>

እነ ቄስ ሞገሴ  አሁንስ ምን ይሉን ይሆን? (አቻምየለህ ታምሩ)

እነ ቄስ ሞገሴ  አሁንስ ምን ይሉን ይሆን? 
አቻምየለህ ታምሩ
ዘንድሮ ያላየነው ነገር የለም። የመንግስት አክቲቪስት አይተናል፤  በአለም ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ  የመንግሥት ደጋፊ ለመሆን በብርሀኑ ነጋ የሚመራ ፓርቲም ተመስርቶ ተመልክተናል። ፋሽስት ወያኔ ቀለብ ይሰፍርላቸው የነበሩትና ታማኝ ተቃዋሚ ይባሉ የነበሩት  እነ አየለ ጫሚሶ ብርሀኑ ነጋ ከሚመራው ኢዜማ የተሻሉ ተቃዋሚዎች ነበሩ። በእውነቱ ኢዜማ  በመንግሥት ደጋፊነቱ የአየለ ጫሚሶን ፓርቲ አስንቋል። መንግሥትን ለመደገድ ፓርቲ ያቋቋሙት እነ ብሬ ግን ምርጫ ተብዮው ሲመጣ የመንግሥት ደጋፊ ሆነው  እንዴት አድርገው  ምረጡ ብለው ይቀሰቅሱ ይሆን? ሕዝቡስ የሚመርጠው ከሆነ ዋናውን  መንግሥት ትቶ  የመንግሥት ደጋፊዎች እነ ብርሀኑ ነጋን ለምንድን ነው የሚመርጠው?
የሆነው ሆኖ እነ ቄስ ሞገሴ የዜግነት ፖለቲካ አራማጅና ከዘር ፖለቲካ ወደጸዳ ምሕዳር የሚያሻግር እያሉ ሲዘምሩለት የነበረው ዐቢይ አሕመድ ለአርባ ዓመታት የተሰበከው ዘረኛነት አልበቃ ብሎ ለኦሮሞ ወጣት  በየመንደሩ ለሁለት ቀን የሚቆይ የዘረኛነት ኮርስ ሊሰጥ  መሆኑንና  መርኀ ግብር መውጣቱን  በአገዛዙ ልሳኖች ነግሮናል።
እነ ቄስ ሞገሴ በዐቢይ መሪነት ወደ ዜግነት ፖለቲካ ሊሻግሩን  ኢዜማ የሚል የመንግሥት ደጋፊ  የዜግነት ፖለቲካ አራምዳለሁ የሚል  ማኅበር  ቢመሰርቱም ተስፋ የጣሉበት  ሙሴያቸው ግን መንገድ ላይ ጥሏቸው የዜግነት ፖለቲካን ባፍ ጢሙ ደፍቶ የኦሮሞ  ወጣት  የዜግነት ፖለቲካ  በደረሰበት እንዳይደርስ ሊያስተምር የዘረኛነት ኮርስ ቀርጾ ሊያስተምር ወደ መንደሩ ወረደ።
ዐቢይ የዘረኛነት ኮርስ ቀርጾ ሊያስተምር ወደ ሰገባው ሲገባ ዐቢይን ለመደገፍ የተቋቋመው የኢዜማ እጣ ፈንታ ምን ሊሆን ነው? 🙂  ነው እነ ቄስ ሞገሴ እንዲህ  በየመንደሩ የዘረኛነት ኮርስ ሊሰጥ መርኀ ግብር መያዙን እንደኛ በዜና ሲሰሙ  ሳያፍሩ አሁንም ዐቢይን  አሁንም ወደ ዜግነት ፖለቲካ የሚያሻግረን ሙሴ ነው ሊሉን ነው? አሁንም የተለመደ ዜማቸውን ይዘው «ለውጡን እንዳይደናቀፍ ዝም በሉ» ይሉን ይሆን?
Filed in: Amharic