>

ፍርድ ቤቶች ራሳቸዉን ሊፈትሹ ይገባል!!!»   (ጋዜጠኛ እና የመብት ተሟጋች እስክንድር ነጋ-ለዶይቼ ቬለ )

ፍርድ ቤቶች ራሳቸዉን ሊፈትሹ ይገባል!!!»
 ጋዜጠኛ እና የመብት ተሟጋች እስክንድር ነጋ 
ዶይቼ ቬለ

«ፍርድ ቤቶች ራሳቸዉን ሊፈትሹ ይገባል» ሲል የባልደራስ ምክር ቤት ሰብሳቢ ጋዜጠኛ እና የመብት ተሟጋች እስክንድር ነጋ አመለከተ። ጋዜጠኛው ይህን የተናገረዉ የባልደራስ ዋና ጸሐፊ ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ እና የበረራ ጋዜጣ እንዲሁም የአስራት ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ በሪሁን አደራ መታሠራቸዉን ተከትሎ ነዉ።

ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ለእስር የበቃዉ ፖሊስ ባሕር ዳር ተሞከረ ከተባለዉ መፈንቅለ መንግሥት ጋር በተያያዘ በሽብር ጠርጥሬዋለሁ በማለቱ ነዉ ሲል እስክንድ ለዶይቼ ቬለ ገልጿል።

ባሕር ዳር ላይ የተከሰተዉ ሙሉ ለሙሉ የኢህአዴግ የዉስጥ ጉዳይ መሆኑን ያመለከተው እስክንድር ነጋ፤ ጋዜጠኞችም ሆኑ የባለአደራዉ ም/ቤት፤ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቂ ማለትም «አብን»ም ሆነ እንዲሁም በመንግሥት ላይ ሰላማዊ ተቃዉሞ የሚያነሱ ከባሕር ዳሩ ክስተት ጋር ግንኙነት የላቸውም ብሏል። በዚህ ሰበብ ሰላማዊ ተቀናቃኞች እየታሠሩ፣ እየታደኑ እና እየተንገላቱ ነው ሲልም ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ተናግሯል። «በየእስር ቤቱ የተያዙበት ሁኔታም እጅግ የሚያሳዝን ነዉ፤ ከህወሃት ዘመን የሚብስ እንጂ የሚስተካከል አይደለም። ወንድሞታችን እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ላይ ነዉ የሚገኙት፤ እጅግ ጠባብ በሆነ ፤ ምንም ብርሃን በሌለበት ጨለማ እና ቀዝቃዛ ክፍል፤ ከፈነዳ መፃዳጃ ቤት የሚወጣ ሽታን እየተነፈሱ፤ ኢ- ሰብዓዊ በሆነ ሁኔታ ላይ ነዉ የሚገኙት» ሲልም ታሳሪዎቹ ይገኙበታል ያለውን ሁኔታ ዘርዝሯል። «ሁኔታውም ለሀገራችን የኋልዮሽ ጉዞ ነው» ም ብሏል። ፍርድ ቤቶችም ችግር እንዳለባቸዉ ከወዲሁ ምልክት እያየን ነዉ የሚለው ጋዜጠኛ እስክንድር «ንፁሐን ዜጎች ሽብር በሌለበት ሀገር በሽብር ተጠርጥረዋል ተብለዉ የአቃቤ ሕግን ጥያቄ ተከትሎ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ፤ ሙሉ ማስረጃ እንኳ ሳይሆን አመላካች ማስረጃ አላችሁ ብሎ እንኳ ሳይጠይቅ በደፈናዉ እየተቀበለ ነዉ» ሲል ለዶይቼ ቬለ ገልጿል። ፍርድ ቤቶች በአንድ ዓመት ዉስጥ መለወጥ ነበረባቸዉ የሚለው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፤ «የመንግሥትን ጥያቄ በደፈናዉ መቀበል አይገባቸዉም ነበር ፤ ነፃነታቸዉን በዚህ አጋጣሚ ማሳየት ይገባቸዉ ነበር፤ አሁን እከሌ ከእከሌ ሳንል ፍርድ ቤት የቀረቡት ሙሉ በሙሉ ንፁሐን ናቸዉ ሲል» የባለዳራዉ ምክር ቤት ሰብሳቢ ለዶቼ ቬለ «DW» ተናግሯል። ይህን ተከትሎ ወደ አቃቤ ሕግ ቢሮ በተደጋጋሚ ያደረግነዉ የስልክ ጥሪ ስልካቸዉን ባለማንሳታቸዉ አልተሳካም።

Filed in: Amharic