>

የአብይ አስተዳደር እና ዋልታ ረገጥ አስተሳሰቦች ኢትዮጵያን ወዴት...?!?  (ያሬድ ሀይለማርያም)

የአብይ አስተዳደር እና ዋልታ ረገጥ አስተሳሰቦች ኢትዮጵያን ወዴት…?!? 
ያሬድ ሀይለማርያም
በደስታ እና በተስፋ የተቀበልነው ለውጥ እየተውገረገረም ቢሆን የአመት ከመንፈቅ እድሜ አስቆጥሯል። ዛሬ ያደስታ እና ተስፋ በብዙዎች ዘንድ እየተሟጠጠ ይመስላል። ደስታችን በበርካታ አስደንጋጭ ክስተቶች ተውጧል። ተስፋችንም በአስተዳደሩ መብረክረክ እጅግ እያቆለቆለ መጥቷል። ከመጀመሪያውም በለውጡ ላይ ደስተኛ ያልነበሩም ሆነ ተስፋ ያላደረጉ ሰዎች የተመኙት ወይም የፈሩት የደረሰ መሆኑን ለማሳየት ንግግራቸውም ሆነ ምልከታቸው ‘እንደተመኘኋት አገኘዋት’ የሚለውን ዘፈን የሚያቀነቀኑ አስመስሏቸዋል። በጎ ተመኝተው፣ ተስፋ አድርገው እና ለውጡን በሚችሉት መንገድ ሁሉ ደግፈው አመድ አፋሽ የሆኑ የመሰላቸው ደግሞ የተከጂነት ስሜት ተሰምቷቸው እዮዮውን ተያይዘውታል። አሁንም በለውጡ ላይ ሙሉ በሙሉ ተስፋ ያልቆረጡ የኔ ብጤዎች ቢጨልምም ይነጋል በሚል እምነት መንግስትን መወትወት እና ችግሮቹን በጊዜ እንዲያስተካከል ማሳሰባችንን ቀጥለናል።
ኢትዮጵያ ዛሬ ከመቼው በከፋ አስፈሪ ሁኔታ ውስጥ እንደምትገኝ መተንተን አያስፈልግም። እየመጣ ያለውን አደጋ የተረዳንበት ደረጃ ይለያይ ይሆናል እንጂ ሁሉም አካል የገባው ይመስላል። ሰሞኑን የሚወጡ የመንግስት መግለጫዎችም ይህንኑ ነው የሚያሳዩት። ሥርዓቱም ሆነ ለውጡን የሚመራው አካል ግራ የተጋባ መሆኑን በግልጽ ለማየት ጠ/ሚ አብይ ከሳምንት በፊት አገሪቱ የገጠማትን ፈተና በማስመልከት ለፓርላማ ያደረጉትን ንግግር በደንብ ማድመጥ በቂ ነው።
ጠ/ሚትሩን ለስሜታዊነት የሚገፉ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሯቸውም ንግግራቸው ግን በብዙ ተቃርኖ የተሞላ፣ አቅጣጫ የማያሳይ፣ ቁጣና ድንፋታ የበዛበት፣ አለመረጋጋት እና አቅም ማጣት የታየበት እና መሰረታዊ የሆኑ የአስተሳሰብ መዛነፎችም የታዩበት ነበር። በሕገ መንግስት ዙሪያ ከሰጡት አስተያየት መካከል አንዷን እንኳ ብገልጽ በቂ ማሳያ ትሆናለች። ‘ይህን ሕገ መንግስት የማይቀበል ሰው ሰለ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ሊያወራ አይችልም’ የምትለዋ አነጋገራቸው የሰብአዊ መብት መርሆዎችን ከመጣስ ባለፈም ሁለት እንድምታ አላት። አንድም ጠ/ሚንስትሩ በዚህ ጉዳይ የሕግ አማካሪዎቻቸውን ሃሳብ አይቀበሉም ወይም ሳይጠይቁ በደመ ነፍስ ነው የተናገሩት። አለያም አፈናን እንደ አዋጪ መንገድ ማሰላሰል ጀምረዋል ማለት ነው።
ለውጡ በብዙ ፈተናዎችም ውስጥ ሆኖ በርካታ በጎ ነገሮችንም ስላከናወነ ይህን የለውጥ ኃይል በጭፍን ከሚነቅፉ እና ከሚረግሙ ሰዎች ጋር አልስማማም። መልካሙን ሥራ የማወደስ እና መጥፎውን የማውገዝ ሚዛን በብዙ ተችዎች ዘንድ ጎድሎ ይታያል። ከፖለቲካ ባህላችንም ውስጥ ተሟጦ እየጠፋ ያለ ይመስላል። መጥፎ የሚባሉ ነገሮችን ብቻ እያነፈነፉ ሥርዓቱን ማጠልሸት ለሚፈልጉም ሆነ የተሰራውን ጥቃቅን በጎ ነገር አገዝፈው ሌሎችን መሰረታዊ ችግሮችን እና ግድፈቶችን ማየት ለተሳናቸው ሰዎች በየጊዜው የሚከሰቱት አድጋዎች፣ ግጭቶች እና ውዝንብሮች ምቹ እድል የፈጠሩላቸው ይመስላል።
ጭፍን ተቺዎቹ ሰዎች ከሞላው ዘጠኝ ይልቅ የጎደለችው አንድ ነገር እንደ ተራራ ገዝፎ ስለሚታያቸው መልካሙን ነገር እንዳያዩ ይጋርዳቸዋል። ከመልካሙም ነገ ውስጥ እንከን እና አቃቂር ለማውጣት ከመጣር ባለፈ በጎን ነገር በፍጹም አያደንቁም። የጨለምተኝነት አደጋው ይሄው ነው። በተቃራኒው ጽንፍ የያዙ አፍቃሪ አብዮች ደግሞ እንዲሁ ዘጠኝ ቢጎድል አንዷን ስኬት ብቻ እንደተራራ አግዝፈው እያዩ ሌሎችን የመንግስት ጉድለቶች እና ፈተናዎች እንዳላዩ እና እንዳልሰሙ ሆነው አወዳሽ ብቻ ይሆናሉ። የታወረ ፍቅርም ክፋቱ አገርን የሚያጠፋ ግዙፍ ስህተትን እረብ በሌለው ስኬት እና እርካታ ለመሸፈን እና በባዶ ለመመጻደቅ መዳከርን ያስከትላል።
እነዚህ ሁለት ተቃርኖዎች የአገሪቱን ፖለቲካ ወደ ንትርክ እና ብሽሽቅ እየገፋት ለመሆኑ በየመድረኩ እና በማህበራዊ ድህረ ገጾች የሚደረጉ ጉንጭ አልፋ እና ሚዛን የማይደፉ ንትርኮች ጥሩ ማሳያዎች ናቸው። ጽንፍ ለፍቅርም ይሁን ለጥላቻ ውጤቱ አወንታዊ ነው። ማህበረሰባችን፤ በተለይም ልሂቃኑ በእነዚህ ዋልታ እረገጥ ጫፎች ላይ ሆነው እና ተቧድነው እየተጓተቱ እና እየተጎነታተሉ አገሪቱን ወደ መጥፎ አቅጣጫ እየገፏት ይመስለኛል። በላዩ ላይ ዘር ተኮር የጥላቻ ንግግር እና የሃሰት ትርክቶች ስለታከሉበት ሁኔታውን የበለጠ አሳሳቢ እና የከፋ አድርጎታል።
፩/ የአብይ አስተዳደር
የአብይ አስተዳደር ልንገምተው ከምንችለው በላይ በውስጣዊ ችግሮች እና ውጫዊ ጫናዎች ተከቦ ከላይም ከታችም በእሳት እንደ እንደታጀለ ድፎ ዳቦ አጣብቂኝ ውስጥ ያለ ይመስላል። ይህ ዳቦ ሦስት እድሎች ያሉት ይመስለኛል። አንድም አሮ እና ከስሎ የማይበላ ዳቦ ሆኖ መጠል። ሁለትም ከላይ እና ከታች በስሎ ውስጡ ሊጥ እንደሆነ ከእሳቱ ሊወጣ ይችላል። ሦስተኛው ደግሞ እንዳማረ ድፎ ዳቦ ውጪውም ውስጡም በጥሩ ሁኔታ በስሎ የሚበላ ሊሆን ይችላል። የአንድ ዳቦ እጣፈንታ በጋጋሪው ሙያ እንደሚወሰን ሁሉ የዚህ ሥርዓትም የለውጥ እና የሽግግር ጉዞ እንደ መሪዎቹ ብቃት፣ ጥንካሬ እና የችግሮች አፈታት ስልት የሚወሰን ነው።
የአብይ አስተዳደር ጥሩ ዳቦ ሆኖ ለመውጣት የተፈጠሩትን እሳቶች ተቆጣጥሮ በሰዓቱ ማስወገድ ይኖርበታል። እሳቱ አገሪቱ የምትገኝበት ውስብስብ እና ከባድ የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሃብት እና የማህበራዊ ቀውሶች ናቸው። አክራሪ ብሔረተኝነት፣ የከፋ ድህነት፣ ከፍተኛ የሆነ ሥራ አጥነት፣ የማንነት እና የወሰን ጥያቄ፣ መረን የለቀቀ ሙስና፣ የተበላሸ የመንግስት አስተዳደራዊ መዋቅር፣ የዘር መሳሳብ እና የተረኝነት ስሜት፣ ብሶተኝነት እና የተገፋው ባይነት እሮሮ፣ የሕገ መንግስት ጥያቄ፣ የገንዘብ ግዥፈት እና የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የተቋማት ብቃትና ገለልተኝነት፣ ቂም እና በቀል፣ የአገራዊ መግባባት አለመኖር እና ሌሎች በርካታ ችግሮች ልክ እንደ እሳት ሥርዓቱን ከላይም ከታችም ዙሪያውን ሰቅፈው ይዘውታል። ሊጥ ዳቦ ለመሆን እሳት እንደሚያስፈልገው ሁሉ እነዚህም የቆዩ እና እየተባባሱ የመጡ ችግሮች ሥርዓቱ በአግባቡ ከተጠቀመባቸው በቅጡ አንዲበስል ይረዱታል። እነዚህን አደጋዎች ወደ እድል መቀየር ካልቻለም ሁለት አደጋዎች ይከሰታሉ።
+ ሥርዓቱ የከበቡትን አደጋዎች ሁሉ በጉልበት እና በአፈና ጠራርጌ ከላዮ ላይ አነሳለሁ በሎ ጡንቻውን ማፈርጠም እና በሕዝብ ላይ ወደ መፈተሽ ካመራ እሳት እንዳላገኘው ዳቦ ሊጥ ሆኖ ይቀራል። ችግሩ ይህ ሥርዓት እንደ ህውሃት ሊጥ ሆኖ ሃያ ሰባት አመት የመቀጠል እድል ስለማይኖረው ባጭሩ ይጣላል፤ አገሪቱም ትርምስ ውስጥ ትገባለች።
+ ሌላኛው አደጋ ደግሞ ይህ ሥርዓት ከላይም ከታችም የከበቡትን አደጋዎች በጥንቃቄ እና በእውቀት ወደ እድል ለውጦ መሆድ ካልቻለ እና መሻሻል የሚገባቸውን ነገሮች ጊዜ ሳይወስድ ማሻሻል ሳይችል ችግሮቹን እንዳዘለ የሚቆይ ከሆነም እንዲሁ በአጭር ጊዜ ውስጥ የማረር እጣ ይገጥመዋል። ያረረም ሆነ ሊጥ የሆነ ዳቦ እንደሚጣል ሁሉ፤ ሥርዓቱም ጊዜ ይፈጃል እንጂ በመጥፎ አኳኋን ይወገዳል። ከዚያ የሚያተርፍ አይኖርም።
ሕውሃት አገር የተቆጣጠረችበትና ስልጣን ላይ የቆየችበት ዘመን እና አሁን ኦዴፓ መራሽ የሆነው ለውጥ ያለበት ዘመን በብዙ መልኩ የተለያዩ ናቸው። ሕውሃት ወደ ስልጣን ስትመጣ የብሔር ድርጅቶች ቢኖሩም ጽንፈኝነቱ እና የከረረ የብሔር አስተሳሰቦች በሕዝብ ውስጥ ገና አልሰረጹም ነበር። ስለዚህ ለወያኔ አንዱ እና ትልቁ ፈተና የኢትዮጵያን ሕዝብ በዘር ማቧደን እና እርስ በርሱ እንዲፈራራ ለማድረግ እቅድ መንደፍ ነበር። ህውሃት ሕገ መንግስቱን ተጠቅሞ ክልሎችን በቋንቋ እና በዘር ማንነት ላይ ከማደራጀት አንስቶ እስከ አንድ ለአምስት የአፈና አደረጃጀት ድረስ የሚችለውን ሁሉ አድርጓል። የተዘራው ዘር ዛፍ ሆኖ ዛሬ ፍሬው መንጠባጠብ ጀምሯል።
የአብይ አስተዳደ የመጣባት ኢትዮጵያ የዘረኝነት አስተሳሰብ ቀንድ ያወጣበት፣ በብሔር ብሔረሰብ ስም የተዘራው ዘር ዛፍ ሆኖ ካላዩ ላይ አክራሪ ብሔረተኞችን በየቅርንጫፉ የተሸከመበት፣ ግለኝነት እና አግላይነት የነገሰባት ነች። ዛሬ ሁሉም ነገ የሚመነዘረው በጎሳ እሳቤ ነው። ሰው ቢሾም፣ ሰው ቢሻር፣ ሰው ቢገደል፣ ሰው ቢታሰር፣ ሰው ቢዋከብ፣ ሰው ቢናገር፣ ሰው ዝም ቢል፣ ሰው ቢከብር፣ ሰው ቢደኸይ፣ ሰው ቢቧደን፣ ሰው እርስ በራሱ ቢባላ የሚመነዘረው በጎጥ የስሌት ማሽን ብቻ ነው። ሕውሃት ያሳደገችው ዛፍ ኢህአዴግ ነው። ኢህአዴግ የተሸከመው ፍሬዎች ደግሞ አክራሪ ብሔረተኞቹ ናቸው። ዛፉ በፍሬዎቹ ሊዋጥ አንድ ሐሙስ የቀረው ይመስላል። ኦዴፓም፣ አዴፓም፣ ህውሃትም ሆኑ ሌሎቹ የደቡብ ድርጅቶች በእነዚህ አክራሪ ኃይሎች ሙሉ በሙሉ የመዋጥ አደጋ ከፊታቸው ተጋርጧል።
፪/ ዋልታ ረገጥ አስተሳሰቦች
ዋልታ ረገጥ የሆኑት አስተሳሰቦች ለዘመናት የነበሩ ቢሆንም አሁን ግን የመንግስት መዳከም እና በአገሪቱ የተናኘው የብሶት ፖለቲካ ትርክት ገበያውን ያደራላቸው ይመስላል። በተለይም የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የትግራይ እና የሲዳማ አክራሪ እና ጽንፍ የያዙ ኃይሎች ኢትዮጵያን እንደ አገር የመቀጠል ተስፋዋን እጅግ እየተፈታተኑት ይመስላል። በዛሬዋ ኢትዮጵያ ማንም የማንም የበላይ የሚሆንበት የዋጪ እና ተዋጭ ወይም የአሸናፊ እና የተሸናፊ ፖለቲካ ማካሔድ እንደማይቻል እነዚህ ኃይሎች የገባቸው አይመስልም። በአክራሪነት አስተሳሰብ ከተሸነፍን እና ወደግጭት ካመራን አብረን ሁላችንም መቀመቅ እንገባለን። ይህን ዋልታ ረገጥ አስተሳሰብ አሸንፈን ወደ መሃል ከመጣን እና ለመደማመጥ፣ ሰጥቶ ለመቀበል፣ ለሥልጡን ፖለቲካ ከተሸነፍን ደግሞ ሁላችንም አሸናፊዎች ሆነን እና ኢትዮጵያም የሥልጡን ዜጎች አገር ሆና ትቀጥላለች።
በአክራሪ ብሄረተኞች መካከል የሚደረግ ፉክክርም ሆነ የእኔ ልብለጥ ውድድር መጨረሻው እልቂት እና መጠፋፋት ብቻ ነው። በእንዲህ አይነቱ ውድድር ውስጥ አሸናፊነት የለም። ሁሉ ተሸናፊ ነው የሚሆነው። በሩዋንዳ እልቂት ያሸነፈ የለም።
ማጠቃለያ
የአብይ አስተዳደር አገሪቱ የተጋረጠባትን አደጋ በቅጡ ተረድቶ ከወዲሁ ወሳኝ የሆኑ እርምጃዎችን ሊወስድ ይገባል። ከእነዚህም ውስጥ፤
+ በሕግ ማስከበር እና በአፈና መካከል ያለውን ልዩነት በቅጡ ያገናዘበ የሕግ የበላይነትን የማስከብር እና ሰላም የማስፈን፤ እንዲሁም በሰሞኑ ግርግር ያለ አግባቡ የታሰሩ ጋዜጠኞች፣ የፓርቲ አባልቶች እና ደጋፊዎቻቸውን፣ እንዲሁም የማህበራዊ ድርጅት ተወካዮችን ባፋጣኝ መፍታ፤
+ በፖለቲካ ኃይሎች መካከል ያለው ቁርሾ እና መቃቃር እንዲረግብ፤ በዘለቄታም እንዲወገድ ብሔራዊ የእርቅ እና መግባባት መድረክ ማዘጋጀት እና ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎችና ባለ ድርሻ አካላት አገሪቱ ከገባችበት ቅርቃር እንድትወጣ የሚያስችል፤ አስገዳጅነት ባሕሪ ያልው የመግባቢያ ሰነድ በጋራ ማዘጋጀትና ማስፈረም፤
+ ዋልታ ረገጥ አስተሳሰብ ያላቸው ድርጅቶች፣ ቡድኖች እና ግለሰቦች በጋራ ቁጭ ብለው የሚወያዩበት እና ልዩነቶቻቸውን አጥበው ተጠያቂነት በተመላው መልኩ ለአገር ግንባታው የሚያበረክቱትን አስተዋጸኦ እንዲቀጥሉ ማድረግ፤
+ የሃይማኖት ተቋማት እና የአገር ሽማግሌዎች በተከታዮቻቸው ላዩ በጎ ጫና በመፍጠር የዘረኝነት አስተሳሰብን ማህበረሰቡ እንዲጠየፍ ማስተማር እና መወትወት ይጠበቅባቸዋል።
ይህን ክፉ ጊዜ በጥንቃቄ ካልተሻገርን ኢትዮጵያ ዛሬ ባለችበት ቁመና እና ቅርጽ የመቀጠሏ ነገር አጠያያቂ ነው። ጠቅላይ ሚንስትሩ በኢትዮጵያ አንድነት አንደራደርም፣ በክላሽ እንፋለማለን የምትለዋን መፈክር ከሳቸው በፊት ኮረኔል መንግስቱም ደጋግመው ይሏት ነበር ልብ ሊሉት ይገባል። የኮረኔሉ ፉከራ ግን ኤርትራን ከመገንጠል አላስቀረም።
ቸር እንሰንብት!
Filed in: Amharic