>

የታፈነው እስክንድር ብቻ ሳይሆን እኔም እናንተም ሁላችንም ነን!!! (ሙሉነህ እዮኤል)

የታፈነው እስክንድር ብቻ ሳይሆን እኔም እናንተም ሁላችንም ነን!!!
ሙሉነህ እዮኤል
እስክንድር በሚናገረው ላትስማማ ትችላለህ። ላትስማማ የምትችለውን ሀሳብ የማፈን መብት ግን ሊኖርህ አይችልም። ሃላፊነቱን የተረዳ መንግስት ቢኖር ኖሮ ድርጊቱ ወንጀል ሆኖ ያስከስስና ሊያስቀጣ ይችል ነበር።
እስክንድርን በማፈን አብይን፣ መንግስቱን፣ ኦሮሚያ፣ ኦሮሞንም ሆነ ቄሮን እንደጠቀምካቸው ታስብም ይሆናል። መደማመጥ የምንችልበት ሁኔታ ቢኖር ኖሮ አብይንም ሆነ ሌሎቹን አካላት እንዴት እንደጎዳሃቸው ማስረዳት እጅግም ባልከበደ።
የታፈነው እስክንድር እንጂ እኔ ምን አገባኝ በሚል አልያም ድርጊቱ ትክክል ባይሆንም ትልልቅ ጉዳዮች ላይ ማተኮር እንጂ እንዲህ ያሉ ትናንሽ ነገሮች በለውጥ ወቅት የሚያጋጥሙ ትናንሽ ነገሮች እንደሆኑ ተረድቶ በተለይም የለውጡን ስሱነት ከግንዛቤ አስገብቶ በትዕግስትና ሆደ-ሰፊነት ማለፍ ይሻላል በሚል፤ አልያም በመንግስቱ ውስጥ ተሰግስገው ለውጡ እንዲቀለበስ ወይም ጥላሸት እንዲቀባበት ለሚያደርጉ ቀልባሾች መሳሪያ ላለመሆን በሚል ዝምታን መርጠህ ይሆናል።
መደማመጥ ቢቻል ኖሮ እንዲህ ያለው ነገር ውሎ አድሮ አንተም ዘንድ እንደሚደርስ ወይም በርግጥ እንዳልከው ለውጡን መቀልበስ የሚፈልጉ ሃይሎች በመንግስቱ ውስጥ ተሰግስገው ከሆነ በዛሬ ዝምታህ ለውጡ እንዲቀለበስ እንዴት እንዳገዝህ ማስረዳት አይከብድም ነበር። መደማመጡ እንኳን ቅንጦት ቢሆን የምንናገረውን እንደሀሳብ ልዩነት ለማየት የሚያስችል ህሊና በጠፋበትና የምንናገረውን ሁሉ እንደጨለማ እየተቆጠረ ባለበት ሁኔታ እንዲህ ያለውን አፈና በዝምታ ማለፍ አደገኛ እንደሚሆን ለማስረዳት መዳከር ትርፉ ድካም ብቻ ነው።
ይህን የምጽፈው ለህሊናዬና ለእስክንድር ነው። ከእስክንድር ጋራ ላልስማማ እንደምችል እርሱ እራሱ አሳምሮ ያውቀዋል። በብዙ ጉዳዮች ላይ በእስር ቤት ተማግቼዋለሁ። እርሱ መብትን ያለገደብ የሚፈቅድ ሲሆን እኔ ግን በተገደበ ነጻነት የማምን ነበርሁ አሁንም ነኝ። ዛሬ ከማንም በላይ ከእስክንድር ጎን መቆም ይገባቸው የነበረው የኦሮሞ ልሂቃን ቢሆኑም ያ ግን በተለያየ ምክንያት አልሆነም። ድምጻቸው በታፈነበት ዘመን፤ እነአብይ እነለማ የጨለማው ሃይል የአፈናው ጉልበት በነበሩበት ዘመን፤ የኦሮሞ ጥያቄ ምን እንደነበር፣ ለምን የኦሮሞ ወጣቶች ጥያቄ ፍትሃዊ እንደነበር ሲጽፍና ሲከራከር የነበረው የዛሬው ታፋኝ እስክንድር ነበር። ሚንሊክ ይመስክር!
ለእስክንድር ላረጋግጥለት የምችለው የታፈነው እርሱ ብቻ ሳይሆን በማሰብ ነጻነት የምናምን ሁላችን እንደሆንና የማሰብ፣ የመናገርና የመደራጀት መብቱ በማንም ሊገረሰስ የማይገባውና ይሄ ሆኖ ሲገኝ አብሬው እንደምቆም ብቻ ነው። የታፈነው እስክንድር ብቻ ሳይሆን እኔም እናንተም ሁላችንም ነን። ባያውቁት ነው እንጂ ያፈኑት እራሳቸውንም ጭምር ነው።
Filed in: Amharic