>

ኢ.ሶ.ዴ.ፓ - ኢ.ዜ.ማ ላይ "ስያሜዬን ተነጠቅኩ" በማለት ክስ መሰረት!!! (አጎናፍር ገዛኸኝ)

ኢ.ሶ.ዴ.ፓ – ኢ.ዜ.ማ ላይ “ስያሜዬን ተነጠቅኩ” በማለት ክስ መሰረት!!!

 

አጎናፍር ገዛኸኝ

 

አዲስ አበባ፡– የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲ /ኢሶዴፓ/ ስያሜ በኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) መወሰዱን የፓርቲው ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ገለፁ። የኢዜማ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ናትናዔል ፈለቀ በበኩላቸው የፓርቲያቸው ስያሜ ከማንም ፓርቲ ጋር እንደማይገናኝ ተናግረዋል።

ፕሮፌሰር በየነ ኢዜማ… የሚባለው ቡድን “ማ” የምትለዋን ፊደል ማህበራዊ ፍትህ ብሎ ይተረጉማል። ይህ ትርጓሜ ሶሻል ዴሞክራሲ ከሚለው የፓርቲያችን ስያሜ ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ ተቃውመናል፤ ቅሬታችንንም ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አቅርበናል ብለዋል።

ፕሮፌሰር በየነ ‹‹የኢዜማን ዝርዝር ፕሮግራም ባናውቅም ስያሜው ከእኛ ፓርቲ ጋር ተመሳሳይ ነው። በዚህም ህብረተሰቡን እያሳሳቱ ናቸው። በኢዜማ ውስጥ የተካተቱት እንደ ሰማያዊና ኢዴፓ የመሳሰሉ የፓርቲ አባላት የሊብራል አራማጆች ናቸው።

አሁን ሃሳብ አለቀባቸው መሰለኝ ማህበራዊ ፍትህ ይላሉ። የፓርቲዎች ማቋቋሚያ አዋጅ ተመሳሳይ ስያሜ ያላቸውን ፓርቲዎች ስለሚከለክል መጠሪያው እንዲከለከልልን ጥያቄ አቅርበናል›› ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ናትናዔል (ኢዜማ) የሚለው ስያሜ ከየትኛውም ፓርቲ ጋር ይመሳሰላል የሚል እምነት የለንም። እስካሁን ለፓርቲውም ሆነ ከምርጫ ቦርድ የቀረበ ቅሬታም ሆነ ሌላ አስተያየት የለም፤ ቅሬታ ያቀረበ ካለ በህጋዊ መንገድ ታይቶ ምላሽ እንሰጣለን ሲሉ ተናግረዋል።

አቶ ናትናዔል ‹‹ፓርቲያችን መሰረቱ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ማህበራዊ ፍትህ የሰፈነበት እንዲሆን ለመስራት የተመሰረተ ነው።ማህበራዊ ፍትህ አሰፍናለሁ ሲልም ሁሉንም የሶሻል ዴሞክራሲ ፍልስፍናና አይዲዮሎጂ ሙሉ ለሙሉ እንቀበላለን ማለት አይደለም። ሶሻል ዴሞክራት ነን አላልንም። ፓርቲያችን በአንድ አይዲሎጂ የተወሰነ አይደለም። ማህበራዊ ፍትህ እስከሰፈነ ድረስ ከተለያዩ አካላት አይዲዮሎጂ ልንወስድ እንችላለን›› ብለዋል።

ቅሬታው በምርጫ ቦርድም ይሁን ከማንኛውም ፓርቲ ከመጣ በመተዳደሪያ ደንባችን መሰረት የሚታይ ይሆናል ያሉት አቶ ናትናዔል፤ኢዜማ ህጋዊ ሰርተፍኬት ለማግኘት መረጃዎቹን አሟልቶ ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አቅርቦ መልስ እየተጠባበቀ በመሆኑ ጊዜውን ጠብቆ ምላሽ እንደሚሰጣቸው ገልጸዋል።

የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሙኒኬሽን አማካሪ ወይዘሪት ሶሊያና ሽመልስ የኢዜማ ፓርቲ ስያሜ ከኢሶዴፓ ፓርቲ ጋር ተመሳሳይ መሆኑን የሚገልፅ ተቃውሞ ለቦርዱ መቅረቡን አረጋግጠው፤ ስያሜው ተመሳሳይ ነው ወይስ አይደለም የሚለው በአዋጁ መሰረት ለፓርቲው የምስክር ወረቀት ሲሰጠው አብሮ ምላሽ እንደሚያገኝ፤ ለኢሶዴፓም የኸው እንደተገፀለት ተናግረዋል፡

Filed in: Amharic