>
10:08 am - Friday May 20, 2022

በር ከሌለው መቃብር መውጫ ያለውን እስር ቤት ይሻላል!  (ሚኪ አምሀራ)

በር ከሌለው መቃብር መውጫ ያለውን እስር ቤት ይሻላል! 
ሚኪ አምሀራ
አንድ ሁለት ነገር ልበል:- የክልሉ መንግስት የላከዉን ወታደር አስወጥቶ በሽማግሌ እና አካባቢዉ ሰወች መፍትሄ እንዲመጣ ማድረግ አለበት፡፡
——-
እነ ማስረሻ እና ዘመነ እንዲሁም ሌሎች ሰዎች በህግ ትፈለጋላችሁ የተባሉ ካሉ የሚሻለዉ ወደ ህግ ቀርቦ መከራከርን እና ንጽህናን ማስጠበቅ ነዉ፡፡ የጸጥታ ሃይል ብዙ ጊዜ ለመያዝ እሄዳለዉ ይላል ግን በአመለጡኝ ሰበብ ወይም ተኮሱብኝ ሰበብ ብዙ ሰወቻችን ገሎብናል፡፡ የሰዉ ህይወት መጥፋት የለበትም፡፡ ስለዚህም የሚከተለዉን የግሌን አስተያየት አስቀምጣለሁ:-
ለክልሉ መንግስት
—–
1. የክልሉ መንግስት እጠረጥራለሁ እከሳለሁ ካለ በክልሉ ፍርድ ቤት ክስ ጀምሮ መጥሪያ ይስጥ፡፡ በዛ መሰረት እንዲቀርቡ የፍርድ ቤት ፕሮሰስን ይከተል እንጅ ሃይል መጠቀምን ማቆም አለበት፡፡
2. መክሰስ ካለበት የፌደራል መንግስት ሳይሆን የክልሉ መንግስት ሆኖ ፍ/ቤት እጠረጥራቸዋለዉ ወይም ጥፋት አለባቸዉ ካለ ነጻ እና ገለልተኛ ሁኖ እንዲያይላቸዉ ማስተማመኛ ይስጥ፡፡
3. በአካባቢዉ ሽምግሌዎች፤ በቤተሰቦች፤ እና በሚቀርቧቸዉ ሰወች አማካኝነት በድርድር በሰላም የሚቀርቡበትን መንገድ መፈለግ አለበት፡፡
4. እነሱን ለመያዝ የተሰማራዉን ወታደርም ሆነ ሌላ የጸጥታ ሃይል ከአካባቢዉ ወጥቶ ልጆቹ በሰላም ተደራድረዉ የሚመጡበትን ሁኔታ ማመቻቸት አስፈላጊ ነዉ፡፡ጊዜ ሊሰጣቸዉ እና የአካባቢዉ ማህበረሰብ፤ አስተዳደር እና ሽማግሌዎች መክረዉ መፍትሄ እንዲያመጡ ጊዜ ያስፈልጋል፡፡
ለእነ ማስረሻ እና ዘመነ
——-
ለራሳችሁም፤ ለቤተሰቦቻችሁም እንዲሁም ለአማራ ህዝብም ሲባል ሰላማዊ በሆነ መንገድ የምትፈልጉበትን ነገር ቀርቦ ማስተባበል የተሻለ ነዉ ባይ ነኝ፡፡ ወታደር በእርግጠኝነት በሰላም የመያዙ እድሉ ቢኖረዉም እንኳን ወደ መግደል ነዉ የሚያዘነብለዉ ለዛዉም የእኛን ሰዉ እና እኛ ጓሮ መጥቶ፡፡ በር ከሌለው መቃብር መውጫ ያለውን እስርቤት ይሻላልና በዚህ ወቅት የማንኛዉም ሰዉ ህይወት መጥፋት ስለሌለበት ቢታሰብበበት ጥሩ ነዉ፡፡ በህይወት እየኖሩ መታገል ነዉ ለዉጥ የሚያመጣዉ፡፡ በሆነ ባልሆነዉ ነገር መሞት ለቤተሰብብ ለህዝቡም ቁጭት እንጅ ሌላ የሚያተርፈዉ ነገር የለም፡፡ በህይወት ስለኖራችሁ ታስራችሁ፤ ተከራክራችሁ ንጽህናችሁን አስጠብቃችሁ አይታችሁታል፡፡ አሁንም ቢሆነ ከዚህ የተለየ ነገር ስለማይገጥማችሁ በትግላችሁ ነጻ የወጣችሁበትን መንገድ በመከተል አሁንም ድጋሜ ነጻነታችሁን በዛዉ መንገድ ለመወጣት መጣር አስፈላጊ ነዉ፡፡
ለአክቲቪስቶች
——
እነዚህን ልጆች ታጥቆ ከሄደ ወታደር ጋረ እንዲገጥሙ እና ችግር እንዲደርስባቸዉ የምታበረታቱ ልጆች ብታርፉ ይሻላል፡፡ ጭራሽ እንዲህ ገደሉ እንዲህ አደረጉ እያላችሁ ልጆችን ወንጀለኛ ለማድረግ መጣር እጅግ ብስለት የሌለዉ ነገር ነዉ፡፡ እነዚህ ልጆች ቤተሰብ አላቸዉ ፡፡ ቤተሰቦቻቸዉ ይፈልጓቸዋል፡፡ በመሆኑም ጀብድ ሰርተዉ እንዲሞቱ ከማበረታት ይልቅ ተደራድረዉ፤ ከሽማግሌዎች እና ከአካባበዊ አስተዳደሮች ጋር መክረዉ እንዲመለሱ ማድረግ ለራሳቸዉም፤ ለቤተሰብም ፤ለህዝብም ጠቃሚዉ ነገር ነዉ፡፡ በእርግጠኝነት ይሄን የምትመክሩ አክቲቪስቶች ወንድሞቻችሁ ቢሆኑ ይሄን አትሉም፡፡ ችግር ሲደርስ ከንፈር ከመምጠጥ እና ከሳምንት ቁጭት ዉጭ የማታስታዉሱ፤ ቤተሰቦቻቸዉን እንኳን ዞር ብላችሁ የማታዩ፤ ዛሬ ላይ በስሜት እና በጭፍን ግጠሙ ጣሉት  እያላችሁ የምታበረታቱ ልጆች አደብ ግዙ፡፡
ለሽማግሌዎች እና ልጆቹ ይገኙበታል ለተባለዉ አካባቢ ላላችሁ አስተዳደሮች
——–
የአካባቢዉ አስተዳደሮች እና ሽማግሌዎች ጊዜ ወስዳችሁ ከልጆቹም ጋር ከክልሉ መንግስት ጋርም በመመካከከር እና በመተማመን በጦር እና በወታደር ሳይሆን ሰላማዊ በሆነ መንገድ፤ ምንም ጥይት ኮሽ ሳይል፤ የሰዉ ህይወት ሳይጠፋ መፍትሄ የሚገኝበትን መንገድ ማበጀት አስፈላጊ ነዉ፡፡ የእይዝሃለዉ አልያዝም ጀብደኝነት የአማራን ህዝብ ነዉ የሚጎዳዉ፡፡ስለዚህም በመተማመን ላይ የተመሰረተ ዉይይት በማድረግ መፍትሄ እንዲመጣ መሰራት የእናንተ ሃላፊነት ነዉ፡፡ ይሄን ሃላፊነታችሁን እንድትወጡ ጥሪ አቀርባለሁ፡፡
Filed in: Amharic