ሌት ተቀን እያብጠለጠለ – ሐዘንተኛ ቤተሰቦቹን አላስለቅስ፣ አላስቀብር፣ አላስቆም፣ አላስቀምጥ የሚል – ነውሩንና ስም ማጥፋቱን በአደባባይ እየደጋገመ ጨፍኑ ላሞኛችሁ እያለ የሚያደነቁር መንግሥት – እውነት እውነት እላችኋለሁ – በኢትዮጵያ ታሪክ ሙሉ ሰምቼም፣ አንብቤም፣ አይቼም፣ አጋጥሞኝም አያውቅም!
እንዴ!!??? ገደላችሁት! በቃ የሙት መንፈሱ ይረፍበት!! ምን ያለ መረኖቹን ፈቶ ለቀቀብን አያ?!! ኧረ ምን ዓይነቶቹን ወራዶችና ይሉኝታ-ቢሶቹን ነው ያጋጠመን ዘንድሮ ደግሞ በእግዚአብሔር አምላክ?!
ይሉኝታ የላቸው። ጨዋነት የላቸው። እዝነት የላቸው። ለከት የላቸው። ሼም አይጨመድዳቸው። በቃ እንዲሁ መፈንጨት ብቻ። መተርተር ብቻ። ነውር ብቻ። ያገኙትን ሁሉ በስማ በለው እበት መቀባት ብቻ።
ምን ዓይነት ጉድ ነው የገጠመን ጎበዝ?!
ጀግናውማ ጀግኖ ሞቶ አየን። የጀግና ሞት። የክብር ሞት።
የጀግናው መንፈስ የሚያስቃዣቸው ፈሪዎች ግን የሌለ ጠላት እየመጣባቸው ሠይጣን እንደያዘው ሌት ተቀን ሲያስለፈልፋቸው እያየናቸው ነው። ሠይጣናቸው ጀግናው እንደ ጦስ ዶሮ ታርዶለትም፣ ታስሮለትም የሚያስለፈልፈው ዛሩ ቶሎ የሚለቃቸው አይመስልም።
እንግዲህ እንዲህ በቁም ያሳታቸው ውቃቢያቸው ወደየት እንደሚያደርሳቸው – እና ወደየት እንደሚያደርሱን – ማየት ነው! መቼም የኛ ትዕግሥት መቋጫ የለውምና ዝም ብሎ ማየትና መስማት ነው መጨረሻችንን። ከልብ በተሰበረ ልቦና ሆነን። ምነው እዝጌሩ እንዲህ ጨከነ? ከሞቱ በኋላ ስንት ሞት አለ? ስንት ሞት ይሙት ጀግናሽ እመብርሃን?!!
አዬ እመብርሃን…!
 
“ምነው እመብርሃን? ኢትዮጵያን ጨከንሽባት?
ምነው ቀኝሽን ረሳሻት?
እስከ መቼ ድረስ እንዲህ፣ መቀነትሽን ታጠብቂባት?
ልቦናሽን ታዞሪባት?
ፈተናዋን፣ ሰቀቀንዋን፣ ጣሯን ይበቃል ሳትያት?
አላንቺ እኮ ማንም የላት?”
       – ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድኅን፣ ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት
የጀግናውን ነፍስ ይማር እርሱ አንድዬ ቸሩ መድኃኔዓለም!
Filed in: Amharic