>
9:46 am - Thursday August 18, 2022

ወደድንም ጠላን - ሁላችንም - የወያኔ የእጁ ስራ ውጤት ሆነናል!!! (አሰፋ ሃይሉ)

ወደድንም ጠላን – ሁላችንም – የወያኔ የእጁ ስራ ውጤት ሆነናል!!!
አሰፋ ሃይሉ
“ወይ ታሪክ ዋሽቷል ፥ ወይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወኔውን ሸንቶታል!”
          – ሌተና. ኮ/ል ጓድ መንግሥቱ ኃይለማርያም
ጓድ መንግሥቱ በግድ ታፍሶ በሚዋጋ የውጊያ ሞራል በሌለው ሠራዊት እና ከእግር ጥፍሩ እስከ ራስ ፀጉሩ በዘረኝነትና ጥላቻ እልህ በተንተከተከ አጥፍቶ-ጠፊ ሠራዊት መካከል ያለው የመዋጋትና ገሎ የመሞት ተነሳሽነት ልዩነቱ የሠማይና የምድር ያህል የሚራራቅ መሆኑ የተገለጠላቸው አልመሠለኝም።
ኮሎኔሉ የሚያውቁት ታሪክ ደግሞ ደጋግሞ የዘገበውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ጀግንነት ነው። እና ወስፌ ቅቤን አልወጋም ብሎ ደግሞ ደጋግሞ ሲለግምባቸው – ወይ በኢትዮጵዊነት ደም ውስጥ ስለተዋሀደው ጀግንነት ታሪክ ደግሞ ደጋግሞ የፃፈው ዋሽቷል፣ ወይ ደግሞ የዘመኔ ኢትዮጵያዊ ወኔውን አንጠፍጥፎ ሸንቶት ሽንታሙ ብቻ ቀርቷል – ብለው ተንጨረጨሩ።
ሌላም ጊዜ ጓድ ኮሎኔል መንግሥቱ – “እንግዲህ ልብን በወታደር ልብ ውስጥ ከፍተን አንጨምር ነገር! ያላስታጠቅነው መሣሪያ የለምኮ! ምን እናድርግ? ችግር ገጠመን እኮ ጎበዝ!” ሲሉ እጅጉን ቅር ባሰኛቸውና እርሳቸው በሥልጣን ዘመናቸው ሁሉ ፈልገው ባጡት የኢትዮጵያውዊነት በታሪክ የተነገረለት ጀግንነት ላይ ሥሞታቸውን እንዳሰሙ ነበር ከሥልጣናቸው የተሰናበቱት!
አይ አለማወቅ! አይ አለመታደል! ያለመታደል ሆኖባቸው መሠለኝ! አንተም ጨካኝ ነበርክ፥ ጨካኝ አዘዘብህ – እንደሚባለው!!
አሁን ከስንት ዘመን በኋላ እኔ ደግሞ የኮ/ሉ አይረሴ አባባል ደግሞ ደጋግሞ እየመጣብኝ ተቸግሬያለሁ። ወይ ታሪክ ዋሽቷል! ወይ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ዕውቀታቸውን ሸንተውታል!! እያልኩ አስባለሁ።
ወያኔዎች ባብዛኛው ጠብመንጃ ከመተኮስና ገሎ ለመሞት ፈቃደኛ ከመሆን ውጭ ፊደል ያልቆጠሩ፣ ታሪክን ያላጠኑ አንዳች ነገር ስለሀገርና ስለዓለም የማያውቁ ጥልቅ መሀይማንን ከእረኝነትም፣ ከመስክም ከጢሻም ከበረሃም አሰባስባ ነበር ጦርሠራዊቷን የመሠረተችው።
እንግዲህ ያ ወታደራዊ ሥልጠናና ዓለማዊ ዕውቀት የሌለው የገበሬ ሠራዊት ነበረ የሠለጠነውንና የተማረውን የኢህአፓ ሠራዊት በአሲምባ ላይ አፈር ያለበሰው። ያ ያልተማረ የወያኔ ሠራዊት ነበረ የሠለጠነውን የኢትዮጵያ ጦርሠራዊት እንደ ወፍቆሎ አርግፎ አዲስ አበባ ድረስ የዘለቀው። ያ የማይማን ሠራዊት ነው የአራት ኪሎን ቤተመንግሥት የተቆጣጠረው።
ያ ያልተማረ ያልተመራመረ የወያኔ ሠራዊት ነው ለ3ሺህ ዘመን የቆየውን በታሪክ ድርሳናት የተረጋገጠውን የኢትዮጵያ የ3ሺህ ዓመት ታሪክ ጨርግዶ ወደ 100 ዓመት ታሪክነት ያጣፋው።
ያው ራሱ ጥልቁ የወያኔ ኃይል ነው ለ20 ክፍለ ዘመናት የኖረውን የኢትዮጵያ ነባር ሕዝቦች ታሪክና የግዛት አስተዳደር በትልቅ የማይማን ላጲስ ደምስሶ – በታሪክ ታይቶ ተሰምቶ የማይታወቅ “ኦሮሚያ” የሚል “ክልል” የፈጠረው።
ያው የወያኔ ያልሠለጠነ ሠራዊት ነው የ3ሺህ ዓመት የኢትዮጵያን የሥልጣኔና የሥልጣን ታሪክ ሽሮ – በታሪክ ያልነበረ – “አማራ” የሚል “ክልል” የፈጠረው!!
ከህንድ ሀገር የዕደጥበብ ባለሙያዎችን እያስመጣ ቤተመንግሥቱን ያሳንፅ የነቀረው፣ ሌላ ቀርቶ በምኒልክ ራሱ እንዲጠፋ ያልተደረገው ታላቁ የአባጂፋር ክፍለሀገር ከፋ የሚባለው የእነ ጋኪ ሴሮቾ የንጉሣን አስተዳደር ሲተዳደር የነበረው ታሪክ ከጥንት የመዘገበው ክፍለሀገር የት ገባ? ወያኔ ከታሪክ ደመሰሰው!!
የእነ ካዎ ጦና ጥንታዊ ሀገር ወላይታ የት ገባ? ሲዳሞስ? ወያኔ “ደቡብ” በሚል ላጲስ ከታሪክ ደመሰሰው!!
በራሱ ንጉሥ በራሱ አስተዳደር ከጥንት ጀምሮ ሲተዳደር የኖረው የፋሲል ሀገር፣ የበካፋ ሀገር፣ የምንትዋብ ሀገር ጎንደር ከሀገሪቱ ክፍለሀገርነት ምን ፋቀው? የት ገባ? የወያኔ ጥልቅ ሠራዊት “አማራ” በሚል ትልቅ “ክልላዊ” ቅርጫት ውስጥ ጨምሮ ከአስተዳደር ታሪክ ደመሰሰው!
የንጉሥ ሚካኤል ሀገር፣ የወረሼሆች ሀገር ጥንታዊው የወሎ ክፍለሀገር የት ገባ? የንጉሥ ተክለሀይማኖት ሀገር ከጥንት ጀምሮ በታሪክ የተመሠከረለት የራሱ አስተዳደር የነበረው የጎጃም ክፍለ ሀገር የት ገባ? የወያኔ ጥልቅ ሠራዊት “አማራ” በሚል ትልቅ “ክልላዊ” ቅርጫት ውስጥ ጨምሮ ከአስተዳደር ታሪክ ደመሰሰው!
በታሪክ አውሮፓ ድረስ በሚፃፃፋቸው ባለማተም የነገሥታት ደብዳቤዎች ጭምር ታሪክ የመሠከረለት የንጉሥ ሳህለሥላሴ ሀገር፣ የኃይለመለኮት ሀገር፣ የእነ ስብስቴ ነጋሲ ክፍለሀገር ሸዋ ፣ ሸዋን ምን ዋጠው? እርሱንም የወያኔ ጥልቅ ሠራዊት “አማራ” በሚል ትልቅ “ክልላዊ” ቅርጫት ውስጥ ጨምሮ ከአስተዳደር ታሪክ ደመሰሰው!
ከሁለት ክፍለዘመናት በፊት ዓለማቀፍ የክርስቲያን ሚሲዮናውያን የመጀመሪያውን መፅሐፍ ቅዱስ ከጀርመን ወደ ኦሮምኛ ተርጉመው የሰበኩበት በራሱ ነገሥታትና ሰዎች ሲተዳደር የኖረው ጥንተ ታሪክ ያለው የወለጋ ክፍለሀገር የት ጠፋ? ምን ዋጠው? እርሱንም የወያኔ ጥልቅ ሠራዊት “ኦሮሚያ” በሚል ትልቅ “ክልላዊ” ቅርጫት ውስጥ ጨምሮ ከአስተዳደር ታሪክነት ደመሰሰው!
የአዳል ሡልጣኖችን ሀገር፣ የመስጊዶቹን ሀገር፣ የግራኝ አህመድን ሀገር፣ የእነ ምኒልክንም የእነ ራስ መኮንን ወልደሚካኤል ጉዲሳንም ሀገር ሐረርጌን በታሪክ ከታወቀለት ክፍለሀገርነት ምን ፋቀው? የወያኔ ጥልቅ ሠራዊት እርሱንም “ኦሮሚያ” በሚል ትልቅ “ክልላዊ” ቅርጫት ውስጥ ጨምሮ ከአስተዳደር ታሪክ ደመሰሰው!
ባሌስ? ሱጴስ? የእመቤቲቱ አድባር በታሪክ የነገሠችበት አሩሲስ? ባሌስ? ኢሉባቦርስ? ሁሉንም የዘመናት ታሪክ የሚያውቃቸውንና የመዘገባቸውን የራስ አስተዳደሮችና ሕዝቦች ምን ዓይነት የታሪክ ዳምጠው መጥቶ ነው ከታሪክ መዝገብ እየዳጠ ታሪካዊ ህልውናቸውን ሽሮና ጨፍልቆ በመሰለውና ባሻው የ”ክልል” ከረጢት ውስጥ አስገብቶ የጠፈጠፋቸው? የገጠገጣቸው?
አዎ። ታሪክ ደላዡ ወያኔ ነው። የወያኔ ጥልቅ ሠራዊት ነው ሁሉንም በታሪክ የታወቁ Ethiopian self-governing peoples and entities “አማራ” “ኦሮሞ” “ደቡብ” በሚሉ ትላልቅ “ክልላዊ” ቅርጫቶችና አንቀልባዎች ውስጥ ጨምሮ ከአስተዳደር ታሪክ ጨርሶ የደመሰሳቸው! ለዚህም ሥር-ኖል ድምሰሳው ነው “አብዮታዊ!” የሚል የጥፋት ማዕረግ ለራሱ የጫነው!! ወደድንም ጠላን – ሁላችንም – የዚህ የወያኔ አብዮት ፍጡራን ሆነናል!
ሌላ ቀርቶ አፍንጫው ሥር ያለውን የአክሱምንና የአክሱም ፅዮንን የሶስት ሺህ ዓመት ታሪክ ለማወቅ የተሳነው የወያኔ አላዋቂ  ሠራዊት ታሪክንና ሕዝብን ሁሉ ፍቆና ደምስሶ በአቦሰጡኝ የፈጠራቸውን ከታሪክ የተከለሉ የክልል ተብዬዎች ትርክት እንዴት ይሄ ሁሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ ቦይ ውሃ ከማይማኑ ጋር እየፈሰሰ ሲያላዝን ኖረ??
እንዴት አላዋቂዎች ይሄን ሁሉ ድፍረት ትጥቷቸው ኢትዮጵያን በማይም ላጲስ ሲሰርዙና ሲደልዙ – ይህ ሁሉ የታሪክ ኦማ በሀገሪቱ ገብቶ የነበረውን ሁሉ ሲያወድም – ይህ ሁሉ ሲሆን – የኢትዮጵያ ሕዝብ ምንድን አፍዝዞት ነው እንደ መንፈሰ ቀሊል ዝም ብሎ በተቀደደለት ዲብ መፍሰሱን የቀጠለው??
አሁንስ ለምንድነው በሌለና በመሀይማን በተጠፈጠፈ የክልል ትርክት ውስጥ – ከገበሬ እስከ ፕሮፌሰር ሰምጠን የምንጃጃለው? እንዴት ከወያኔ አላዋቂ ሠራዊት የሚሻል የሀገር አስተዳደር ማዋቀር ተሳነን?
የወያኔ ሠራዊት ከሞነጫጨረው የተሻለ አዲስ ሀገራዊ አስተዳደርን ማሰብና ማዋቀር ቢያቅት – እንዴት ታሪክ በወፋፍራም ቀለሞች ያሰመረባቸውን፣ የፃፋቸውን፣ ያወቃቸውን፣ ለዘመናት አብረውን የኖሩትን የሕዝብ አስተዳደሮችና ነባር ስሪቶች ማስታወስ እንዴት ተሳነን?
ምን ዓይነት አፍዝ አደንግዝ ቢረጭብን ነው ሁሉም ሁላችንም ተላላ ሆነን የቀረነው? ጥልቁ ወያኔ እንዴት ሁላችንንም እንዲህ ፉዞ አድርጎ አጃጅሎ አስቀረን?
ወላዲተ አምላክን!! (ካስፈለገም – ወላሂ ለአዚም!!) የምሬን እኮ ነው የምንጨረጨረው!!! ወይ ታሪክ ዋሽቷል? አሊያ የኢትዮጵያ ሕዝብ ማሰቢያውን ሸንቶታል! አለበለዚያ ግን ከወያኔዎች ቅዠት የተሻለ ዘላቂ ሥርዓትን ይፈጥራል/ያዋቅራል!!!
ግራ ገባን እኮ እንዲህ አፍዞ ያስቀረን ነገር!
መፍዙዛችንን ከዓይናችን ይግፈፍልን አቦ!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ።
የተሰወረ ልቦናችንን ይመልስ።
አበቃሁ።
Filed in: Amharic