>

ፍርሃትን አታንግሱት! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ፍርሃትን አታንግሱት!
ያሬድ ሀይለማርያም
ማህበረሰባችን በሦስት ክፉ ነገሮች ሲሰቃይ ዘመናትን አስቆጥሯል። ከሦስቱ አንዱ ፍርሃት (fear) ነው። ሁለቱ ክፉ ነገሮች ደግሞ ተስፋ ማጣት የወለደው ጨለምተኝነት (hopelessness) እና የሃገር ባለውለታ የሆኑ ግለሰቦችን፣ ተቋማትን፣ እሴቶችን እና ትውፊቶቻችንን ማቃለል ወይም ማዋረድ (humiliation) ናቸው። ለጊዜው ሁለቱን የመጨረሻዎቹን ላቆያቸው እና በፍርሃት ላይ ላተኩር ወደድኩ።
ላለፉት አርባ አመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ፍርሃት የንጉሶች ንጉስ ሆኖ ቆይቷል። ሕዝብ በፍርሃት ውስጥ እየማቀቀ እንዲኖር ተደርጓል። የሚገርመው ግን በሕዝብ ላይ በጉልበት የነገሱት የአገዛዝ ሥርዓቶቹም ከሕዝብ በላይ በፍርሃት ይማቅቁ ነበር። ፍርሃታቸው በጨመረ ቁጥር የአፈና ሸምቀቋቸውን ያጠብቁት ነበር። ፍርሃታቸው ትንሽ እረገብ ሲል እንዲሁ ለሕዝብ አንጻራዊ ነጻነትን ለቀቅ ያደርጉ ነበር። ብቻ ሕዝብን የሚጋልቡበት የሥልጣን ፈረስ ልጓሙ ፍርሃት ነበር።
ፍርሃት በማህበረሰባችን ውስጥ እና በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ያሳረፈውን ጫና በተመለከተ የዛሬ አምስት አመት “የፍርሃት ባህልን እያነገሰ ያለው የኢትዮጵያ ፖለቲካ፤ አንድ እርምጃ ወደፊት ሁለት ወደ ኋላ” በሚል ርዕስ https://humanrightsinethiopia.wordpress.com/2013/12/ ተከታታይ ጽሁፍ ጽፌ ነበር።
ሕዝብ መንግስትን እንዲፈራ የሚደረግበት መንገድ በዙ መልክ አለው። ከብዙዎቹ ሁለቱን ባነሳ አገራችን ውስጥ ያለውን የፍርሃት ምንጭ ጥሩ አድርጎ ሊያሳይ ይችላል። አንደኛው በጡንቻ እና አፈና የሚሰርጽ ፍርሃት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ጉልበት ሳይጠይቅ በብልጠት እና ስልት በመቀየስ የሚመጣ ነው። በየመጀመሪያው የፍርሃት ማስረጫ መንገድ ሕዝብን ወይም የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ሂላማ ያደረገ እና ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ መውሰድ ነው። ሰዎችን በአሰቃቂ ሁኔታ በአደባባይ መግደል፣ በጅምላ ብዙዎችን አስሮ ማሰቃየት፣ ዛቻ እና ማስፈራሪያ፣ ማዋከብ እና በማህበረሰቡ ውስጥ ጎልተው የወጡ ሰዎችን በተለየ ሁኔታ የጥቃት ሂላማ በማድረግ ማሕበረሰቡን ማሸማቀቅ እና እገሌን ያየ በእሳት አይጫወትም እያለ መንግስትን እንዲፈራ ማድረግ ነው። የተሳካለት የማፈኛ ስልት ሆኖ ቆይቷል።
ሁለተኛው ፍርሃት በሕዝብ ውስጥ እንዲሰርጽ ማድረግ የሚቻለው ሰዎች የደህንነት ዋስትና እንዲያጡ በማድረግ ነው። መንግስት በቀጥታ እርምጃ ባይወስድም እኔን ካልደገፍክ እና ከእኔ ጎን ካልቆም የሌሎች ጥቃት ሰለባ ትሆናለህ በሚል በእጅ አዙር ፍርሃትን ማስረጽ ነው። የህዝብን ደህንነት አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ትናንሽ ጉልበተኞችን ሆን ብሎ በማደራጀት ወይም እንዲደራጁ እድሉን በመፍጠር ሕዝብን ስጋት ላይ መጣል እና የምታደግህም እኔው ብቻ ነኝ ብሎ ዘብ መቆም። ይህ አይነቱን ስልት በርካታ ለዘብተኛ አምባገነኖች ወይም ከፊል ዲሞክራት (partial dictatorial or partial democrat) የሆኑ መንግስታት የሚጠቀሙበት ስልት ነው። ሕዝብ በሥልጣን ላይ ያለው ኃይል ከሌለ እጠፋለሁ፣ መተላለቅ ይፈጠራል፣ አገር ይወድማል በሚሉ ያልተጨበጡና ምናባዊ በሆኑ ወይም ባፈጠጡ ስጋቶች ተሸማቆ ከአደጋው ለመዳን ገዢውን ኃይል የሙጥኝ ብሎ እንዲይዝ የማድረግ የብልጣብልጦች ስልት ነው።
በዚህ አይነቱ ስልት ውስጥ ሕዝብ ምርጫ ቢሰጠው እንኳ የሚመርጠው ይህንኑ ኃይል ስለሆነ ነጻና ፍትሐዊ የሚመስል ምርጫ እኳን ቢካሄድ ሕዝብ በመንፈስ ተጽዕኖ ስር ስለወደቀ ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል።
ላለፍቱት ሃያ ሰባት አመታት ሕውሃትን ሲፈራ የኖረው ሕዝብ ዛሬ ብዙ የሚፈራቸው ኃይሎች ተፈጥረውበታል። የፍርሃት ድባቡ መልኩን ቀይሮ እና በብዙ መልኩ ምናልባትም ካለፈው ጊዜ በባሰ ሁኔታ በሕዝብ ዘንድ የነገሰ ይመስላል። ሕዝብ ትላንት መንግስትን በሚፈራበት መጠን ዛሬ መንግስትን አይፈራም። ነገር ግን ሌሎች የሚፈራቸ በርካታ ኃይሎች ግን በሕውሃት እግር ስር ተተክተዋል። ከዛሬ አሥር አመት በፊት በኢትዮጵያ ህልውና ላይ ከነበረው ስጋት ይልቅ ዛሬ ያለው ስጋት በብዙ እጥፍ ጨምሯል። የዛሬ አስር አመት ኢትዮጵያን ያሰጋት የነበረው የመፈራረስ አደጋ ሳይሆን የአንባገነን ኃይል መፈርጠም ነበር። ዛሬ ደግሞ በተቃራኒው ኢትዮጵያ የመፍረስ አደጋ ያጋጥማታል የሚለው ስጋት እየጨመረ እና የመንግስት ጡንቻ የረገበበት ሁኔታ ላይ ነን ያለነው።
ዛሬ ሕዝብ ከመንግስት ይልቅ አክራሪ ብሄረተኞችን፣ ትጥቅ ሙሉ በሙሉ ያልፈቱ ተቃዋሚ ኃይሎችን፣ በየመንደሩ የታጠቁ ቡድኖችን እና ግለሰቦችን፣ የተደራጁ ማጅራት መቺዎችን እና በማህበራዊ ንቅናቄ ስም እራሳቸውን አደራጅተው ለውጡን እየገፉ እዚ ያደረሱና ብሔርን ማዕከል ያደረጉ ቁጡና ሥርዓት አልባ የሆኑ ወጣቶችን አጥብቆ ይፈራል። ሕዝብ ከመንግስት አስፈሪነት ተላቆ በነጻነት መኖርን ተለማምዶ ሳይጠግብ እነዚህ የመንደር ኃይሎች መልሰው ፍርሃት ውስጥ ከተውታል። መንግስትም እነዚህን ኃይሎች በጊዜ በሕግ ጥላስር ማዋል አንድም አልቻለም፤ አለያም አልፈለገል።
ሕዝብ አገር ሊተራመስ፣ ግጭት ሊፈጠር እና ሥርዓት አልበኝነት ሊነግስ ይችላል በሚል ስጋት ውስጥ ገብቷል። በየቀኑ በመንግስት ሚዲያዎች ጭምር የሚነገሩት ስጋት አዘል ዜናዎች ሕዝብን ሽብር ውስጥ የሚከቱ ናቸው። ሕገ ወጥ መሳሪያ ተያዘ፣ ሰዎች ባልታወቁ ኃይሎች ተገደሉ፣ ታፈኑ፣ ንብረት ወደመ ወዘተ … የሚሉ ወሬዎች ከየቀኑ ዜና ስርጭት ላይ አይጠፉም። በተለይም መንግስት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚፈጸሙ ጥቃቶችን እነማን እዳደረጉት እያወቀ ‘በአንዳንድ ኃይሎች’ እያለ የሚሰጠው መግለጫ ሕዝብን ሆን ተብሎ ስጋት ውስጥ ለመጨመር የተፈለገ እስኪመስል ድረስ ተደጋግሞ ተገልጿል። ሕዝብ መንግስት ሊቆጣጠራቸው ያልቻለ እና ከአቅሙ በላይ የሆኑ ኃይሎች አሉ ብሎም እንዲያስብ አድርጎታል። በመሆኑም በሰላም ወጥጬ በሰላም እቤቴ እገባለው የሚል እምነት እንዳይኖረው አድርጎታል። ያ ብቻም ሳይሆን ለአንድ ቀን መንግስት ባይኖር ደግሞ እነዚህ ማንነታቸው የማይገለጽ ኃይሎች እቤቱም ጅምር በሰላም እንደማያስተኙት እንዲያስብ ተደርጓል።
ይህ አይነቱ በፍርሃት እና በስጋት የሚገኝ የሕዝብ ድጋፍም ለጊዜው የመንግስት የሥልጣን ህልውና መሰረት ቢሆንም እያደር ግን ብዙ መዘዞችን ያስከትላል። ወያኔ በዱላ እና በአፈና ያሰረጸውን ፍርሃት ኦዴፓ መራሹ መንግሥት ደግሞ ሕዝብን ለአጥቂዎች ስጋት በማጋለጥ ሊያተርፍበት አስቦ ከሆነ ከወዲሁ አያዋጣምና ተዉት ለማለት እደፍራለሁ። እርስ በርስ እየተጎነታተላችው፣ አልፎ አልፎም እየተጋደላችው፣ የሕግ የበላይነትን ለሥርዓት አልበኞች ምርኮ አድርጋችው አሳልፋችው ሰጥታችው፣ ሕዝብን የሚያሸብሩ እና ስጋት ውስጥ የሚጥሉ ፕሮፓጋንዳዎች እንዲተናኙ እድል እየፈጠራችው ሕዝብን የፍርሃት ምርኮኛ ለማድረግ የሚታዩት አንዳንድ ምልክቶች ለማንም አይበጁም።
ንግግሮቻችሁ ከወዲሁ በዛቻ እና በማስፈራሪያ እየተሞሉ ነው። የሰሞኑ የህውኃት እና የአዴፓ ንትርክ አንዱ ማሳያ ነው። ሕዝብ ዛሬ በእናንተ ስህተትም ሆነ በእርስብ በርስ መናቆር የሚመጣውን አደጋ እያሰበ ስጋት ውስጥ ነው። በላዩ ላይ በለውጥ አራማጅ ስም የተደራጁ ኃይሎችን ይፈራል። ሕዝብ ቄሮን፣ ፋኖን፣ ኤጆቴን እና ሌሎች የየመንደሩን ጉልቤዎች ይፈራል።
ፍርሃትን እያነገስን ዲሞክራሲያው ሥርዓትን ልንገነባ አንችልም። የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መሰረቱ ነጻነት ነው። ነጻነት ማለት ከፍርሃት መላቀቅ ነው። በፍርሃት ቆፈን ውስጥ ያለ ማህበረሰብ አንባገነኖችን የሚያበቅል ሰፊ ማሳ ነው። ኢትዮጵያ ከቀበሌ ሊቀመናብርት አንስቶ እስከ አገር መሪ አንባገነኖችን በየጊዜው እንደ አሸን የምታፈራ አገር የሆነችው በቀይ ሽብር እና ከዚያ ወዲ በተፈጠሩ አሰቃቂ ጥቃቶች እንዲሸማቀቅ እና በፍርሃት እንዲኖር የተደረገ ሕዝብ አንባጋነኖቹ መፍጠር ስለቻሉ ነው።
ሕዝብን ሆን ብሎ በጉልበቱ በሚያስፈራራ እና በእጅ አዙር በፍርሃት ውስጥ እንዲወድቅ አድርጎ የመንግስት ጥገኛ እንዲሆን በማድረገ በኩል ያለው ልዩነት የስልት እንጅ የውጤት አይደለም። ሁለቱም አላማቸው በሕዝብ ላይ ተፈናጦ ለረዥም ጊዜ በሥልጣን ላይ መቆየት ነው። እውነተኛ ዲሞክራሲ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲመጣ ከተፈለገ ከምርጫው በፊት ሕዝብን ከፍርሃት እና ከስጋት ነጻ አውጡት። በነጻነት ያስብ፣ በነጻነት ይደራጅ፣ በነጻነት ሃሳቡን ይገልጽ፣ በነጻነት እምነቱን ያራምድ፣ በነጻነት በአገሪቱ ውስጥ ይንቀሳቀስ።
ይቺ ፍርሃትን በጅ አዙር የማንገስ አካሄድ እያደር ጉልበት ከታከለባት እንደገና ‘አዲስ ንጉስ እንጂ ለውጥ መቼ መጣ …’ በምትለው የቴዲ አፍሮ ዜማ ልንቆዝም ነው። ከዛያስ ያውጣን።
በቸር እንሰንብት!
Filed in: Amharic