>
10:58 am - Friday May 20, 2022

ለኦሮሞና ለአማራ አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞች ---- (ከአፈንዲ ሙተቂ)

ለኦሮሞና ለአማራ አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞች
—-
ከአፈንዲ ሙተቂ
—–
ባለፉት ጥቂት ወራት በሶሻል ሚዲያው ላይ ጎራ ለይተን ስንሰዳደብ ከርመናል። የቻልነውን ያህል ተቀጣቅጠናል። ተናቁረናል። ተቦጫጭቀናል። ከእንግዲህ ንትርኩና ሁከቱ ቢበቃን ይሻላል። ይህ አድራጎት በዚህ ካልተገታ ያልተጠበቀ መዘዝ ሊያመጣብን ይችላል።
—–
አማራና ኦሮሞ ነን!!
 
አዎን! የታሪክ አጋጣሚና የፈጣሪ ፈቃድ ሆኖ ከእነዚህ ሁለት ታላላቅ ህዝቦች ተወልደናል። እነዚህ ህዝቦች 75% የሚሆነውን የሀገሪቷን ህዝብ ይወክላሉ። የሚኖሩበት መሬትም ኢትዮጵያ ከምትባለው ሀገር የሚበዛውን እጅ ይወክላል። በፖለቲካና በኢኮኖሚ ስምሪታቸውም የአንበሳውን ድርሻ ይዘዋል። እነርሱ የሌለችበትን ኢትዮጵያ ማሰብ ከቶ አይቻልም። በሌላ በኩል ሁለቱ ህዝብ ከምናስበው በላይ በጋብቻ፣ በአምቻ፣ በጉዲፈቻ ተዛምደዋል። በቋንቋና በባህልም በእጅጉ ተዛምደዋል። በጉርብትና፣ በእድር፣ በማህበር እና በሃይማኖት ተሳስረዋል። የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ ከእነርሱ ጋር የተቆራኘ ነው። ኢትዮጵያን ማጥፋትም ሆነ ማልማት የሚችሉት እነርሱ ናቸው።
—-
እነዚህ ህዝቦች በራስ ወዳድ መሪዎችና በአፋኝ ስርዓቶች ስር ለብዙ ዘመናት በጭቆና ሲማቅቁ ነበር። ልጆቻቸው ለነፃነት ቢታገሉም የሚጠበቀውን ውጤት ለማምጣት አልቻሉም። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ግን ከሁለቱ ህዝቦች የወጡ ፖለቲከኞች የጋራ መቀራረብ በመፍጠር የትብብርን ሃያልነት አሳይተውናል። ፖለቲከኞቻችንና ታጋይ ወጣቶቻችን በፈጠሩት መቀራረብ አፋኙን የወንበዴ ስርዓት ጠራርገው ከወንበሩ አባርረውታል።
ጨቋኙን ስርዓት ከተገላገልን በኋላ ግን የለውጡን ሂደት በትክክል ማስቀጠል አልቻልንም። አንደኛው ሌላኛውን የጎሪጥ እያየና እየተጠራጠረ እጅግ አሰልቺና አሰቀያሚ የሆነ የፖለቲካ ጨዋታ ሲጫወት ከርሟል። “ስልጣን ለእገሌ ተሰጠ፣ የኔ ብሄር ተበደለ፣ ከእዚህ ለውጥ ይልቅ የድሮው ወንበዴ ይሻለኛል” የሚሉ ትርክቶችን እያስጮኽን በጥቂት አመታት ያዳበርነውን የትብብር መንፈስ ከመሬት ደባልቀነዋል። በዚህ ወቅት ሁኔታዎች ተካርረው የኢትዮጵያችንን ህልውና ከሚፈታተኑበት ደረጃ ደርሰዋል።
—-
የሁላችንም ዓላማ በአንድ ሀገር ውስጥ መኖር አይደለምን? ከኢትዮጵያ ተገንጥሎ መንግስት ልሁን የሚል ብሄርና ብሄረሰብ አለን? መልሳችን “የለም” የሚል እንደሆነ አልጠራጠርም። እንዲያ ከሆነ አሁን የምናየውን ዋልታ ረገጥ ስም የመጠፋፋት ፕሮፓጋንዳ መንዛት እና የጥላቻ ዘመቻ ማካሄድ ለማን ይጠቅማል? በአንድ ሀገር ጥላ ስር የሚኖር ህዝብ መረን በለቀቀ ሁኔታ አይበጣበጥም። መሳሪያ እየወለወለ “ይዋጣልን!” አይባባልም። የሀገሪቱን ህልውና አደጋ ላይ በሚጥል ሁኔታ አይናቆርም። ትውልድን የሚበክል የጥላቻና የጥርጣሬ ዘር አይዘራም። ህዝቦችን ሰላም የሚነሳ የውሸት ፕሮፓጋንዳ ለመርጨት አይራወጥም።
—-
በእኔ እምነት የዚህ አሳፋሪ ቀውስና ዝቅጠት መንስኤዎች ሁለት ናቸው። አንደኛው የአሁኑ ለውጥ የመጣበትን አኳኋን መርሳታችን ነው። ሁለተኛው አምና በዶክተር አቢይ የሚመራው መንግስት ስልጣን በያዘበት ጊዜ እኛ የሁለቱ ህዝቦች ተወላጆች ለለውጡ መንግስት ድጋፍ የሰጠንበትን መነሻ መርሳታችን ነው። እስቲ በመጠኑ ነካ ነካ ላድርጋቸው።
የአሁኑ ለውጥ የመጣው ህዝቦቻችን ለዘመናት ባደረጉት ተጋድሎ ነው። ታዲያ ተጋድሎው እንዲህ በቀለለ መንገድ የተካሄደ አይደለም። በትግሉ ሂደት እጅግ ልብ የሚነኩና ተስፋ የሚያስቆርጡ ክስተቶች አጋጥመውናል። አንዳንዴ ገዥዎቻችን ላደረሱብን በደል ብድራችንን የምንከፍልበት መንገድ ጠፍቶን በጋራ ሆነን እንባችንን እያፈሰስን ወደ ፈጣሪያችን ያለቀስንበት ሁኔታም ታይቷል። በ2009 መጀመሪያ ላይ የኢሬቻ በዓልን ለማክበር በወጡት የኦሮሞ ወንድሞቻችን ላይ በደረሰው አሳዛኝ ትራጄዲ ያላዘነ የአማራ ተወላጅ አክቲቪስት አለን? አማራው ከኦሮሞው እኩል አላለቀሰምን? ኦሮሞውስ በአማራው ወንድሞቹ ላይ ሲደርስ ለነበረው የጅምላ ግድያና ውድመት አላለቀሰምን? የስርዓቱ ተጠቃሚዎች “ጎሽ! ዋጋችሁን አገኛችሁ። የኛ መንግስት በአፍሪቃ የማይደመሰስ ነው” እያሉ ሲያሾፉብን አልነበረምን?
እውነቴን ነው። ትልቁ የጎንደር የገበያ ማዕከል በመስከረም 2009 በተቀነባበረ የእሳት አደጋ በወደመበት ወቅት ያለፈው መንግስት ደጋፊዎች “ጎሽ! እሰይ ሲያንሳችሁ ነው” እያሉ ሲደነፉብን ነበር። በኢሬቻ አደጋ ወቅትም ሌቦችና ማጅራት መቺዎቹ “አደጋውን ያቀናበሩት ከግብፅ የተላኩ የኦነግ ምንደኞች ናቸው” እያሉ ሙድ ሲይዝብን ነበር። በዚያች አስጨናቂ ወቅት ተስፋችን ፈጣሪያችን ብቻ ነበር። ለብዙ ወራት ሁላችንም እያለቀስን ወደ ፈጣሪ ስንጮኽ ቆይተናል። ፈጣሪያችንም ፀሎታችንን ሰምቶ በሸረኛው መንግስት ላይ እሳት አነደደበት። እሱ ካልጠበቀበት አቅጣጫ የተነሱ ልጆቻችን ፈር ቀዳጅ ሆነው የህዝቡን እምባ አበሱለት።
አዎን! ለማ መገርሳ፣ ገዱ አንዳርጋቸው፣ አቢይ አህመድ፣ ንጉሱ ጥላሁን፣ ደመቀ መኮንን፣ አምባቸው መኮንን ፣ አዲሱ አረጋ፣ ሙፈሪሃት ካሚል ወዘተ በማጅራት መቺው ቤት ያደጉ ፋኖዎች ነበሩ። ለዓመታትም ስርዓቱን አገልግለውታል። በህዝባቸው ላይ ይደርስ የነበረውን ጭቆናና በደል ቢያውቁትም ሃይላቸውን አስተባብረው የሚታገሉበት ሁኔታ ቸግሮአቸው ቆይተዋል። በህዝቡ ላይ ሲደርስ የነበረው በደል ፅዋውን ሞልቶ መፍሰስ ሲጀምር ግን “ከዚህ በኋላ ጭቆናው ይበቃል። ህዝቦቻችን ነፃ መውጣት አለባቸው” አሉ።
እነ ለማ መገርሳ እና እነ ገዱ አንዳርጋቸው በኢህአዴግ አባልነታቸው የሰርዓቱን ድክመቶችና ጥንካሬዎች በቅርበት የማወቅ እድል ነበራቸው። እነዚህ ውድ ሰዎቻችን ከሁሉም በላይ የተረዱት ነገር የማጅራት መቺው ስርዓት በአማራና በኦሮሞ ታጋዮች መካከል ባሰመረው የክፍፍልና የጥላቻ መስመር ላይ ቁመናውን መትከሉን ነው። በዚህም መሰረት ኦህዴድ እና ብአዴን የሚባሉትን ድርጅቶች በማቀራረብ ለመታገል ወሰኑ። አንድ ላይ ሆነውም ማጅራት መቺውን ቡድን ተጋፈጡት። በዓለም ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ አብዮትን ከመንግስቱ አስኳል ውስጥ ወደ ውጪ አፈነዱት። ብዙዎችም በሁኔታው ተገርመው “እንቁላል ከውስጥ ሲሰበር ጫጩቱ አይሞትም፣ ከውጪ ሲሰበር ግን ህይወት አይዘራም” በማለት ተናገሩ። በአፈና ሲማቅቁ የነበሩት የኦሮሞና የአማራ ህዝቦች ልጆቻቸው ከውስጥ ያቀጣጠሉትን ትግል ከውጪ በማጋጋል የማጅራት መቺውን ስርዓት ለግብአተ መሬት አደረሱት።
—-
ይህ የቅርብ ጊዜ ታሪካችን ነው። ይህንን ከቶውንም መዘንጋት አልነበረብንም። ነገር ግን አሁን የምናየው ነገር የያኔውን ደማቅ ታሪካችንን ከአፈር እየቀላቀለው ነው። ትግሉ ለመሬትና ለነዋይ የተደረገ ይመስል በኩርማን ቦታና በመታወቂያ እየተነታረክን ነው። የአስተሳሰብ አድማሳቸው የጠበበ የሃሳብ ድሃዎች “በዚህ ከተማ ቆንጨራ እየታደለ ነው፣ አማራው ተነስ፣ ኦሮሞው ታጠቅ” በሚሉ የሃሰት ድንፋታዎች ሲያናቁሩን ያየ የቀድሞው ማጅራት መቺ አንጀቱ ቅቤ መጠጣቱም አይደለምን? ይህ አካኄድ ከዚህ በኋላ መቀጠል የለበትም። ለህዝቦቻችን ጥቅም የምናስብ ከሆነ የግዴታ መቆም አለበት።
—–
ሁለተኛው ነጥብ ለአሁኑ የለውጥ መንግስት ድጋፍ የሰጠንበትን መነሻ መዘንጋታችን ነው። እርግጥ ሁሉም ሰው በዚህ ላይ ተመሳሳይ እይታ የለውም። እኔ በግሌ የምስማማው ከዶክተር ብርሃኑ ነጋ አባባል ጋር ነው። ዶክተር ብርሃኑ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ናቸው። ሆኖም በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ የሚመራው መንግስት ለሚያካሄደው የለውጥ እንቅስቃሴ ድጋፋቸውን እንደሚሰጡ በተደጋጋሚ ጊዜ ገልፀዋል።
እኔም የዶክተር አቢይ እና የፓርቲያቸው ደጋፊ አይደለሁም። ድጋፍ የሰጠሁ ያለሁት ለለውጥ ሂደቱ ነው። በማጅራት መቺው ስርዓት ያጣሁት ነፃነትና ዲሞክራሲ በሀገሬ ላይ እንዲያብብ እፈልጋለሁ። ስለሆነም የአሁኑ ኢህአዴግ በዶክተር አቢይ መሪነት የጀመረውን የለውጥና የተሓድሶ ሂደት ሙሉ በሙሉ እደግፋለሁ። መንግስት ለህዝቡ ቃል በገባው መሠረት ዲሞክራሲያዊ ምርጫ አካሂዶ በህዝብ የተመረጠ አካል ስልጣን ላይ ሲወጣ ለማየት እፈልጋለሁ።
እርግጥ የዶክተር አቢይ መንግስት አምና በጠበቅነው ፍጥነት እየተጓዘ አይደለም። ይህም ብዙ ምክንያቶች አሉት። ከምክንያቶቹ መካከል አንደኛው መንግስት ከአቅጣጫው በሚመጡበት ጊዜያዊ አጀንዳዎች መወጠሩ ሲሆን ሌላኛው መንግስቱ ራሱ ከህዝብ የተሰጠውን mandate መዘንጋቱ ነው። ለምሳሌ ሃኪሞችና መምህራን የሚያካሄዱት የስራ ማቆም አድማ፣ በየክልሉ የሚነሱት ግጭቶችና የሰዎች መፈናቀል፣ “ክልል እንመስርት” እየተባለ በየስርቻው የሚንከባለለው አጀንዳ፣ በአብዮት አደባባይ፣ በቤተ መንግስት እና በባህር ዳር የተከሰቱት አስደንጋጭ ድርጊቶች፣ ወዘተ መንግስት ተረጋግቶ ስራውን እንዲሰራ የሚያደርጉ አልነበሩም። በሌላ በኩል መንግስት ራሱ ከህዝቡ የተሰጠውን ኃላፊነት ረስቶ ራሱ የሚፈጥራቸውን አጀንዳዎች ማስጮኹ ብዙ ጉዳት እያደረሰ ነው። በስድስት ወራት ውስጥ ለሶስት ጊዜ ያህል የካቢኔ ሹምሽር ማድረግ፣ የአዲስ አበባ ወንዞች ልማት ፕሮጀክት በሚልና ከጊዜው አንፃር አስፈላጊ ባልሆነ እቅድ ራስን ባተሌ ማድረግ፣ የመንግስት ተሿሚዎች የባለአደራ መንግስት አገልጋዮች መሆናቸውን ባላገናዘበ ሁኔታ በሚዲያ እየቀረቡ አነታራኪ መግለጫዎችን መስጠት ወዘተ በመንግስት በኩል የታዩ ድክመቶች ናቸው። እነዚህን ስህተቶችና ድክመቶች እየነቀሱ በማውጣት መንግስት የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደቱን እንዲያፋጥን መቀስቀስ ይገባናል።
—–
ውድ የአማራና የኦሮሞ ልጆች!
ስሜታዊነት በእጅጉ ጎድቶናል። በያለንበት ራሳችንን መፈተሽ አለብን። እኛ እዚህ ስንነታረክ በገጠር የሚኖረው ህዝባችን በኮሌራ እያለቀ ነው። የኑሮ ውድነቱ ብዙዎችን ተስፋ እያስቆረጠ ነው። ስለሆነም ሰከን ብለን በማሰብ የተሻለች ሀገር ስለምንገነባበት ሁኔታ መነጋገር አለብን።
በቅርቡ የገባንበት መንገድ መጨረሻው ጥፋት ነው። ስለዚህ ከዚህ መሸሽ አለብን። ሁላችንም በያለንበት መሳሳታችንን አምነን ሂስ እናውርድ።
እኔ አፈንዲ ሙተቂ ከአሁን በኋላ ንትርኩን አቁሜአለሁ። ድሮ ወደምታወቅበት የመሃል ግራ (Center Left) ፖለቲካ አቀንቃኝነትም ተመልሻለሁ።
ገለምሶ፣ ሀረርጌ
Filed in: Amharic