>

በደቡብ አፍሪካ ከ600 በላይ ኢትዮጵያውያን ወደ እስር ቤት ተጋዙ!!! (D.W ዶቼ ዌሌ )

በደቡብ አፍሪካ ከ600 በላይ ኢትዮጵያውያን ወደ እስር ቤት ተጋዙ!!!
D.W ዶቼ ዌሌ 
…ሐበሻን በጠቅላላ የመኖሪያ ፈቃድህን፤ የስደተኛ ወረቀትህንም ብታሳይ አይሰሙህም “..ግባ ወደ እስር ቤት ነው!” ነው የሚሉህ!»
በደቡብ አፍሪካ ጆሐንስበርግ ከተማ የጸጥታ አስከባሪዎች እና በንግድ ላይ የተሰማሩ የውጭ አገር ዜጎች ከተጋጩ በኋላ ወደ 600 ኢትዮጵያውያን መታሰራቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገሩ። የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ተመሳስለው በተመረቱ ሸቀጦች እና ሕገ-ወጥ ንግድ ላይ ያነጣጠረ ያለው ዘመቻ ከተጀመረ በኋላ የኢትዮጵያውያን ንብረት መዘረፉን ሴቶች መደብደባቸውን የአይን እማኞች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያውያን በሚበዙበት ጂፒ የተባለ የጆሐንስበርግ ከተማ የንግድ አካባቢ ከትናንትናው ዕለት ጀምሮ ፖሊሶች በትንሹ 600 ኢትዮጵያውያን ማሰራቸውን ፍቅር ሳቀታ የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
«ትናንት ከአምስት ከስድስት ፖሊስ ጣቢያዎች የተውጣጡ ተልዕኮ [ኦፕሬሽን] አለን ብለው መጡ። እንደመጡ ማሰር የጀመሩት መንገድ ላይ የሚያዩትን ሐበሻ በጠቅላላ ነው። የመኖሪያ ፈቃድ ብታሳይም፤ የስደተኛ ወረቀትህንም ብታሲዝ አይቻልም፤ ግባ ወደ እስር ቤት ነው የሚሉት» ሲሉ የተናገሩት አቶ ፍቅር በትንሹ 600 ኢትዮጵያውያን መታሰራቸውን ተናግረዋል።
በጆሐንስበርግ ከተማ ጄፒ በተባለው አካባቢ የሚሰሩት አቶ ኪዳኔ ወልደየሱስ በበኩላቸው የደቡብ አፍሪካ ፖሊሶች ኢትዮጵያውያንን እየለዩ በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል። የደቡብ አፍሪካ ሶስት የቴሌቭዥን ጣቢያዎች 600 ሰዎች ታስረዋል የሚሉ ዘገባዎች መስራታቸውን እንደተመለከቱ የገለጹት አቶ ኪዳኔ «ሕዝቡ ከዚያ ይበልጣል ነው የሚባለው፤ እዚያ ስለነበርን ያየንው በቃ አፈሳ ነበር፤ ይኸ የማን ሱቅ ነው? በሕጋዊ መንገድ ይነግዳል? የሚባል ነገር የለም። ሁሉንም የኢትዮጵያውያን ሱቅ ለይቶ መስበር ነው» ሲሉ የታዘቡትን አስረድተዋል። ከታሰሩት መካከል ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸው ኢትዮጵያውያን እንደሚገኙበት አቶ ኪዳኔ ገልጸዋል። «እኔ አንድ አራት አምስት ሰዎች አውቃለሁ» ብለዋል።
አቶ ፍቅር ኢትዮጵያውያኑ «ጆን ፎስታ የሚባል ፖሊስ ጣቢያ ነው የታሰሩት። መጠየቅ አይቻልም። ከታሰሩ 24 ሰዓት ሞልቷል ነገር ግን ፍርድ ቤት አልቀረቡም» ሲሉ አክለዋል።
በትናንትናው ዕለት ጄፒ የተባለ በአካባቢ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የደቡብ አፍሪካ ፖሊሶች በተሽከርካሪ እና በሰለጠኑ ፈረሶች ቅኝት ሲያደርጉ የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ለዶይቼ ቬለ ደርሰዋል። የአገሪቱ የፖሊስ ሚኒስትር ብሔኪ ሴሌ በዘመቻው 1500 ገደማ ፖሊሶች መሰማራታቸውን ተናግረዋል።
ፖሊሶቹ በመደብሮች ባደረጉት ብርበራ አልባሳት እና ሸቀጦች እያወጡ ሲቆልሉም ታይቷል። «ከረቡዕ ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በንግድ ቦታ  ላይ ፖሊሶች ሕዝቡን ከበው ያዙት። ድብደባ ዘረፋ ተጀመረ። ሱቅ እየከፈቱ ሕጋዊ የሆነ ሱቅ መዝረፍ ተጀመረ።እስከ ለሊቱ ስድስት ሰዓት ድረስ እዚያው ነው ያደሩት። አሁንም ሱቁ አልተከፈተም፤ ሰው ባልተረጋጋ ሁኔታ ላይ ነው ያለው» ብለዋል።
አቶ ኪዳኔ ወልደየሱስ «ሕገ-ወጥ ሥራ እየሰራችሁ ነው በሚል ሰበብ አበሻ ላይ ብዙ እርምጃ ወስደው ሱቆች በመዝረፍ ላይ ናቸው» ሲሉ ተናግረዋል። በብርበራ ወቅት ሕገ-ወጥ ተብለው የተሰበሰቡ አልባሳት እና ሸቀጦችን ለመሸጥ ሞክረዋል የተባሉ ሰባት ፖሊሶች በቁጥጥር መዋላቸውን አይኦኤል የተባለ የደቡብ አፍሪካ ድረ-ገፅ ዘግቧል።
የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ተመሳስለው የተመረቱ ሸቀጦችን ከግብይቱ ለማስወገድ ከአንድ ሳምንት ገደማ በፊት ብርበራ ከጀመረ በኋላ ከነጋዴዎች ጋር ግጭት ውስጥ ገብቷል። የደቡብ አፍሪካ መገናኛ ብዙኃን ባለፈው ማክሰኞ በነጋዴዎች እና በፖሊሶች መካከል የተፈጠረውን ግጭት የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ለእይታ አብቅተዋል።
Filed in: Amharic