>
8:52 am - Tuesday July 5, 2022

ለዘረኝነታችን ለከት እናበጅለት!!! (አፈንዲ ሙተቂ)

ለዘረኝነታችን ለከት እናበጅለት!!!
አፈንዲ ሙተቂ
በዘረኝነት ዛር የተለከፉ በርካታ ኢትዮጵያዊያን በየማህበራዊ መገናኛው ላይ የሚጽፉትን ነገር ማንበቡ ያሳቅቃል። ይዘገንናል። ይህ በሽታ በጊዜ ሂደት ይሻሻላል ብለን ስንጠብቅ ከነጭራሹ ብሶበታል።
 በእርግጥ ኢትዮጵያዊያን እንዲህ ነበርን? የአባቶቻችንና የአያቶቻችን ልማድ ይህ ነበር? በገጠርና በከተማ የሚኖረው ብዙኃኑ ኢትዮጵያዊስ በዚህ ነው የሚታወቀው??
በእውነቱ በጣም ያሳቅቃል። ያሳፍራል። ልማዳችን ይህ ከሆነ ተስፋ ያስቆርጣል። የሀገራችን መጻኢ እጣ ፈንታ በእንደዚህ ዓይነት ትውልድ ላይ የሚወድቅ ከሆነ በጣም ያሳስባል።
የዚህ መንስኤ የዘረኝነትን ትርጉምና ፍቺ ካለመረዳት አይመስለኝም። መንስኤዎቹ ሁለት ነገሮች ናቸው። አንደኛው መነሾ የራስን ኢጎ እያስቀደሙ ዘረኝነትን በራስ ፍላጎትና መንገድ ብቻ መተርጎም ነው። ሁለተኛው መንስኤ ሆን ብሎ የህዝቦችን ክብርና ስብዕና በማዋረድ ነውረኛ ሱስ መጠመድ ነው።
ሰሞኑን እየጦዘ ያለውን አጀንዳ እንውሰድ። በባህር ዳር የሆነ ቡድን ተነሳና እነ አምባቸው መኮንንን ገደለ። እርሱን የሚቃወመው የፌዴራል መንግስት ግርግሩን እንደ መፈንቅለ መንግስት ስለተመለከተው የአፀፋ እርምጃ ወሰደ። በዚህም ከሁለቱም ወገን ብዙዎች ተገደሉ። የተፈጠረው ይኸው ነበር።
ታዲያ ከዚያ ክስተት ማግስት ጀምሮ በየማህበራዊ መገናኛው የሚካሄደው የዘረኝነትና የጥላቻ ዘመቻ በታሪካችን አይተነው የማናውቀው ነው። አንዱ ይነሳና በፌስቡክና በዩቲዩብ “ሴራውን ያቀናበረው ዶክተር አቢይ ነው፣ ዓላማው ዘሩን በሁሉም መስክ የበላይ አድርጎ ማንገስ ነው፣ ድሮም ከእገሌ ዘር የሚጠበቀው ይኸው ነው፣ የእገሌ ዘር በግ ነው” ብሎ ይለፈልፋል። እርሱን በመቃወም ደግሞ ሌላ ወጀላቴ ይነሳና “የእገሌ ዘር የድሮ ንግስናውን ማስመለስ ነው የሚፈልገው፣ አሳምነው ፅጌ ያደራጀውን ልዩ ሃይል ለዚህ ዓላማ ሊጠቀምበት ነበር፣ የእገሌ ዘር እባብ ነው” የጥላቻ ዘሩን ይበትናል። ሶሻል ሚዲያው የሁለቱንም አርቲ ቡርቲ እያሽከረከረ፣ በዓለም ዙሪያ ያዳርስና የንፁሐንን ልብ ይበክላል።
ህሊናው ያልታወረ ሰው ዛሬ እንደ ዋዛ የተዘራው የዘረኝነትና የጥላቻ ዘር ነገ ተክል ሆኖ ሲያድግ ምን ዓይነት ፍሬ እንደሚያፈራ ያመዛዝናል። “ለሀገርና ለትውልድ እናስባለን” የምን ከሆነ ትውልድን ከሚበክል የጥላቻ ልክፍት ልንርቅ ይገባል። ይህ እኩይ አካሄድ በጊዜ ካልተገታ በአንድ ሀገር ጥላ ስር የመቀጠላችን ነገር አጠያያቂ ይሆናል።
—–
ዘረኝነት “እኔ ኦሮሞ ነኝ” ማለት አይደለም። “እኔ አማራ ነኝ” “አፋር ነኝ” “ሶማሊ ነኝ” “ሲዳማ ነኝ” ወዘተ ማለት ዘረኝነት አይደለም። የብሄርና የጎሳ መለያውን ለመግለጽ የማይፈልግና “ኢትዮጵያዊ ብቻ በሉኝ” የሚል ሰውም ዘረኛ አይባልም።
አንዳንዶች ግን የብሄር መለያቸውን የሚገልጹ ሰዎችን “ዘረኛ” ሲሏቸው ይታያሉ። ጉድ በል ወገኔ? የትኛው ሳይንስ ነው ዘረኝነትን እንዲህ የፈሰረው? የትኛው ሃይማኖት ነው ዘረኝነትን እንዲህ እየፈታ የሚያስተምረው?
በውጪው ዓለም Hispanic, Jew, Arab, Irish, Roma, German, Zulu, Yoruba, Kikuyu እየተባባሉ መጠራት አሁንም ድረስ አለ። በሃይማኖት ድርሳናትም ሰዎች “የእገሌ ነገድ ተወላጅ፣ የእገሌ ጎሳ አባል፣ የእገሌ ህዝብ ልጅ” እየተባሉ ይጠራሉ። ሰዎች በዚህ ዘይቤ መጠራታቸው ዘረኛ አስብሎአቸው አያውቅም።
ዘረኝነት ማለት አንድን ህዝብ፣ ብሄር፣ ጎሳ፣ ነገድ ወይንም  የሃይማኖት ተከታይ በነገዱ፣ በጎሳው፣ በቀለሙና በሃይማኖቱ ብቻ ለይቶ ማጥቃት ነው። ዘረኝነት አንድ ሰው ባጠፋው   ጥፋት ሳቢያ እርሱ የተወለደበትን ብሄርና ከእርሱ ጋር ተመሳሳይ ሃይማኖት የሚከተሉትን በሙሉ በጠላትነት መፈረጅ ነው። ዘረኝነት በስራ ቅጥር ጊዜ ሰዎችን ከብቃታቸው ይልቅ በብሄራቸው እየለዩ ማወዳደር ነው። ዘረኝነት በፍርድ ጊዜ ሰዎችን በብሄራቸው እየለዩ መዳኘት ነው። ዘረኝነት ለህዝቦች ቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክና ወግ ተገቢውን ክብር በመንፈግ ህዝቦችን መጨቆን፣ በህዝቦች ላይ የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ማካሄድ እና ህዝቦችን በጅምላ እያጠለሹ በጠላትነት መፈረጅ ነው።
—–
ከዚህ አንፃር የማህበራዊ መገናኛው ተጠቃሚዎቻችንን ሁኔታ ያየ ሰው በዘቀጠ ሁኔታ ላይ መሆናችንን ይገነዘባል። ታዲያ መሄጃችን ወዴት ነው? ይህንን አሳሳቢ በሽታ ለማስወገድ ምን እናድርግ?
ሁላችንም ልናተኩርበት የሚገባ ጉዳይ ነው። ዛሬ በሽታውን በዝምታ ካለፍነው ነገ ወረርሽኝ ሆኖ ሀገር ማጥፋቱ የማይቀር ነው። ስለዚህ ነቃ ብለን እንዝመትበት። በቅድሚያ ዘረኛ ፖስቶችን ላይክ ባለማድረግ እንጀምር።
Filed in: Amharic