>
4:53 pm - Monday May 25, 5226

እንደ መኪኖቻችን ሞዴሎች አንለያይም፤ እንደ አነዳዳችን ተመሳሳይ ነን!!! (ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ) 

እንደ መኪኖቻችን ሞዴሎች አንለያይም፤ እንደ አነዳዳችን ተመሳሳይ ነን!!!
ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ
ኢትዮጵያውያን በየእለቱ ከምናከናውናቸው ተግባራት መካከል እንደመኪና አነዳዳችን ደህና አድርጎ የሚገልጸን የለም፤ በተለይ ‹‹ሰልጥነናል፤ ተምረናል›› የምንለውን ከተሜዎች፡፡
በአንድ ሀገር ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ባህርይ እንደሚኖሩነት አካባቢ (ይህ ከማህበረ-ባህላዊ ሁለንተናቸው ጋር ይያያዛል)፣ እንደትምህርት ደረጃቸው፣ እንዳሳለፉት የህይወት ገጠመኝ፣ . . . ወዘተ. ይለያያል፡፡ ሌላው ቀርቶ የሚነዱት መኪናና አነዳዳቸው የአሽከርካሪዎችን ማንነት ይመሰክራል፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ካልሆነ በስተቀረ፡፡ አውሮፓና አሜሪካ ዘመናዊ መኪና ማለት ዘመናዊ ሰው ማለት ነው፡፡ ዘመናዊ ሰው በከተማ የሚኖር ስለሆነ የከተማን የአኗኗር ስርአት ይከተላል፤ የከተማ አኗኗር ደግሞ ህግን አጥብቆ የሚያከብርና ትህትናን አርማው ያደረገ ነው፡፡ ሀገሬ ውስጥ ይህ አይሰራም፣ በአብዛኛው (ሙሉ ለሙሉ ለማለት በሚያስከጅል ሁኔታ) ዘመናዊ መኪና የሀብት እንጂ (በስራ ወይም በሌብነት ልታገኘው ትችላለህ) የስልጣኔ ወይም ዘመናዊነት ምልክት አይደለም፡፡ በተለይ ባለፉት ሀያ ሰባት አመታት ዘመናዊ መኪና የሙስናና አጭበርብሮ ገንዘብ የማግኘት መገለጫ ሆኗል፡፡ አውሮፓ አንድ ባለመኪና መንገድ ተሸጋሪ መሆንህን ካወቀ ዜብራ ላይ ጠብቆ ቆሞ ያሳልፍሀል፡፡ ሀገሬ ‹‹ዜብራ ነው›› ብለህ ተዝናንተህ አታቋርጥም፤ ላዳ ታክሲውና ሀመሩ ያለ ልዩነት ከመሀል ዜብራ በጡሩንባ አስደንብረው አባረውህ ይነዳሉ፡፡
.
ከሲግናል ወደ መገናኛ የሚሄደው መንገድና ከለም ሆቴል ወደ ሾላ ገበያ የሚሄደው መንገድ የሚቋረጡበት ቦታ ላይ ነው፤ አንድ ቅዳሜ ቀን አራት ሰአት ላይ፡፡ በአራቱም አቅጣጫ የሚመጡት መኪኖች እርስ በርስ ተቆላልፈው ቆመዋል፤ በዚያ ላይ የመኪኖቹ ጡሩንባ እራሱ ያበደ እንጂ ሰዎች የሚቆጣጠሩት ፈጽሞ አይመስልም፡፡ ከሀያ ደቂቃ ጥበቃ በኋላ ከመኪናዬ ወርጄ ወደ መስቀልያው መንገድ መሀል ገባሁ፡፡ መሀል ላይ በዋናነት መንገዱን የዘጉት ሁለት መኪናዎች ናቸው፡፡ አንድ ከሾላ ገበያ በኩል መጥቶ ወደ ለም ሆቴል የሚሄድ ሆዱንና ጀርባውን በተለያዩ የአትክልት አይነቶች የሞላ የተንጋደደ አሮጌ ውይይትና አንድ ከመገናኛ ወደ ሲግናል የሚሄድ ዘመናዊ ራቭ 4 መኪና፡፡ እነሱን ተከትለው በየአቅጣጫው በመቶዎች የሚቆጠሩ መኪኖች ተደርድረዋል፡፡ ከጀርባ ያሉት መኪኖች ካላፈገፈጉ መንቀሳቀስ አይቻልም፡፡ የሁለቱ መኪኖች ሹፌሮች መሀል ላይ ከመኪናቸው ወርደው ይሰዳደባሉ፡፡ አለባበሳቸው መኪናቸውን ይመስላል፡፡ ከመኪናቸው ቀጥሎ ጎልቶ የሚታየው ልዩነት አለባበሳቸው ነው፡፡ ተሳዳቢነታቸው ተመሳሳይ ቢሆንም፣ ስድባቸው ይለያያል፡፡ ባለ ዘመናዊ መኪናው ጭቃ እና ደደብ የበዛበት ስድብ ሰውየው ላይ ፣ ‹‹what a crazy morning›› ማለዳው ላይ ያርከፈክፋል፡፡ ባለ ውይይቱ፣‹‹ሰውየው አብዷል! ኧረ ባክህ! ቆይ ሰው ሰርቶ አይብላ ነው! መቼስ ከመስረቅ መስራት ሺ ጊዜ ይሻላል›› እያለ በምክር መስቀያ የተንጠለጠሉ ስድቦችን ይወረውራል፡፡
.
በጣም ገረመኝ! ሹፌሮቹ እንደ መኪናቸው አለመለያየታቸው ገረመኝ፡፡ ምን አልባት አውሮፓ ወይም አሜሪካ ኖሮ የመጣው፣ ምናልባትም የተማረው፣ ንጹህ ልብስ የለበሰው ሰው፣ ምናልባት ከጉራጌ ገጠር ከመጣው፣ ምናልባትም መደመርና መጻፍ ብቻ ከሚችለው ሰው ጋር የአስተሳሰብና የአሰራር ለውጥ አለማምጣቱ ገረመኝ፡፡ ባለራቩ የከተማን ህግ አክብሮ ትህትናን አርማው አድርጎ የሚኖር ስልጡን አይደለም፡፡ ከተማ ውስጥ ቢኖርም ከገጠር አልወጣም፡፡ ድሀው መኪናው የትም ልትቆምበት እንደምትችል፤ ያ ሲሆን አትክልቱ ገበያው ሳይደርስ የጸሀይ ሲሳይ ሊሆን እንደሚችል፤ ስለዚህም አነዳዱ ሰቀቀን እንጂ፣ እንደሱ መዝናናት እንዳልሆነ ሊያስብ አልቻለም፡፡ ቆሞ ስላላሳለፈው ቆሞ ይሰዳደባል፡፡ ይህ እኛን በደንብ የገልጸናል፤ ተማርን አልተማርን፣ በከተማ ኖርን በገጠር፣ በአለም ተሸከረከርን አገር ቤት ተዘግተን ኖርን፣ የአሰራርና የአስተሳሰብ ልዩነታችን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ የተማርነውና በየሰለጠነው፣ አለም የዞርነው ካልተማሩትና ብዙ ካላዩት የምንለየው በእውቀትና በመረጃ ብቻ ነው፤ መረጃውና እውቀቱ ደግሞ ለወሬ እና ለጉራ ካልሆነ የእለት ተእለት ድርጊታችን (አሰራሩ) ላይ ያመጣው ለውጥ የለምና ካልተማረው ጋር ልዩነት የለንም፡፡ ኢትዮጵያውያን ትምህርት ላይ ጎበዝ ነን፤ ሸምድደን እውቀትን መቋጠር ላይ፣ ተፈትነን ማለፍ ላይ የሚስተካከለን የለም፤ ግን የየእለት አሰራራችንን በዚያ እውቀት አንመራውም፡፡
.
የኢትዮጵያውያንን አቅል የነሳው እራስ ወዳድነት እንደአነዳዳችን የሚገልጸው የለም፡፡ ለዚህ ደግሞ በቀይ የትራፊክ መብራት ታግተው የተሰለፉ መኪኖችን መመልከት ይበቃል፡፡ ልክ አረንጓዴ ሲበራ ከኋላ የተሰለፉት መኪኖች ጡሩንባቸውን ያቀልጡታል፡፡ ሲጀመር መኪኖቹ ከፊት ያለው ሲሄድ ተራ በተራ አይደለም እንዴ የሚያልፉትና መንገድ የሚለቁት!? ጡሩንባው ምን ይጠበስ ነው!? ልክ አረንጓዴ እንደበራ አስራ አምስተኛው መኪና አስራ አራተኛው ላይ ጡርንባ የሚነፋው ምን እንዲሆን ነው? በአስማት ብን ብሎ እንዲጠፋ ነው? አብዛኞቱ የከተማ ነዋሪዎች እነዚህን ጥቃቅን ጥያቄዋች እንኳን እራሳቸውን ለመጠየቅ ወደር የለሽ እራስ መዳድነታቸው አይፈቅድላቸውም፡፡
እስቲ ትራፊክ በተጨናነቀበት ሰአት፣ ባለሶስት ረድፋ አስፋልት ላይ፣ በመካከለኛው መስመር ላይ እየነዳህ ከፊተኛው መኪና ቀረት ብለህ አንድ መኪና የሚያስገባ ክፍተት ፍጠር! ከግራና ከቀኝ መስመር ያሉት መኪኖች ያቺን ክፍተት ለመሙላት ፊትህ ካልተላተሙ እድለኛ ነህ፡፡ . . . ይህ ሁሉ የስብእናችን ነጸብራቅ ነው፤ እራስ ወዳዶች ነን፡፡ . . . . በደምሳሳው ኢትዮጵያውያንን ለማወቅ አስፋልት ወጥቶ አነዳዳችንን መቃኘት በቂ ነው የምለው ለዚህ ነው፡፡ በየጓዳው በገመና ከረጢት የታሸገውን፣ በመጠይቅ የማታገኘውን ጉድፍ ጎዳና ተሰጥቶ ታየዋለህ፡፡
Filed in: Amharic