>

በቀጠሮ ለተፈጸመው ሰቆቃ ተጠያቂው ማን ነው? (ያሬድ ሀይለማርያም)

በቀጠሮ ለተፈጸመው ሰቆቃ ተጠያቂው ማን ነው?
ያሬድ ሀይለማርያም
ባሳለፍነው ሳምንት የሲዳማን የክልል ጥያቄ ተከትሎ በአዋሣ እና አዋሳኝ ወረዳዎች በንጹሃን ዜጎች ላይ ግድያ፣ ድብደባ፣ የአካል ማጉደል፣ ወከባ እና ንብረት ውድመት ተፈጽሟል። ለደረሰው ጥቃት  ተጠያቂው ማን ነው?
ይህ ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል በርካታ አመላካች ነገሮች ነበሩ።
+ አቶ ጃዋር የሲዳማ የክልል ጥያቄው በጉልበትም ቢሆን ምላሽ ያገኛል በሚል ከወር በፊት ያደረገው የአደባባይ ቅስቀሳ እና ማነሳሳት፣
+ ኢጆቴ የተባለው የሲዳማ ወጣቶች ቡድን የጊዜ ገደብ ሰጥቶ ጥያቄው ካልተመለሰ እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል ቀደም ብሎ ማስጠንቀቂያ መስጠቱ፣
+ ይህን ተከትሎም የአካባቢው ነዋሪዎች ጠቃት ሊፈጸምባቸው እንደሚችል በመስጋት መንግስት ጣልቃ እንዲገባ እና የጸጥታ ኃይሎችን ቀድሞ ወደ አካባቢው በመላክ አደጋውን እንዲከላከል ጥሪ ቢያቀርቡም አፋጣኝ ምላሽ ማጣታቸው፣
+ መከላከያ ሰራዊቱ አዋሳ ከተማ ሲገባ በተመሳሳይ ሌሎች በዙሪያው የሚገኙ ከተሞች ላይ ጥበቃ ባለመደረጉ እና ሌሎች ምክንያቶች ተደራርበው በአካባቢው የሚኖሩ በርካቶች የጥቃት ሰለባዎች ሆነዋል።፡
አንድ የተደራጀ ቡድን የሚያነሳውን የመብት ጥያቄ በጉልበት አስፈጽማለሁ ብሎ ሲዝት እና በተግባር ሲንቀሳቀስ በመንግስት በኩል ምን መደረግ ነበረበት?
በወንጀል አድራጎት የማነሳሳት ተግባር በሕግ እንደሚያስጠይቀው ሁሉ፤ መብታችሁን በጉልበትም ቢያን አስመልሱ ብሎ አንድ ሰው በአደባባይ ጥሪ ሲያደርግ እና ሲቀሰቅስ ዝም ይባላል ወይ?
አደጋ ይደርሳል ተብሎ በተገመተበት ስፍራ መንግስት ቀድሞ ደርሶ የጉዳቱን መጠን መቀነስ ባለመቻሉ ለተከሰተውስ የመብት ጥሰት ተጠያቂው ማን ነው?
ቀስቃሽ ወይን አነሳሺ፣ በቀጠሮ ጥቃት ሰንዛሪ እና የጥቃት ማስጠንቀቂያውን ችላ በማለት ለሕዝብ ጥበቃ ያላደረጉት የመንግስት አካላት በጣምራ ሊጠየቁ አይገባም ወይ?
Filed in: Amharic