>

ምኒልክን አለማወቅ ይቻላል ....!?! (ሄኖክ ስዩም)

ምኒልክን አለማወቅ ይቻላል ….!?!
ሄኖክ ስዩም 
…. ግን! የመጀመሪያውን ባቡር፣ የቀደመውን መኪና፣ አንድ ብሎ የጀመረውን አስኳላ ማወቅ ምኒልክን ማወቅ ነው፡፡ ነጭና ጥቁር እኩል ነው ብሎ ማመን፣ ጥቁር ነጭን ድል እንዳደረገ መስማት፣ የመጀመሪያው ሆስፒታል ሪፈር ተጽፎ መምጣት ምኒልክን ማወቅ ነው፡፡
****
ሰሞኑን አንድ ሰው ምኒልክን አላውቅም አለ ተብሎ እዚሁ መንደር ከዚህም ከዚያም የሚባለውን አደመጥሁ፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባለች ከዛሬዋ ይልቅ በትናንትናዋ በምትመካ ሀገር – ምኒልክን አለማወቅ ብዙ አይገርምም፡፡ ምክንያቱን ታላቁ ንጉሥ ከታላላቅ ነገሮች ጀርባ አሉና፡፡
.
በምኒልክ ባቡር ተሳፍሮ መጥቶ የምኒልክ ሚስት የቆረቆሯት ከተማ የገባ ምኒልክን ባያውቅም አውቋቸዋል፡፡ ምኒልክ የትም ያሉ ኢትዮጵያዊ ንጉሥ ናቸው፡፡ ፖስታ ቤቱ በር ላይ የቆመ ሰው ፖስታና ኢትዮጵያ ማን አስተዋወቃቸው ብሎ ሲያሰላስል እየመረረው ከምኒልክ ይተዋወቃል፡፡
.
ጅማ ከተማ ቆሞ ጅሬን አሻግሮ የሚመለከት ሰው ሳይፈልግ በግድ አባ ጅፋርን ያስብና ከማይነጥላቸው ንጉሥ ጋር ያስተሳስራቸዋል፡፡ ያኔ ምኒልክን ለማሰብ ጤናማ አእምሮ ብቻውን በቂ ነው፡፡ ጅማን ልለፍ ያለ ቤኒሻንጉል ገብቶ አሶሳ ሲደርስም እንዲሁ ሼህ ሆጀሌን አስታውሶ ሊዘላቸው የማይችል ንጉሥ ፊቱ ድቅን ይላሉ፡፡ እኒያ ንጉሥ ምኒልክ ናቸው፡፡
.
ነቀምቴ ያለ ሰው የኩምሳ ሞሮዳን ቤተ መንግሥት እንደምን አላውቀውም ይላል፡፡ ከዚያ ቤተ መንግሥት መኳንንቶች ጀርባ ሸዋ የነበሩ የሀገር ንጉሥ ማስታወስ ደግሞ የአእምሮ ጤንነትን ብቻ ነው የሚጠይቀው፡፡
.
በየቀኑ ምኒልክ ሆስፒታል ሪፈር ሲባል የሚውል ታካሚ የሆስፒታሉን በር ጽሑፍ ማንበብ ባይሻ ካርዱ ላይ የሠፈረው ስም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሆስፒታል እየታከመ እንደሆነ ይነግረዋል፡፡ ያ ስም ምኒልክ ነው፡፡
.
ምኒልክን አለማወቅ ስምን የመርሳት ያክል መብት ነው፡፡ ስሙን የረሳ ሰው ስም የለውም ማለት አይደለም፡፡ ስሙን የረሳ ሰው ራሱን ከመርሳት ያለፈ
ሌላ በደል በማንም ላይ አልፈጸመም፡፡
.
ምኒልክን መርሳት ይቻላል፤ ዓለምን አታስታውሱኝ ማለት ግን ሞኝነት ነው፡፡ ዓለም ጥቁር ለነጻነቱ የከፈለውን የድል ታሪክ ከምኒልክ ስም ጋር አቆራኝቶ ይገልጸዋል፡፡ # አድዋ የትም ጥቁር ልብ ያለ የነጻነት ታሪክ ነው፤ እንደ ሃያ ዓመት የሀሰት ታሪካችን ምኒልክን ከአድዋ ነጥለን እንይ ብንል ዓለም በዓይናችን ጣልቃ ባይገባም በዓይኑ ደግሞ አያስገባንም፡፡
.
ምኒልክን ማወቅ ግድ አይደለም፡፡ በስልክ ሽቦ የመገናኘት ቴክኖሎጂን ያወቀ ኢትዮጵያ ያኔ ቀድመው ያስተዋወቁትን ንጉሥ እንዳወቀ ይቆጠራል፡፡ ምኒልክን ማወቅ ግዴታ አይደለም፤ ሆቴል ተቀምጦ ባላውቃቸው ላለ የመጀመሪያውን ሆቴል ሲያስታውስ ከመቅጽበት ተዋውቋቸዋል፡፡
.
ምኒልክን ማወቅ ግዴታ አይደለም፤ ምኒልክን አላውቃቸውም ብሎ ለዓለም ነግሮ ፊደል ቆጥሬያለሁ ማለት ግን ያስቅበታል፡፡ የመጀመሪያው አስኳላ መስራች ቀለም ለቆጠረ ዓለም ሁሉ እውቅ ንጉሥ ናቸውና፤
Filed in: Amharic