>

በኢትዮጵያ የሚገኘው የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ አሣሣቢ ደረጃ ላይ ደርሷል - ኢሰመጉ

ኢሰመጉ በኢትዮጵያ የሚገኘው የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ አሣሣቢ ደረጃ ላይ ደርሷል አለ!!!
ኢሰመጉ
 
የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ‹ሰብዓዊ መብቶች አያያዝን ለማሻሻል ተጀምሮ የነበረው ተስፋ ሰጪ እርምጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሲሸረሸር ቆይቶ፣ ሁኔታው አሁን አሣሣቢ ደረጃ ደርሷል› ብሏል፡፡
 
በመግለጫው ዜጎች በፈለጉበት የሃገራቸው አካባቢ ኑሯቸውን የመመስረት እና በሰላም የመምራት መብታቸውን ከፍተኛ ችግር ውስጥ የከተቱ ድርጊቶች መከሰታቸውና በአጠቃላይ በሀገሪቱ ወደ ሦሥት ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸውን አስታውቋል፡፡
 
ኢሰመጉ ለእዚህ በማሳያነት በተለያዩ አካባቢዎች ማንነትን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች፣ በቡድን የተደራጁ እና የታጠቁ ሃይሎች የሰላማዊ ዜጎች ህይወትን የቀጠፉና የሌሎችን የመሰብሰብና ሃሳብን የመግለፅ መብት የተገዳደሩ ድርጊቶች የነበሩ መሆናቸውን አቅርቧል፡፡
 
ድርጅቱ በዚሁ መግለጫው እጅግ አሣሣቢ ያላቸውን አራት ሁኔታዎችንም ዘርዝሯል፡፡ ኢሰመጉ ሰኔ15፣ 2011 ዓ.ም በባህርዳር እና በአዲስ አበባ የተፈፀሙትን ዘግናኝ ግድያዎች እና በመንግስት እየተወሰዱ ያሉ ተከታታይ እርምጃዎች፤ ፣ የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ፣ የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ፤ እንዲሁም የገዢው ፓርቲ አባል ድርጅቶች መግለጫዎችን በተመለከተ ስጋቶች እንዳሉት አስታውቋል፡፡
 
ሰኔ 15፣ 2011 ዓ.ም የሀገር መከላከያ እና የአማራ ክልል አመራሮች ላይ በተፈፀመው ጥቃት ድርጊቱን አቀነባብረዋል ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦችን  መጠነ ሰፊ  በመሆነ መልኩ የሚፈጸመው እስራት ‹የጭቆና እና አፈና ስርዓትን በሚያስታውስ መልኩ› መሆኑ ኢሰመጉ እንዳሳሰበው ነው የገለጸው፡፡
 
ይህም በአማራዊ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ በኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ በኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) እና በአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት በመባል በሚታወቀው ስብስብ አባላት እና ደጋፊዎች ላይ እንደተተገበረ በመግለጫው አትቷል፡፡
መንግስት ራሱ ተቃውሞን ለማፈን ይጠቀምበት እንደነበረ የገለፀውን የፀረ ሽብር ህግ፣ የጠቅላይ አቃቤ ህግ አዋጁን ለማሻሻል በሂደት ባለበት ወቅት በእዚህ ህግ መሰረት ታሳሪዎቹ ላይ ምርመራ መጀመሩ፣ ድርጅቱ  ለውጡ ወዴት እያመራ አንደሆነ ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ ነው ብሏል፡፡
 
ሌላኛው በመግለጫው ላይ አሣሣቢ የተባለው ጉዳይ የኢንተርኔት አገልግሎትን መቋረጥ ነው፡፡
የኢንተርኔት አገልግሎት ሐሳብን ከመግለፅ መብት ጋር እጅጉኑ የተቆራኘ እንደሆነ ኢሰመጉ በመግለጫው አንስቶ በዘፈቀደ ይህንን አገልግሎት መዝጋት ተቀባይነት የለውም ሲል ተቃውሟል፡፡
 
በሦሥተኝነት በመግለጫው ላይ አሣሣቢ የተባለው የሲዳማ  የክልልነት ጥያቄ ነው፡፡ በሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ዙሪያ ጥያቄውን በሚያስተባብሩ አካላት እየተሰጡ ያሉ ተደጋጋሚ መግለጫዎች እና ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች  ውጥረቱን ወደ ፀጥታ ስጋት ከፍ አድርገውታል ሲል ኢሰመጉ አስታውቋል፡፡ ይህንን የፀጥታ ስጋት መንግስት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ጥያቄውን የሚያስተባብሩ አካላት እና ምሁራን በጋራ በመሆን መፍትሄ እንዲፈልጉ አሳስቧል፡፡
 
በመግለጫው አሳሳቢ የተባለው ሌላው ጉዳይ  የገዢው ፓርቲ አባል ድርጅቶች የሚሰጡት መግለጫ ነው፡፡ ሰሞኑን ሕዝባዊ ወያኔ ኃርነት ትግራይ (ህወሃት) እና አማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(አዴፓ) ያወጡት ጠንከር ያለ ይዘት ያለው መግለጫ ወደ ግጭት እንዳይወስድ ኢሰመጉ አሳስቧል፡፡ ድርጅቶቹም በሰላማዊ እና በሰለጠነ መንገድ ልዩነቶቻቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ አሳስቧል፡፡
 
“ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ የሰላም እጦት ስጋት ውስጥ ነች” ያለው ኢሰመጉ ፣ መንግስት ይህ ችግር እንዲቀረፍ የሚመለከታቸው አካላትን ሁሉ ያሳተፈ መፍትሔ እንዲያፈላልግ ጠይቋል፡፡ የሰላም እና እርቅ እንዲሁም የማንነት እና የድንበር ኮሚሽኖች በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገቡም ኢሰመጉ ጠይቋል፡፡
 
የተፎካካሪ ፓርቲዎችም ሆኑ የሀሪቱ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ተቆርቋሪዎች ሁሉ ለሀገር ሠላምና አንድነት አዎንታዊ ሚና እንዲጫወቱ ኢሰመጉ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
አሻም ቲቪ
Filed in: Amharic