>
5:13 pm - Tuesday April 20, 1328

የአዲስ አበባ ስነ ልቦና 101 - በተለይ ለኦህዴድ ሰዎች (አቤል ዋቤላ)

የአዲስ አበባ ስነ ልቦና 101

በተለይ ለኦህዴድ ሰዎች

 

አቤል ዋቤላ

“የሆነ አጓጉል የበቀለ ከተማ የተሰበሰበ ልሂቅ አለ፡፡” አንድ ጎጠኛ ነው እንዲህ ያለው፡፡ ስለሚያወራው ነገር ትንሽ እውቀት ይኖረው ይሆን ብዬ የህይወት ታሪኩን ፈተሸኩኝ፡፡ ውጭ ሀገር ነው የተማረው፡፡ ቢበዛ አዲስ አበባ የመጣው ስድስት ኪሎ ካሉት አንበሶች ጋር ፎቶ ሊነሳ ነው፡፡ ስለማያውቀው አዲስ አበባ ነው የሚያወራው፡፡

ሌላ ደግሞ አለ በልጅነቱ ወይም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመድቦ የሚመጣ፡፡ ከአዲስ አበባ ባህል ጋር ራሱን ማዋሀድ ያቃተው፡፡ የችሎታው ማነስ የሚመጣው እሱ ስለአዲስ አበባ ካለው አረዳድ ነው፡፡ አንዳንዱ እዚሁ ሸገርም ተወልዶም ቤቱ ውስጥ ባለው ጎጠኛ ዲስኩር ምክንያት ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች ጠላትነት የሚያዳብር፡፡ ሌላው ደግሞ የሆነ ርዕዮተ ዓለም ይጫነውና የአዲስ አበባ ነዋሪ እና የከተማዋ መኖር በራሱ ያበሳጨዋል፡፡

ይህ የሚመጣው የከተማውን ነዋሪ ስነ ልቦና ካለመረዳት ነው፡፡ የአዲስ አበባ ማኀበረሰብ እንደሌሎች ከተሞች ሂፕ ካልቸር የተጫነው አይደለም፡፡ አዲስ አበባ በአብዛኛው ለሀገር ቤት ማኀበረሰብ ልማድ እና ባህል እውቅና የሚሰጥ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ህዝብ ከልቅነት ይልቅ ለወግ አጥባቂነት ያደላል፡፡ ይህም ማለት በአዲስ አበባ የኢትዮጵያ ትራዲሽኖች ቦታ አላቸው ማለት ነው፡፡

የአዲስ አበባ ህዝብ የኑሮ ልማድ የኢትዮጵያውያን የተለያዩ እሴቶች ማቀናበሪያ ቤተ ሙከራ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ህዝብ ልማድ በአንድ ቦታ የረጋ አይደለም፡፡ ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የሚመጡ ባህሎች እና ልማዶችን ገንዘቡ የሚያደርግ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ልማዶች ብቻ ሳይሆን ከባህር ማዶ ወደ ሀገር ቤት የሚሻገሩ የባህል ዘውጎች በአዲስ አበባ ይስተዋላሉ፡፡ የምዕራብም የምስራቅም ባህል ትቀበል እንጂ አዲስ አበባ ለኢትዮጵያ ማኀበረሰብ የባህል እሴቶች ታዳላለች፡፡

ከየትኛውም ማኀበረሰብ ይምጣ፣ የትኛውንም ቋንቋ ይናገር የስነ ልቦና ችግር ከሌለበት አዲስ አበባ ተወልዶ ካደገው ከአብዛኛው የአዲስ አበባ ልጅ የተሻለ የስኬት እድል ይኖረዋል፡፡ ይህ ድምዳሜ ስንኖር ያየነው እንጂ በጥናት የተደገፈ አይደለም፡፡ የአዲስ አበባን ልማድ ለማወቅ ካንድ ወር በላይ አይፈጅበትም፡፡ ነገር ግን ይዞት የመጣው ተጨማሪ እሴት የበለጠ ተወዳዳሪ እና አሸናፊ እንዲሆን ያስችለዋል፡፡

አዲስ አበባ ክህሎት ትሸልማች፣ ጥረትን ታከብራለች፣ ልዩ ተሰጥኦን ታመልካለች፡፡ ማህሙድ አህመድ እና ጥላሁን ገሠሠ በዚህ ሂደት ያለፉ የአዲስ አበባ ፈርጦች ናቸው፡፡ እነርሱን ተዋቸው፡፡ አሁን አማርኛ መናገር ማይችሉ የአዲስ አበባ መንገዶችን የሞሉትን ሊስትሮዎች ጠይቁ፡፡ እነርሱ እና ሌሎች ታታሪ ኢትዮጵውያን የዚህ ህያው ምስክር ናቸው፡፡ ታምራት ነገራ ከስደት የተመለሰ ሰሞን የአዲስ አበባ መንገዶች ሊንጓ ፍራንካ ወላይተኛ ነው ብሎ መጻፉን አስታውሳለኹ፡፡ ጎበዝ ሆነህ በስራ የምታምን ከሆን አዲስ አበባ እንዲህ በዋዛ፣ በተፈጥሯዊ መንገድ የምትወራት ከተማ ናት፡፡

አዲስ አበባ ክፉ አመል አለባት ከተባለ ወደ ከተማዋ በሚመጣው ሰው ላይ ማሾፍ እና ሙድ መያዝ መውደዷ ነው፡፡ ይህ ግን ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ እና ክብረነክ አይደለም፡፡ መረን የለቀቀ ሲሆን ራሱ የከተማው ሰው ያንን ባለጌ ተው ለማለት ከፍ ሲልም ከመቅጣት አይመለስም፡፡

አዲስ አበባ ስልጣን፣ ቀበሌ፣ ኦውቶሪቲ፣ ገለመሌ አትወድም፡፡ የፖለቲካ ስልጣን ሹመኛ ከማኀበረሰቡ ራሱን ይነጥላል ወይም ሹመኛውን ማኀበረሰቡ በስልት በሩቁ ያደርገዋል፡፡ የተወሰኑ የሚያሸረግዱለት በዙሪያው ቢኖርም ከማኀበረሰቡ ልብ ውስጥ ግን ቦታ አይኖረውም፡፡ የፖለቲካ ስልጣን ከከተማዋ ጋር ሆድ እና ጀርባ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ሰው ቀበሌ ወዶ አይሄድም፤ መዘጋጃ ቤትም ጠላቱ ነው፡፡ ለዚህ ከኢህአዴግ በላይ ምስክር የለም፡፡

አዲስ አበባ ዘረኝነትን በጣም ትጠየፋለች፡፡ ከስሪቷ ጋር ስለማይሄድ ያንገሸግሻታል፡፡ አዲስ አበባ መማር የምትፈልገው የምግቡን አሰራር ለገበታዋ ማጣፈጫ፣ ቋንቋው ለአራዳ መዝገበ ቃላቷ ማስፋፊያ፣ ጭፈራውን ለአሸሸ ገዳሜ ማድመቂያነት እንጂ አጥንት እና ዘር ቆጠራውን አይደለም፡፡

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የባህል ክንዋኔዎች ጥዩፍ አይደሉም፡፡ ተጨማሪ ቡና መጠጫ መድረክ፣ አዳዲስ የመዝናኛ ኹነቶች፣ የሽቀላ ዕድል እንደሚያመጣላቸው ጠንቅቀው የሚያውቁ የሰለጠኑ ናቸው፡፡ የአዲስ አበባ ህዝብ የሚጠላው የፖለቲካ ስልጣንን(ጉልበትን) ተገን አድርጎ የሚመጣ የባህል መገለጫ ነው፡፡

ከጥቂት አመታት በፊት አሸንዳ በሀያ ሁለት እና ቦሌ አከባቢ ጉልህ ክስተት ሆኖ ይከበር ነበር፡፡ የአዲስ አበባ ነዋሪ ግን በማድፈጫው ወራት ውስጥ ሆኖ በበጎ አልተመለከተውም፡፡ የቆነጃጅቱን ጸዐዳ ቀሚስ እና የሚስረቀረቅ ድምጽ አይደለም የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የጠሉት፡፡ ወያኔ ባመቻቸላቸው ዕድል ተጠቅመው መጀመሪያ የፖለቲካ የበላይነት፣ በመቀጠል የኢኮኖሚ የበላይነት ባገኙት፣ ከዚያም ይህ የሀብት ሙቀት የሚፈጥረው የባህል መገለጫን ነው የተጠየፉት፡፡

የኦህዴድ መሪዎችም የአዲስ አበባ ነዋሪን ስነ ልቦና የተገነዘቡ አይመስሉም፡፡ ባህልን ከፖለቲካ ስልጣን የበላይነት/ የተረኝነት ስሜት ነጥለው ማቅረብ አልተቻላቸውም፡፡ መሀል ኢትዮጵያ ላይ ከኢትዮጵያ ማኀበረሰብ አንዱ የሆነው የኦሮሞን ባህላዊ ክንዋኔ ለማካሄድ ታሪክን ማጣመም አያስፈልግም፡፡ የፖለቲካ ስልጣን ግን ያንን ያደርጋል፡፡ ሎጂክ የተማረ ሰው፣ በተፋለሰ ትርክት የሚታመስ ህዝብን የሚያስተዳደር መሪ ይህችን ትንሽ ጥንቃቄ አለማድረጉ ይገርማል፡፡ እነ ዶ/ር አምባቸው ከህዝብ ይልቅ ለእነርሱ የሚቀርቡ መሪዎች ነበሩ፡፡ ቢያንስ በህወሓት ፊት ተደጋግፈው ቆመዋል፡፡ ታዲያ እነርሱን መስዋዕት ያደረገው የፖለቲካ ትኩሳት አደገኛነት እንዴት መረዳት ይከብዳል?

በእጃቸው በደንብ ያልያዟትን የስልጣን አርጩሜ የወያኔ ግፍ ባደቀቀው አዲስ አበቤ ላይ መሰንዘር ለማንም አይጠቅምም፡፡ ኃይል ማሳየቱን ወደጎን አድርጉት፡፡ ህዝቡን የራሱን ባህል እንዲጠየፍ አትገፋፉ፡፡ በወንድማማች መካከል ጥላቻን አትዝሩ፡፡ ባይሆን ችግር የሚሆነው መስቀል አደባባይ ቆሽሾ አቢቹ ስራ እንዳይበዛበት ነው፡፡ አታስቡ በመጥረጉ እናግዘዋለን፡፡ እናንተም የዘረኝነት ትርክታችኹን አስወግዱ፡፡

Filed in: Amharic