>

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ብሔራዊ የችግኝ ተከላ ቀን በተመለከተ ያስተላለፉት መልእክት

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሐምሌ 22 ቀን የሚደረገዉን ብሔራዊ የችግኝ ተከላ ቀን
በተመለከተ ያስተላለፉት መልእክት

ለብዙ ዘመናት ከኢትዮጵያ ሰማይ ስር ሲስተጋባ የኖረውና ‹ለምለሟ ሀገሬ› የሚለው ዕድሜ ጠገብ ዜማ የልጆቻቸን የዛሬ እውነታ የእኛ ደግሞ ከጆሯችን ሁሌም ያለ ቅርብ ትዝታ ነው፡፡

ትላንት እውነት እና ሐሴት የነበረው፤ ዛሬ ግን ምኩን እና ቁጭት ሆኖ የቀረው ዝማሬ በሁሉም ኢትዮጵያዊ ኅሊና ውስጥ አብዝቶ ይመላለሳል፡፡

እውነት ነው ሀገራችን ለምለም ነበረች- ዛሬ ግን አይደለችም፤ ምክንያቱም አባቶቻችን ያቆዩልንን እኛም በተራችን ለልጀቻችን አላቆየንም- እናም ልምላሜዋን እና አረንጓዴ ውበቷን ከትዝታ ብቻ አወዳጅተን አደራችንን በልተናል፡፡

ዜማዎቻችን ብቻ ሳይሆኑ ተረቶቻችንም ሀገራችን በደን የተሞላች እንደነበረች ይነግሩናል፡፡ በተረቶቻችን ውስጥ የምናገኛቸውን ብዙዎቹን እንስሳት ዛሬ በአካባቢያችን አናገኛቸውም፡፡

በየቋንቋችን ስማቸው ብቻ የቀረው የዛፍ ዓይነቶች ሀገራችን ዓይነተ ብዙ ደን እንደነበራት ቋሚ ምስክሮች ናቸው፡፡

የዛፎች ጉዳይ ለእኛ የውበት ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ የኅልውና ጉዳይ ነው፤ የእምነት ጉዳይ ነው፤ የባሕል ጉዳይ ነው፤ የኢኮኖሚ ጉዳይ ነው፤ ዛፍ ማለት እኛ ነን- እኛ ማለት ያለዛፍ ምንም ነን፡፡

የበረሃማነት መስፋፋትና የአየር ንብረት መዛባት ያስከተለው ቀውስ ሀገራችንን አደጋ ላይ ከመጣል አልፎ የስሟ መገለጫ እስከ መሆን ደርሷል፡፡

ባለፉት ዐርባ ዓመታት ብቻ እያሠለሰ የሚመታን ድርቅ በምግብ እህል ራሳችንን ለመቻል የምናደርገውን ትግል ተፈታትኖታል፤ ወገኖቻችንንም ከክብር ማማ አውርዶ የተረጅነት ወለል ላይ አስቀምጦብናል፡፡

የዝናብ ወቅቶቻችን እየተዛቡ፣ ለጎረቤት ይተርፉ የነበሩት ወንዞቻችን እየጎደሉ፤ ምንጮቻችን እየነጠፉ፤ ወይና ደጋው በረሃ፣ ደጋው ቆላ እየሆነ የኅልውና አደጋ ጋርጦብናል፡፡ ያራሳችንን ኅልውና በራሳችን ጥርስ ግጠነው- የነበረውን አፍርሰን እንዲያ ያልነበርን መስለናል፡፡

ከተሞቻችን በአንድ በኩል በኢንዱስትሪዎችና በተሸከርካሪዎች ጢስ ይበከላሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ዛፎቻቸውን ጨርሰው ከአንድ ፀሐይ ቢሆኑም የሦስት ፀሐይ ያህል በገረረ ንዳድ ተንቀልቅለው ኅያው በድኑን ያቃጥላሉ፡፡

ከተሞቻችን የከተማ መቃጠያ መሆናቸው ቀርቶ የከተማ መኖሪያ እንዲሆኑ ደናማ ከተሞች መሆን አለባቸው፡፡

ወገባችንን አሥረን የምንሠራቸው ግድቦች በደለል እየተሞሉና በውኃ እጥረት እየተመቱ ልፋታችንን መና እያስቀረነው ነው፡፡

እጃችንን በእጃችን እየበላን ጸጸት ቁጭታችን ብዙ ነው፡፡ ይህ ቁጭት እና መብሰክሰካችን የይቸላል ስሜታችንን አቀጣጥሎ ወደ አረንጓዴ ሰገነታችን በኃይል ካንደረደረን እሰየው፤ ቁጭት ብቻ ከሆነ ግን ዋይታችንን የማይቋጭ ያው ከንቱ ቁጭት ብቻ ነው፡፡

ሐይቆቻችን የነበራቸውን ቦታ እየለቀቁ፣ አንዳንዶቹ ከነባር ይዞታቸው ሲሸሹ ሌሎቹ ጨርሰው እየደረቁ ነው፡፡

ሐዘናችን መሪር ሆኗል፡፡ ለነ ሀረማያ ያፈሰስነው እንባ ገና ከጉንጫችን ሳይደርቅ የሌሎች ሐይቅ ጅረቶቻችንም ኅልውና ጉዳይም ለሌላ ሐዘን እያጨን ነጋችንን ጽልም አርጎታል፡፡

በዚህም የተነሣ በዓሣ ሀብታችን ላይ ፈተና እየተደቀነ ነው፡፡ በሐይቆቻችን ላይ ሠፍረው ይኖሩ የነበሩት አዕዋፍ ሀገር ጥለው እየኮበለሉ በሐይቆች ውስጥ የሚኖሩ እንስሳትም ዘራቸው እየተመናመነ ነው፡፡

እንባችንን ከዓይናችን ለመክላትና ዋይታችንን ወደ ዝማሬ ለመቀየር ማን ይምጣ? ለእኛ ሕመም እና ስቃይ ማሻሪያው እና ፈውሱም ያለው እኛው እጅ ነው፡፡
ዓለም ያደነቃቸው ታላላቅ ቤተ እምነቶቻችን የተሠሩት ከሀገር በቀል ዛፎች በተገኙ እንጨቶች ነበር፡፡

በውስጣቸው የምናገኛቸው ቅርሶችና ንዋያተ ቅዱሳት የተዘጋጁት ከኢትዮጵያውያን እንጨቶች ነበር፡፡

ሥዕሎቻችን፣ ቅርፆቻችንና የወግ ዕቃዎቻችን በሙሉ የደኖቻችን ውጤቶች ነበሩ፡፡
ቀደምቶቻችን የተጠበቡባቸው ዓምዶችና ወጋግራዎች፣ በሮችና መስኮቶች፣ ጣራዎችና አቴናዎች የደኖቻችን ትሩፋቶች ነበሩ፡፡

ትውፊታዊ ክዋኔዎቻችን ደኖቻችንን አበክረው ይፈልጓቸዋል፡፡ አረንጓዴው ዓለማችን የሁሉ ነገራችን አልፋ እና ኦሜጋ ነው፡፡

ሰርግ ሐዘናችን- ስግደት ሶላታችን- ልደት ሞታችን- አምልኮ ከበራችን ወግ እና ጨዋታችን እንኳን ከዛፍ- ደኖቻችን ጋር እጅጉን ተሰናስሏል፡፡ ሕይወታችን ከደኖቻችን ጋር የተያያዘ ነው፡፡

የደኖቻችን መመናመን በጎ ዕሴቶቻችን እንዲመናመኑ አድርጎብናል፡፡ ዕርቅ፣ ሸንጎ፣ ውይይት፣ ታሪክ ነገራ፣ በባሕላችን ውስጥ የሚከወኑት በዋርካዎቻችን ሥር ነው፡፡

በሁሉም ኢትዮጵያዊ ልብ እና ትውስታ ውስጥ አረንጓዴ ደኖቻችን የደግነት፣ የፍቅር፣ የሠላም፣ የሕይወት እና የተስፋ ውካዮች ናቸው፡፡ በገጠሬው ሕይወትና በከተሜው ትዝታ ውስጥ የሚገኙት የዱር ፍሬዎች የባሕላችን አካላት ነበሩ፡፡

ሌላው ቀርቶ ባሕላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎቻችን እንኳን የሚዘጋጁት ከደን ውጤቶቻችን ነው፡፡ በባሕላችን የአንድ ዋርካ መውደቅ የአንድ እንጨት መውደቅ ሳይሆን የአንድ ትልቅ ሰው፤ የአንድ ትልቅ ሽማግሌ መውደቅ ምልክት ነው፡፡

በሀገራችን ብዙ ወገኖቻችን ኑሯቸውን በደኖችና በደን ውጤቶች ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ የደን ፍሬዎችን ለቅመው፣ የደን ቅጠሎችን ሰብስበው፣ የደን ውጤቶችን ቆርጠው፣ የደን ውጤቶችን ወደ ልዩ ልዩ ዕቃዎች ቀይረው፣ በመሸጥ ኑሯቸውን የመሠረቱ ናቸው፡፡

የሀገሪቱ ዋነኛ የውጭ ምንዛሪ ምንጮች በአንድም በሌላም መንገድ ከደን ውጤቶቻችን ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡

ደኖቻችንና የዱር እንስሶቻችን የቱሪዝም ገቢያችን መሠረቶች፣ የዓይናችን ማረፊያ ጌጦች፣ የባሕል- ወግ እና እምነታችንም መከሰቻ ናቸው፡፡

እነዚህን ሁሉ ስንመለከት ነው የዛፍ ጉዳይ ለእኛ የቅንጦት ጉዳይ የማይሆነው፡፡ ከዚህ በፊትም እንደምለው ይህች ሀገር ከአባቶቻችን የወረስናት ብቻ ሳትሆን ከልጆቻችንም የተዋስናት መሆኗንም ማሰብ ተገቢ ነው፡፡

እኛም በተራችን ለልጆቻችን ስናስረከባት ከነበረሃዋ፣ ከነንዳዷ፣ ከነድርቋ እና ከነደለሏ እንዳይሆን የቤት ሥራችንን እንሠራ ዘንድ ይገባናል፡፡ ከልጆቻችን ነፍስ ላይ የነጠቅነውን በምቹ ሀገር የመኖር የኅልውና መሠረት ሳንውል ሳናድር ከመመለስ እና ከመተካት የሞራል፣ የእምነት እና የሰብዓዊነት ጽኑ ጥያቄ ጋር የተፋጠጥንበት ወቅት ላይ ደርሰናል፡፡

የሀገራችንን የደን ሽፋን እንዲያገግም ማድረግ ኅልውናችንን ማጽናት፣ እምነታችንን መጠበቅ፣ ባሕላችንን ማበልጸግ፣ ኢኮኖሚያችንን ማዳበር ነው፡፡
አራት ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ስንነሣ ለኅልውናችን፣ ለእምነታችን፣ ለባሕላችንና ለኢኮኖሚያችን ስንል ታጥቀን መነሣታችንም ጭምር ነው፡፡

ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምዕራብ ያሳየው ተነሳሽነት ይህን ዓላማ እንደተረዳው የሚያሳይ ነው፡፡

ይህንን ሀገራዊ ዓላማ ለማሳካት እስካሁን ባደረግነው አረንጓዴ አሻራን የማሳረፍ ርብርብ ቢልዮኖች ችግኞችን ተክለናል፡፡

ሰኞ ሐምሌ 22 ቀን በምናደርገው ብሔራዊ የችግኝ ተከላ ቀን 200 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ቀን በመትከል የዓለምን ክብረ ወሰን እንሰብረዋለን፡፡ የያዝነው ክረምት ከማለፉ በፊትም አራት ቢሊዮን ችግኞችን ተክለን ግባችንን እንመታለን፡፡

ይህን ስኬት ለማምጣት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና የክልል አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ በችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች የሚገኙ ሠራተኞች፣ የግብርና ባለሞያዎችና ምሁራን፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ ኮሜዲያን፣ የሚዲያ ኃላፊዎችና ጋዜጠኞች፣ ነጋዴዎችና ታላላቅ ኮርፖሬሽኖች፣ ወጣቶችና ሕጻናት፣ አጓጓዦችና የጉልበት ሠራተኞች ላደረጉት ምትክ የማይገኝለት አስተዋጽኦ በራሴና በኢፌዲሪ መንግሥት ስም ላመሠግን እወዳለሁ፡፡

ለአንድ አገር ጉዳይ፣ አንድ ሆነን በዓላማ ከተነሣን የሚሳነን ነገር እንደማይኖር የአረንጓዴ አሻራ ስኬታችን ምስክር ነው፡፡

ከደን የተራቆተችውን ሀገራችንን ለማልበስ እንደተነሳነው ሁሉ ከሠላም ከፍቅርና ከይቅርታ እየተራቆተች የመጣችውን ሀገራችንንም አንድ ሆነን ማልበስ አለብን፡፡

አራት ቢሊዮን ዛፍ በአንድ ክረምት መትከል ከቻልን አራቱን አስፈላጊ ሀገራዊ ዕሴቶችን፡- ሠላምን፣ ይቅርታን፣ ፍቅርንና አንድነትን መትከልና ማሳደግ አያቅተንም፤ በፍጹም፡፡

በቀሪው ጊዜ የተከልናቸውን ችግኞች በመጠበቅ፣ በመንከባከብና ለፍሬ በማብቃት መትከል ብቻ ሳይሆን ማሳደግም እንደምንችል እናሳይ፡፡

ዛፍ ብሔር፣ ቋንቋ፣ እምነትና ርዕዮተ ዓለም የለውም፡፡ ሁሉም ዛፍ የሁላችንም ነው፡፡ የሠራነው ሥራም ከእነዚህ ሁሉ በላይ ነው፡፡

ክብካቤና ጥበቃውም እነዚህን ልዩነቶች ሁሉ አልፎ ሊደረግ የሚገባው ነው፡፡
ሐምሌ 22 ቀን ሁላችንም ማልደን በመውጣት፣ ችግኞችንም በተገቢ መንገድ በመትከል፣ አረንጓዴ አሻራችንን እናሳርፍ፡፡ ነገንም ዛሬ እንትከል፡፡

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ፣ ተከብራና በልጽጋ ለዘላለም ትኑር!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!

ሐምሌ 19 ቀን 2011 ዓ.ም

Filed in: Amharic