አቻምየለህ ታምሩ
በአገራችን ኢትዮጵያ ምሁራንና የሃይማኖት አባቶች እንደሚባሉት የኅብረተሰባችን ክፍሎች ከየመጣው ጋር አሰላለፉን የሚያስተካከልና የመንፈስ ደካማ የሆነ የኅብረተሰብ ክፍለ ያለ አይመስለኝም። ጥሊያን በአድዋ ጦርነት ድባቅ ተመትቶ ሽንፈት ከመከናነቡ ወራት በፊት ሸዋን እንዲወጋና ኢትዮጵያን ቅኝ እንዲይዝ እነ ባልዴሴራን በመስቀል ባርከው አምባላጌ ድረስ የሸኙት የአክሱሙ ንቡረእድ ነበሩ። ከአርባ አመት በኋላም ፋሽስት ጥሊያንን ከበሮ እየመቱ ለመቀበል እንደ አቡነ አብርሀም አይነቱን የሃይማኖት አባቶችን የቀደመ አልነበረም። የኢትዮጵያ ጀግና አርበኞች የፋሽስት ሰራዊትን አዲስ አበባ አናስገባም ብለው እየተፋለሙ የሃይማኖት አባቶቻ ግን የፋሽስት ጥሊያንን አገዛዝ ተቀብለው ለጦር አዛዡ ለማርሻል ባዶግሊዮ በአክሱም ጽዮን ወረብ እየቀረቡለት ነበር።
በደርግ ዘመን ማተባቸውን በጣጥሰው፣ ጥምጣማቸውን አሽቀንጥረው ጥለው የራሺያን ቀይ ባንዲራ በማንሳቱ ረገድ ቀዳሚዎቹ የሃይማኖት አባቶች የሚባሉት ነበሩ። በፋሽስት ወያኔ ዘመንም የኢትዮጵያን የክብር ካባ አውልቀው የብሔር፣ ብሔረሰቦችን ዜማ ቀድሞ በማሰማት ረገድ የሃይማኖት አባቶች የሚባሉትን የቀደመ የለም። እንደ አቡነ ጴጥሮስና አቡነ ሚካኤል አይነት አርበኛ ሰማዕት ቢኖረንም አብዛኛው የሃይማኖት አባት ግን እንደ አቡነ አብርሃም [ለጥሊያን የገቡት]፣ አቡነ ጳውሎስና አቡነ ማቲያስ ኢትዮጵያን በመፈሳዊነት ያከሰረ ካድሬ ነው።
በትናንትናው እለት በሲዳማ ዞን የደረሰውን ሕገ መንግሥት ወለድ ፍጅትና የንብረት ውድመት የአገረ ስብከቱ ጳጳስ የሃይማኖት አባቶችን ሰብስበው በዞኑ የሚገኙ አማኞች በሙሉ እንደየ ዕምነታቸው ለሳምንት የሚዘልቅ ጾም፣ ጸሎትና ምሕላ እንዲያደርጉ ማወጃቸውን የሀገረ ስብከቱ ቃል አቀባይ በጀርመን ድምጽ ራዲዮ ሲናገሩ ሰምተናል። ይገርማል! ዐቢይ አሕመድቃለ መሀላ የፈጸመበት ሕገ መንግሥት ተብዮው የቅሚያና ግድያ ደንብ ለወለደው ፍጅት፣ የዘር ጥቃት፣ መፈናቀልና የንብረት ውድመት ካድሬዎቹ ምዕመኑ ለሳምንት የሚዘልቅ ጾም ፣ጸሎትና ምሕላ ማዘዛቸው ከአፍንጫቸውና ከሆዳቸው አርቀው ማሰብ የማይችሉ፣ የሞራልና የመንፈሳዊነት ደረጃቸው የወረደ የህሊና በሽታ ተጠቂነታቸውን ብቻ ነው የሚያሳየው።
ሕገ መንግሥት ተብዮው የፋሽስት ወያኔና የናዚ ኦነግ የአፓርታይድ፣ የዘር ማጥፊያ፣ የቅሚያና የግድያ ደንብ በኢትዮጵያ ምድር በርግዶ የከፈተው የሲኦል በር አምላክን፣ መላእክትንና ሰማዕታትን ለመማፀን ለሳምንት የሚዘልቅ ጾም ፣ ጸሎትና ምሕላ በማወጅ ሊዘጋ አይችልም። ዐቢይ አሕመድ ቃለ መሀላ የፈጸመበት ሕገ መንግሥት ተብዮ ለፈጠረው ግድያና መፈናቀል በሱ ጉያ ስር ሆኖ እሱ ቃለ መሀላ የፈጸመበት ሕገ መንግሥት ተብዮው ለወለደው ግድያና መፈናቀል ሌላውን ጾም ፣ ጸሎትና ምሕላ እንዲያደርግ ማወጁ በመንፈሳዊነት በከሰረችዋ አገራችን ቤተ እምነቶች ውስጥ ከየመጣው ጋር አሰላለፋቸውን የሚያስተካክሉት የሃይማኖት አባት ተብዮዎቹ ምዕመኑን ምን ያልህ እንደሚንቁትና አታስቡም ደንቆሮ ናችሁ ብለው እንደሚሰድቡት ብቻ ነው የሚያሳየው።
በየቦታው የሚካሄደው ፍጅት፣ ሕዝብ ማፈናቀል፣ ግድያና ዝርፊያ ሕገ መንግሥት ተብዮው በኢትዮጵያውያን መካከል የቆመውን የጥላቻ ግንብ የወለደው ነው። የኢትዮጵያውያንን ፍጅት፣ መፈናቀልና የአገር ውስጥ ስደት አንድ አካባቢ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ባለቤትና መጤ፣ ሰፋሪና የአካባቢው ተወላጅ በማለት የመደበው ሕገ መንግሥት የወለደው ነው። ባጭሩ በየአካባቢው እየታየ ያለው የጎሳ ግጭት፣ ግድያና መፈናቀል ሕገ መንግሥታዊ መሰረት ያለውና ሕገ መንግሥት ተብዮው እየተተገበረ እንጂ እየተጣሰ አይደለም!
ጾም፣ ጸሎትና ምሕላ የሚሰምረው ስለእውነት እንጂ ስለ አጭበርባሪነት አይደለም። እኔ በማምነት ሃይማኖት ለጾም፣ ለጸሎትና ለምሕላ የልብ ንጽህና ያስፈልጋል። ልባችን ሕገ መንግሥት ተብዮው በለወለው ክፋትና ጥላቻ፣ ቂምና ምቀኝነት ተሞልቶ ንጽሕና ጎድሎች ሺሕ ጊዜ ጾም፣ ጸሎትና ምሕላ በአፋችን ብናደርግ የልባችንን የሚያውቅ አምላካችን የአፋችንን ጾም፣ ጸሎትና ምሕላ የሚሰማበት ጆሮ የለውም።
ስለዚህ ኢትዮጵያ የተዋቀረችበት ሕገ አራዊትና ርዕዮተ ዓለም እስካልተቀየረ ድረስ የጎሳ ግጭትና የእርስ በርስ መከሳከስ ሕጋዊ ነውና ሕገ መንግሥት ተብዮው የአፓርታይድ፣ የዘር ማጥፊያ፣ የቅሚያና የግድያ ደንብ ስር ሆናችሁ በጾም፣ በጸሎትና በምሕላ የጎሳ ግጭት፣ ግድያና መፈናቀል እናስቀራለን እያላችሁ በንጹሕ ልቦና ከእግዚያብሔር ጋር የምንገናኝበትን ጾም፣ ጸሎትና ምሕላ አታራክሱብን። ሕገ መንግሥት ተብዮው አገር አልባ ያደረገን ባላነሳ ለሚሰፈርላችሁ ቀለብ ስትሉ ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ የሆነ የውሸት ጾም፣ ጸሎትና ምሕላ እያወጃችሁ አገራችንን ጭራሹኑ የእርግማን ምድር አታድርጓት።