>

በወሬና በፎቶ ጋጋታ ሀገር አይመራም!.... (ዘመድኩን በቀለ) 

በወሬና በፎቶ ጋጋታ ሀገር አይመራም!
አቢቹ ሙት ልቀቅ – የምር ደክሞሃል!!!
  ዘመድኩን በቀለ 
ዛሬው ማስቀየሻ ፤ የ200 ሚልየን የችግኝ ቀደዳ በዚህ ተፈጽሟል። የነገውን ማምለጫ ደግሞ መድኃኔዓለም ይወቀው። 
•••
“ዳይ አዳሜ ወደ አሁን በሥነ ሥርዓት ወደ ቁዘማህ ተመለስ። ወደ ዘይት፣ ወደ ዳቦ፣ ስኳር፣ ስንዴና ታክሲ ሰልፍህ ተመለስ። ለዛሬ አራዳው አቢቹ የፈለሰማት በችግኝ ተከላም ሰበብ አስተንፍሶሃል። አስቀይሶሃልም። ከነገ ጀምሮ ግን ያው እንደተለመደው ኑሮው ራሱ አናት አናትህን እያቀጠቀጠ ልክ ያገባሃል መስመርም ያስዪዝሃልና በጊዜ ወደ ማንነትህ ተመለስ።
•••
ወዳጄ ችግኝ መትከሉ እኮ ጥሩ ነው። የሚደገፍም የሚበረታታም ነው። ነገር ግን ችግኝ ተከላው ማስቀየሻ መሆኗ ነው። ፎለቲካ መሆኗ ነው። ውጥረት ማስተንፈሻ መሆኗ ነው። እሱ እኮ ነው ዋናው ችግር። ያዘጋጀኸውና የጠራ ሀገር የምትመራበት የእድገትና የብልጽግና ፎሊሲ ከሌለህ እንዲህ ነው የሚያደርግህ። አንዴ ችግኝ አንዴ ጠረጋ ያስወጣሃል።
•••
አቢቹ መለስ ያሳደገው የመሌ ልጅ ነው። መሌ ነፍሴ(ነአ) 99.6 % የፓርላማ  ምርጫ አሸነፍኩ ባለ ማግስት ሀገር ምድሩ እግዚኦ ቅጥፈት ሊለው ሲያኮቦኩብ አራዳው ሆዬ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ብሎ አዳሜን አፉን እንዳስያዘ አቢቹ አሳምሮ ያውቃል። እንደዚያ መሆኑ ነው የአቢቹም አካሄድ። ወዳጄ ችግኝ መትከል ጥሩ ነው። ችግኝ መትከል መልካም ነው አይነቀፍምም። ነገር ግን ደግሞ በችግኝ ተከላ ሰበብ የሌለ ጨለሌ አራዳም መሆን በጣም በጣም ይደብራል።
•••
የብሔራዊ ምርጫ ውጤት ለማወቅ፣ ለማሳወቅ አንድወር የሚፈጅባት ኢትዮጵያ፣ ለገጣፎ የፈረሰ የሺዎችን ቤት አዲስ አበባ ተቀምጦ የማይሰማው ኢቲቪና አቢቹ የአላባ ጠምባሮ የከለሌ ማኅበረሰብ 55 ሺ ችግኝ ተከሉ ይልልሃል። ከለሌ ግን የት ነው ብሎ መጠየቅ ለውጥ እንደማደናቀፍ ይቆጠራል። አይ ከለሌ። ሰዎቹ ኢትዮጵያን ልክ አውሮጳ ወይም አሜሪካ ያለች ኔትወርካም ሀገር አስመሰሏት እኮ። በምን ቴክኖሎጂ ቆጥረውት ነው በመንፈስ ይቆጥሩት ይመስል እስከ 6 ሰዓት ድረስ መቶ ሚልየን ችግኝ ተተከለ ብለው ሆዳችንን የሚነፉን። እስከ 12 ሰዓት 200 ሚልየን አለፈ እያለ ጨፍኑ ላሞኛችሁ ሲል ይደብራል። 10 ሺም ዛፍ ቢተከል እኮ ያስጨበጭባል። ያስመሰግናል እንጂ አያስወቅስም። 200 ሚልየን ግን አይነፋም። ኧረ ንካው።
•••
አዳሜ ደግሞ አይጠይቅም። አይሞግትም። የሰጡትን ሳያላምጥ መዋጥ ልማዱ አድርጎታል። እናም ልክ እንደ አህያማ ዝም ብዬ አልጫንም። ስነግርህ። አልጫንም።
•••
እጠይቃለሁ። ችግኞቹ መቼ ተባዙ? ማን ቆጠራቸው? በየትኛው በጀት? በክልሎች ወይስ በፌደራል መንግሥቱ በጀት? ስንት ሠራተኞች በችግኝ ማፍላቱ ላይ ተሳተፉ? ዛሬን ጨምሮ ለዚህ ፕሮጀክት ተብሎ የወጣውን ወጪ ማን ሸፈነው? በፓርላማ የጸደቀ በጀት ነው ወይ? ወይስ እስራኤል ዳንሳና ኢዩ ጩፋ ከዮናታን ጋር ሆነው በጀቱን እንደ ሙሴ መና ከሰማይ አዘነቡት? ኧረ ቀስ የቀደዳም ዓይነትና መጠን አለው። ኧረ ተዉ ፓስተሮችዬ።
•••
ሲደክምህ ያስታውቃል። ስታወራ ከርመህ አፍህ ሲደርቅ፣ ምራቅ መዋጥ ሲያቅትህም ያስታውቃል። ሰበካ ዳቦ አይሆንም። ሰበካ የቤት ኪራይ አይከፍልልህም። የአቢቹ ዲስኩር የሽንኩርት ዋጋ፣ የዳቦ ዋጋ አይቀንስልህም። ዐብይዬ የኔ ቆንጆ አፈር ስብላልህ ስላልከው አፈር መብላቱ እንደሁ አይቀርልህም።
•••
እንግዲያው ባትሰሙንም እንደ አቅሚቲ እንምከር። አቢቹ ሰበካህን ጨርሰሃልና እንደተከበርክ ሀገር መምራት ለሚችሉ ኢትዮጵያውያን በቶሎ አስረክብ። እንደ ህወሃት ሌባ!
እንደ ብአዴን በድን!
እንደ ኦህዴድ ኦነግ ፀረ ኢትዮጵያ!
 እንደ ደኢህዴን እንቅልፋም!
እንደ ኢዜማ ሰዎች ሥልጣን ይወድቅልኛል ብለው የበሬ ጭራ ከኋላ ከሚከተሉ ናፋቂዎች የሆኑ ዜጎች ሳይሆን የኢትዮጵያ ጉዳይ ግድ የሚላቸውን ሰዎች ከየትም ፈልገህ አስፈልገህ አሰባስበህም ሀገሪቷን በአፍጢሟ ከመድፋትህ በፊት ለተሻለ ሰው አስረክብ። ወሬና ፎቶ ሀገር አይመራም። በኋላ ትቆጭበታለህ። የልጅ ነገር አንዱ ብስል አንዱ ጥሬ ሆነህ ኋላ እንዳትዋረድ።
•••
የኢትዮጵያ ችግር የኩሽና የጓዳ ውስጥ ችግር ይመስል 50% ሴት ሚኒስትሮችን ስለመረጥክ ችግሯ አይፈታም። ኦሮሞና ዐማራን፣ ዐማራና ትግሬን፣ አፋርና ሱማሌን፣ ሱማሌንና ኦሮሞን ሳታስታርቅ ዘለህ ደቡብ ሱዳን ከሰሜን ሱዳን፣ ሶማሊያን ከጅቡቲ በግድ በጌታ ስም ታረቁልኝ ብለህ ደረታቸው ላይ ተለጥፈህ ፎቶ ስለተነሳህ የኢትዮጵያ ችግር አይፈታም። በእነ ዲ.ን ዳኒ ተጽፎ በሚሰጥህ የጥምቀትና የልደት ቃለ ምዕዳን የሚታለል ህዝብ የለም። እናም አቢቹዬ በጊዜ አምልጥ።
•••
ኢትዮጵያዊ ለሆኑ አካላት በቶሎ መንበሩን በጊዜም አስረክብ። ሱማሌ ይሁን ዐማራ፣ ኦሮሞ ይሁን ትግሬ፣ አፋር ይሁን ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል፣ ጉራጌ ይሁን ወላይታ ብቻ ኢትዮጵያዊ ለሆነ ቡድን አስረክብ። አደራህን ለአውሬው ኢዜማ ብቻ አሳልፈህ እንዳትሰጠን። ለአዲስ ፊት፣ ለአዲስ አዋቂዎች ለእነሱ አስረክባት ኢትዮጵያን። አደራህን ጧ ብላ ከመፈንዷቷ በፊት በቶሎ አስረክባት።
•••
ዛሬ ወላይታ ላይ የጨፈረልህ ህዝብ ወዶህ አይምሰልህ። ከዓመት በፊት ዐማሮችም እንዲሁ ሆነውልህ ነበር። ወላይታም ክልል እንሆን እንደሁ ብለው ነው እወቅ። እንዳትሸወድ። የአንተ ችግር የጫበጨበልህ ሁሉ የደገፈህ፣ የወደደህ መስሎህ መኮፈስህ ነው። ስንት አለ መሰለህ እየሳመ የሚነክስህ፣ ጥርሱን እያሳየ ይድፋህ የሚልህ። እናም በጫጫታ አትሸወድ። ይሄ ሁሉ ህዝብ የሆሳዕና ህዝብ ነው። አርብ ብትፈልገው አንዱንም የዛሬ አጨብጫቢ ቀራንዮ ከመስቀልህ ስር አታገኘውም። ወለጋዎች ራሱ ስቀለው ስቀለው ነው የሚሉህ። ዐማራ ገሸሽ አርጎሃል። ትግሬ እንደሁ መሽረፍት ምናምን ካለህ ቆይቷል። አዲስ አበባም ኧረ አበዛኸው ብሎሃል። ሲዳማም በስጩ ብሎብሃል። እናም ራስህን መርምርና አቅም ላለው መርጠህ አንተ ዘወር በል። ከምር እውነቴን ነው። ቢመርም መፍትሄው ይሄው ነው።
•••
ችግኙ ግን በመድኃኔዓለም ቸርነት ከጸደቀ ሸጋ ነው። ለክትክታም፣ ለመከታም፣ ለምሰሶም፣ ለማገዶም ይሆናል። እሱ ሸጋ ነው።
•••
የዛሬው ማስቀየሻ በዚህ ተፈጽሟል። ሌላ ማስቀየሻ ፈጥረህ ከመፍረጥረጥህ በፊት በጊዜ አምልጥ። ወዳጄ አይነጋ መስሏት… የሚባል ተረት እኮ አለ። ኢንዴዢያ ነው።
•••
ሻሎም !   ሰላም !
ሐምሌ 22/2011 ዓም
ከራየን ወንዝ ዳር።
Filed in: Amharic