>

የጋዜጠኛ ኤልያስ ጠበቃ “አካልን ነፃ የማውጣት” አቤቱታ አቀረቡ (የትነበርክ ታደለ)

የጋዜጠኛ ኤልያስ ጠበቃ “አካልን ነፃ የማውጣት” አቤቱታ አቀረቡ
የትነበርክ ታደለ
በእሥር ላይ የሚገኘው የጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ጠበቃ፣ አቶ ተማም አባ ቡልጉ “አካልን ነፃ የማውጣት” (ሃቢየስ ኮርፐስ) አቤቱታ፣ ዛሬ ማክሰኞ ሐምሌ 9 ቀን 2011 ዓ.ም ለፍርድ ቤት ማቅረባቸውን ለኢትዮ-ኦንላይን አስታወቁ፡፡
አዲስ አበባ ፖሊስ፣ ጋዜጠኛ Elias Gebru Godana በሕገ-ወጥ መንገድ እንደያዘው ጠበቃ ተማም አባ ቡልጉ ፍርድ ቤት በአካል በማቅረብ በነፃ እንዲለቀው ጠይቀዋል፡፡
ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ጎዳና፣ በአዲስ አበባ ፖሊስ ሽንት ቤት አጠገብ ለብቻው ጨለማ ቤት በመታሰሩ፣ የ‹‹ሳይነስ›› ህመሙ ተቀስቅሶ እየተሰቃየ ነው ያሉት ጠበቃ ተማም፤ ፖሊስ ሕክምናም አልፈቀደለትም፤ ይህ ሕገ-ወጥ ብቻ ሳይሆን ኢ-ሰብዓዊነትም ነው በሚል አቤቱታቸውን ለፍርድ ቤት አቅርበዋል፡፡
ጠበቃ ተማም አባ ቡልጉ፣ ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ፍትሕ-አብሔር ችሎት ባስገቡት አካልን ነፃ የማውጣት አቤቱታ ላይ፣ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንን በሕገ-ወጥ ድርጊት ከሰዋል፡፡
ፖሊስ ጋዜጠኛ ኤልያስን ወንጀል ሲሰራ እጅ ከፍንጅ ሳያገኘው፣ ያለ ፍርድ ቤት መጥሪያ በ29/10/2011 ዓ.ም ከምሽቱ 2፡40 ሰዓት ላይ ማንነታቸው ባልታወቀ ስድስት ሰዎች ከመንገድ ላይ ጠልፎ መያዙ እስራቱን ሕገ-ወጥ ያደርገዋል ሲሉ ለዘጋቢያችን ገልጸዋል፡፡
‹‹ማንንም ሰው አስሮ ምርመራ የማጣራት ሥልጣን ለማንኛውም አካል የሚሰጠው በግልጽና በሕግ ብቻ ነው›› የሚሉት ጠበቃ ተማም አባ ቡልጉ፣ ‹‹ጋዜጠኛ ኤልያስን ያሰረው አዲስ አበባ ፖሊስ፣ የሽብር ወንጀል የማጣራት ሥልጣን የለውም›› ብለዋል፡፡
ከፖሊስ፣ ከደህንነት ወዘተ የተውጣጣና በሕግ ተቋቁሞ ሰው አስሮ ምርመራ የማጣራት ሥልጣን በሕግ የተሰጠው አካል የለም፤ ጋዜጠኛ ኤልያስ የተያዘውና የተሳረው በዚህ ግብረ-ኃይል ነው ቢባልም ይህ አካል ሰው አስሮ ምርመራ የማጣራት ሥልጣን ስለሌለው እስራቱን ሕገ-ወጥ ያደርገዋል ሲሉ ለዘጋቢያችን ገልጸዋል፡፡
የጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ እስር ሕገ-ወጥ መሆኑን የሕግ መርህዎችን ጠቅሰው አካልን ነፃ የማውጣት ክስ ያቀረቡት ጠበቃ ተማም፣ አዲስ አበባ ፖሊስ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ የጋዜጠኛ ኤልያስ ቤትን በመበርበር ተንቀሳቃሽ ስልኮችን፣ ላፕቶፕ ኮምፒውተሮችን እና ልዩ ልዩ ጽሑፎችን ለቅሞ መውሰዱ ሕገ-ወጥ ነው ብለዋል
Filed in: Amharic