>
5:13 pm - Tuesday April 19, 9003

ኢትዮጵያ÷ሕዝቧ እና ሥርዓታዊ ለውጥ የወያኔ/ኢሕአዴግ አጀንዳዎች አይደሉም! (ይኄይስ እውነቱ)


ኢትዮጵያ÷ሕዝቧ እና ሥርዓታዊ ለውጥ የወያኔ/ኢሕአዴግ አጀንዳዎች አይደሉም!

ከይኄይስ እውነቱ

ዜግነትን የማያውቅ፣ በጐሣ/ነገድ ማንነት ላይ ተመሥርቶ ሚሊዮኖችን አገር አልባ ያደረገ ፣የሕዝብ ሉዐላዊነትንና ግዛታዊ አንድነትን ያልተቀበለ አገዛዝ የመንደር እንጂ አገራዊ አጀንዳ ሊኖረው አይችልም፡፡ በዘር ደዌ የተለከፉ፣ በሥልጣንና ዝርፊያ ሱስ የተጠመዱ ወገኖች ካልሆኑ በስተቀር በትግራይ ሕዝብ ስም የሚነግደው የዘመናችን ፋሽስት (የወንበዶች ስብስብ) ሕወሓት የፈጠራቸው ድርጅቶች እገሌ ከእገሌ ሳይባሉ ለኢትዮጵያ ጠንቆች ስለመሆናቸው አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሚስማማበት ይታመናል፡፡

ኢትዮጵያን የምታኽል ታላቅ አገር እና ፈሪሃ እግዚአብሔር የነበረው ታላቅ ሕዝብ (የዛሬውን አያድርገውና) በነዚህ የአእምሮ ድኩማኖችና ባለጌዎች እጅ ወድቃ የጃርት መብቀያና ባለቤት አልባ መሆኗ በዚህ ዘመን ባልተፈጠርኩ የሚያሰኝ ነው፡፡ የግብር አባታቸው ዲያቢሎስ ከሆነው ከእነዚህ ጉዶች ጋር የተፈጥሮ ‹ዘመድ/ወገን› መሆኔንም እጅግ ተጸየፍኩት፡፡ በተለይ ባለፉት 28 ዓመታት ወያኔ በፈጠረው ቆሻሻ አገዛዝ በአገራችንና በሕዝባችን ላይ የሚታየውንና ሳያባራ የቀጠለውን ኹለንተናዊ ምስቅልቅል ሳስበው ተካክሎ በመበደል የመጣ መርገም ከመሆኑ ውጭ ምን እንደሚገልጸው ግራ ይገባኛል፡፡ ይህች የተቀደሰች ምድር እንዴት ‹የራዓይቶች› እና ‹ኔፍሊሞች› መፈልፈያ ትሁን?

ዛሬ ምድር ላይ ካለው መራር ጽድቅ ጋር ስንጋፈጥ ኢትዮጵያ በመንደርተኞች እጅ ወድቃ አንድ የቤተክርስቲያን ሊቅ ‹‹ለእኔ እናት (ኢትዮጵያ) ማን አዘነላት ሁሉም አፈር ጫነባት›› በማለት የተናገሩትን ያስታውሰኛል፡፡

በእኔ እምነት የማይፈወሰው ነቀርሳ ወያኔ ትግሬ (ሕወሓት) ብቻ ሳይሆን የሱ የእጅ ሥራዎች የሆኑት ኦሕዴድ፣ ብአዴንና ደሕዴን ጭምር ናቸው፡፡ የምንነጋገረው ሳይገባው ኢትዮጵያን እገዛለሁ ብሎ ለጥፋቷ እየተጋ ስላለው ወያኔ/ኢሕአዴግ ስለሚባል ነውረኛ ድርጅት ነው፡፡ ቀደም ባለ ጽሑፌ ከዝንጀሮ ቆጆ ምን ይመራርጡ ስል ገልጬዋለሁ፡፡

በወያኔ ትግሬ ምትክ ወር ተረኛ ሆኖ ራሱን የሰየመው ወያኔ ኦሮሞ (ኦነጋዊው ኦሕዴድ) ሕወሓት በ27 ዓመታት የፈጸማቸውን ነውሮች ሬከርድ በአንድ ዓመት ከመንፈቅ ለመስበር በትጋት ላይ ይገኛል፡፡ የሤራ፣ መጠላለፍና ጥላቻ ፖለቲካውን ከግብር አባቱ ሕወሓት በተማረው መሠረት ዘረኝነቱ÷ግድያው÷በገፍ ማፈናቀሉ÷ዝርፊያው÷ሁሉም ለእኔ ካልሆነ የሚለው ስግብግብነቱ÷ይሉኝታ ቢስነቱ÷ቅጥፈቱ÷የሰብአዊ መብት ረገጣው÷ ኦነጋውያኑ ከሕወሓት ጋር የጻፉት ‹ሕገ አራዊቱ› አይነካብኝ ማለቱ÷አገርን ባጠፋው የጐሣ አገዛዝ አልደራደርም ብሎ መግለጫ ማውጣቱ÷ራሳቸውን እንደ ‹መንግሥት› ከሚቆጥሩ ሽብርተኞች ጋር ያለው ቊርኝት ወዘተ. ሥርዓታዊ ለውጥን ለማምጣት ሳይሆን ሕውሓት የፈጠረለትን ምናባዊ አገር ‹ኦሮሚያ› በ16ኛው ክ/ዘመን የወረራ መንፈስና በሌሎች ኢትዮጵያውያን ኪሣራና መሥዋዕትነት ለማምጣት የሚታገል ነውረኛ ቡድን የመሆኑ አዝማሚያ በግልጽ እየታየ ነው፡፡ ቀድሞውንም ሎሌ ከአሽከርነት በቀር ‹ጌትነትን› ስለማያውቅበት አገራችንን ከገደል ጫፍ ላይ እያደረሳት ነው፡፡

በነውረኝነቱ ተስተካካይ የሌለው፣ ሕወሓትን መስሎና አክሎ ሳይወክለው እወክለዋለሁ የሚለውን ማኅበረሰብ/ነገድ በታሪክ ተወዳዳሪ ለሌለው እልቂትና ሰቆቃ የዳረገው፣ አሽከርነት የባሕርይው የሆነው ሌላ የወያኔ ትግሬ ፍጡር ብአዴን ነው፡፡ አሁንም አጎብዳጅነቱን ለኦነጋውያኑ ኦሕዴድ ለማስመስከር ደፋ ቀና እያለ ይገኛል፡፡ ከፈጣረው ሕወሓት ጋር የሚያደርገው የሰሞኑ እሰጣ ገባ (እውነትም ይሁን ሐሰት) ለኢትዮጵያውያን የሚፈይደው ነገር የለም፡፡ የሥጋት ምንጭ ከሚሆን በቀር፡፡ ምናልባት የቃላት ቊርቋሶው አገርን አደጋ ላይ ሳይጥል ወያኔ/ኢሕአዴግን የመበተን ውጤት ካለው የምናየው ይሆናል፡፡ ስለዚህ ቅሌታም ድርጅት ሳልናገር የማላልፈው ጉዳይ ቢኖር፣ እንኳን በቊጥርና በመልክዐ ምድራዊ ሥርጭት በኢትዮጵያ ታላቅ የሆነውን ነገድ ቀርቶ አንድ ቀበሌን በቅጡ ለማስተዳደር ብቃት÷ወኔና ሐሞት የሌለው ልፍስፍስ ቡድን መሆኑን ነው፡፡ ዘረኝነት የጋራ ገንዘባቸው በመሆኑ ይሄም ቡድን ለኢትዮጵያ÷ለዜጎቿና ለእውነተኛ ሥርዓት ለውጥ የሚቆም ሊሆን አይችልም፡፡ በትንሹ ያልታመነ ማን ለታላቅ ቁም ነገር ይጠብቀዋል?

ሦስተኛውና ሕወሓት እንደ ሸክላ ያበጀው ነውረኛ የመንደርተኞች ስብስብ ደሕዴን ነው፡፡ እንደ ሌሎቹ ሕወሓት-ሠራሽ ድርጅቶች የሕዝብ ውክልና ባይኖረውም፣ በጉልበት ለሚገዛቸው ከ60 በላይ ለሆኑ ጐሣዎች መኖሪያ ለሆነው የኢትዮጵያ ክፍል ማፈሪያ መሆኑ እሙን ነው፡፡ ይህ ቡድን ወያኔ በአቅጣጫ የሰየመውን የኢትዮጵያ ክፍል በዝርፊያና ግድያ ተዋንያን የሆኑ እጅግ በርካታ ተጠርጣሪ ወሮበሎችን አቅፎ የያዘ መሆኑ በስፋት ይነገራል፡፡ በዚህም ምክንያት ትልቁን አገራዊውን ሥዕል ለማሰብ ዓላማም ፍላጎትም የሌለው ቡድን ነው፡፡ የሚጠረጠርባቸውን ግዙፍ ወንጀሎች ለመሸፈን የወያኔ/ኢሕአዴግ አገዛዝ ቀጣይነት እንዲኖረው አጥብቆ የሚሻ ነው፡፡ አሁን ተሰብስቦ የሚዶልተውም የኢትዮጵያ ህልውና÷የሕዝቧ ደኅንነትና መሠረታዊ የለውጥ ፍላጎት አጀንዳው ሆኖ ሳይሆን ለበለጠ ሥልጣንና ዝርፊያ የቋመጡት አመራሮቹ ለጊዜው አምስት በቀጣይ ሃምሳ ክፍለሃገሮች መሥርቶ አገራዊ አንድነትን ማናጋት ነው፡፡ እውነት ድርጅቱም ሆነ ደጋፊዎቹ የነርሱም መኖርና ዋስትና የሚከበረው ኢትዮጵያ እንደ አገር ስትቀጥል መሆኑን ቢያምኑ ኖሮ፣ ኢትዮጵያ ለሁሉም እኩል የምትሆንበትን መንግሥተ ሕዝብ ለማምጣት ይተጉ ነበር እንጂ ወያኔ አገር ለማጥፋት ባዘጋጀው ሰነድ መሠረት መብቱ አለን በሚል ‹ክልል› ወይም ‹ዞን› ካልሆንኩ ሞቼ እገኛለሁ የሚል ጥያቄ ባልተነሳ ነበር፡፡ ወያኔ ከስድሳ በላይ ጐሣዎችን (ከራሱ አጥፊ ቀመር ወጥቶ) ግዛቱን ደቡብ ብሎ ሲሰይም ጊዜ ጠብቆ የሚፈነዳ ቦንብ መቅበሩን በሚገባ ያውቅ ነበር፡፡

ባጠቃላይ ወያኔ ኢሕአዴግ የአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት የሆነው ለውጥ በተለይም ሥርዓታዊ ለውጥ አጀንዳው አይደለም፡፡ ዓላማውም ፍላጎቱም አይደለም፡፡ ብቃቱም የለውም፡፡ ፍጥረቱም አይፈቅድለትም፡፡ የሚገርመኝ የነርሱን ንትርክ ወይም እንካ ስላንቲያ÷ስብሰባ ርእሰ ጉዳያችን አድርገን እኛም ጊዜያችንን ስናጠፋና ስንነታረክ መገኘታችን የቆሻሻ ፖለቲካቸው ሰለባ መሆናችንን የሚያመለክት ይመስለኛል፡፡ ወያኔን እያጀብን የሚጥልልን የነገር አጥንት ዙሪያ እንደ ጉንዳን መሰባሰቡን የምናቆም መቼ ይሆን?

Filed in: Amharic