>
10:15 am - Wednesday December 7, 2022

የሰላሌው ፍሬ የኢትዮጵያው ሰማእት   የብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ያለህ !!! (ዘመድኩን በቀለ)

የሰላሌው ፍሬ የኢትዮጵያው ሰማእት  የብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ያለህ !!!
ዘመድኩን በቀለ
~ ኢትዮጵያ አሁን የምትገኝበትን ሁኔታ ከጳጳሳቱ አባቶቼ ይልቅ ለጄኔራል አሳምነው ጽጌ በገሃድ ተገልጦለት ነበር።
  “ በዘመናችን የቅዱስ ሲኖዶስ ስብስብ  ውስጥ እንዴት አንድ እንኳ ዳግማዊ አቡነ ጴጥሮስን ይጠፋል። እኔማ ከዛሬ ነገ አንድ ነገር ይላሉ ብዬ ጠብቄ ዝም ሲሉ ባይ ጊዜ እየተጨነቅኩ የግዴን ይሄን ጻፍኩ። ይፍቱኝ ይቅር ይበሉኝ።
•••
ለሲዳሞ ምህላ አያስፈልገውም አይደል? ሲኖዶሱ “ትግሬ” የተጠቃ ጉዳትም የደረሰበት በመሰለው ጊዜ ብቻ ነው አይደል ምህላ እንኳን ለማዘዝ ራዲዮፋናን የሚጠራው? ኦሮሞ እንኳ ባለፈው የሚያሸንፍ በመሰለ ጊዜ ምህላ የተደረገለት መሰለኝ። በእውነት ይሄ ፌር አይደለም። ያስተዛዝባልም። ክፋቱ እኮ እዚያ ሲዳሞም የሞቱት እነዚያ መሞት የማይሰለቻቸው፣ ቢሞቱ፣ ቢሞቱ የማያልቁ ዐማሮች መኖራቸው ነው። ጉራጌና ወላይታም ሞቷል። እግዚአብሔር ይመስገን ትግሬና ኦሮሞ አልተጎዱም። ቢሆንም ግን ዘመኑ የኦሮሞ ነው ብላችሁ ዝም ማለት አልነበረባችሁም። የምር እውነቴን እኮ ነው።
•••
በሲዳማ ካህናት፣ ምዕመናን መታረዳቸውን አልሰማችሁም ይሆን? አብያተ ክርስቲያናት መቃጠላቸውንስ አልሰማችሁ ይሆን? ያው መረጃ አይኖራችሁ ይሆናል። ደግሞም  አይፈረድባችሁም። እሳቱ መች አራት ኪሎ ቅድስት ሥላሴ ደረሰና ብላችሁ ነው የምትጨነቁት። ኧረ ምን ምንበወጣችሁ። በዚህ በዚህ እንኳ እስላሞቹ በጣም ያስቀናሉ። የሆነ ነገር ራሳቸውም ቢሆን ፈጥረው ሲያበቁ ተጯጩኸውም ቢሆን እምነታቸውን ያስከብራሉ። የእኛዎቹን ግን ጮጋ ማለት ይሻላል።
•••
ደሞዛችሁ ስንት ገባ ይሆን? ዘንድሮስ የደመወዝ ጭማሪ አግኝታችሁ ይሆን? አበሉስ ከፍ አለ? ወይስ እንደ አምናው ነው? ቤት መሥራት የጀመራችሁ አባቶቼ የቤት ሥራችሁን ጨረሳችሁ ? የሲሚንቶ ዋጋ፣ የብረትም የቆርቆሮና የፊኒሺንጉ ሥራ እንዴት አደረጋችሁ? ናላችሁን አዞረብኝ አይደል? ሰው ግን ገራሚ ነው በሙዳየ ምጽዋት ሳንቲም ተማምኖ እኔነኝ ያለ ቪላ ሲገነባ ግርም ነው የሚለኝ። በ8ተኛው ሺ ጳጳስና መነኩሴ ቤተ ሠሪ ይሆናል ያለው ማን ነበር?
•••
እስከ አሁን ስንት ዘመዶቻችሁን በየሀገረ ስብከታችሁ አስቀጠራችሁ? የሀገራችሁ ልጆችስ ቦታ ቦታ ያዙላችሁ? እሰይ እንኳን ደስ አላችሁ። ይሄም አንድ አስጨናቂ ነገር እኮ ነው። እሱንም መገላገሉስ ቀላል ነው እንዴ? እኔ የምለው የተሻለ ሀገረ ስብከት፣ ጮማ የሚቆረጥበት፣ ጠላ ጠጅ ወይኑ ከሚቀዳበት፣ ገንዘብ እንደ ቅጠል ከሚሸመጠጥበት ተመደባችሁ ወይስ ወንጌል የጠማው ገንዘብ የሌለው ምስኪን ነጫጭባ ደሃ ህዝብ ካለበት መድበው እዚያው አዲስ አበባ አስቀሯችሁ። ህክምናችሁስ ከምን ደረሰ? አሜሪካ ይሻላችኋል አውሮጳ?
•••
መኪኖቻችሁስ ተመቿችሁ? የ2018 ዓም ሞዴል V8 እኮ ብዙም አይመችም። እስቲ የ2019 አዲስ ሞዴል V8 ሞክሩት። በጀትም በቶሎ አስመድቡ። ቪ8 የ2019 ዓም ሞዴሉ ለአስፓልት ጉዞ እንዴት ያለ ሸጋ መኪና መሰላችሁ? እሱን አስገዙ። የመኖሪያ ቢሮአችሁ ምንጣፍስ ተቀይሮላችሁ ይሆን? ወንበሩስ? ሶፋውስ? አልጋችሁስ? ተቀየረላችሁ?
•••
አንድ የምነግራችሁ ነገር ቢኖር ግን አዲስ አበባ መደበቃችሁ ከዐቢይ አህመድ ሰይፍና፣ ከጃዋር መሃመድ ሜንጫ አይታደጋችሁም። የሦሪያ ጳጳሳትም እንደናንተው ነበር ያደረጋቸው። አክራሪው ኃይል ኤሌፖ የማይደርስ መስሏቸው ፈረጅያቸውን አንዘርፍፈው ሲዘናጉ አሸባሪው ቡድን ኤሌፖ ገብቶ የፊጥኝ እያሠረ እንደበግ አረዳቸው። ቀድማችሁ ያላዘጋጃችሁት ህዝብ ቄሮና እጀቶ አራት ኪሎ ደርሶ ቅድስተማርያም በራችሁን ሲያንኳኳ ደወል ብትደውሉ። እሪቋቀምበጭ ብትሉ ሰሚ እንደሌላችሁ ቁርጣችሁን እወቁ።
•••
ሲበዛ ግን ፈሪዎች ጨካኞችም ናችሁ ለማለት እደፍራለሁ። ንስሐ የሚያስገባኝ ከሆነም የልቤን ልናገርና ልዘጋጅበት። እንዴት አስቻላችሁ? ካህን ታርዶ፣ ቤተ ክርስቲያን ወድማ እንዴት እናንተን አስቻላችሁ? አንዲት መግለጫ እንኳን ለማውጣት ምነው ወኔ አጣችሁ? የእናንተስ ለጉድ ነው። በየትኛውም የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ታሪክ ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ ታሪክ ነው።
•••
ከምር ግን የምትበሉት እህል በጉሮሮአችሁ ይወርድላችሁ ይሆን? ደም ደም አይልባችሁም። ያውም የካህናት ደም፣ የምእመናን ደም፣ ደም ደም አይልባችሁም። ልጅ የላችሁ። ሚስት የላችሁ? ለምኑ ነው እንዲህ ዝግት ጥርቅም ማለታችሁ? ወይስ እናንተም የቤተ ክርስቲያንና የኦርቶዶክስ ማጥፋት ፕሮጀክቱ አካል ናችሁ?
•••
ደግሞ ይሄ እብድ ይሄን አለ ብላችሁ አኩሩፉኝ አሏችሁ። ተቀየሙኝ አሏችሁ። ኧረ እናውግዘውም የሚል አይጠፋም። እኔ ግን እላለሁ ያው አንዳንዴ ወፈፍ ያደርገኝ የለ፣ ሽቅብ ሽቅብ ያንጠራራኝ የለ። ይሄ ደግሞ የሐረር ቆቱነቴ ያመጣብኝ ጣጣ ስለሆነ አትቀየሙኝ። እንዴት እንደምወዳችሁም ታውቃላችሁ።
•••
በሉ አባቶቼ ይመቻችሁ?  ሰላም ሁኑ። ይሄንንስ ማን አየበት? ለማንኛውም የሰላሌውን ጀግና ኢትዮጵያዊውን ሰማዕት የብፁዕ አቡነ ጴጥሮስን ተጋድሎ የሚያሳየውን አጭር ፊልም ጋብዤ ልሰናበታችሁ።
•••
ሻሎም !   ሰላም ! 
ሐምሌ 18/2011 ዓም 
ከራየን ወንዝ ዳር።
Filed in: Amharic