>

ህዝቅኤል ጋቢሳ መቀሌ ቢጋበዝ ምን ይገርማል?!?" (አብርሀም በላይ)

ህዝቅኤል ጋቢሳ መቀሌ ቢጋበዝ ምን ይገርማል?!?”
አብርሀም በላይ
በቅርቡ ህዝቅኤል ጋቢሳ ቀጥሎም በቀለ ገርባ መቀሌ ተጋብዘው ነበር። ይህ ጉዳይ የገረማቸው ሰዎች አሉ። ምን ይገርማል? ተረሳ እንዴ? እስቲ ባጭሩ እናስታውስ –
የህወሃት አመራር ሁለት አይነት ስዎችን ያቀፈ ነበር። አንደኛው የገብሩ አስራት ቡድን (ትግራይ/ኢትዮጵያዊ) ሁለተኛው እና ዋናው የስልጣን ቁልፍ ያዢው የመለስ/ስብሃት (አገር የለሽ መርስነሪ) ቡድን። ኢትዮጵያዊው ቡድን ተመታ። መርስነሪዎቹ የኢትዮጵያ ጠላቶች ያቺ “ህወሃት” የምትል ካባ ለብሰው ኢትዮጵያን እየቀጠቀጡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ስልጣን ላይ ኖሩ።
ኢትዮጵያ ለኛ እናት ሀገራችን ነች፣ ለመርስነሪዎቹ ደግሞ እነሱ የሚቆጣጠርዋት ካሲኖ ነች፣ የቁማር ካሲኖ፣ የማትነጥፍ የገንዘብ ምንጭ። ኤፈርት ምንድነው እንዴ? ግዙፍ ካሲኖኮ ነው፣ የስብሃት ነጋ ካሲኖ! መቴክ ምን ነበር እንዴ? ኦዲት የማይደረግ የመርስነሪዎቹ ካሲኖ!
መርስነሪዎቹ አሁንም ከስልጣን ወርደውም በጣም የሚያስፈራቸው እና የሚያስደነግጣቸው ነገር ቢኖር የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነት የቆመ እንደሆን ነው። ያኔ ነው እንቅልፍ የሚያጡት! ያኔ ነው ከምር የሚቅበዘበዙት። ይህ ደግሞ እንዳው በአጭሩ በቅንጅት እና በኢትዮ-ኤርትራ ጊዜ ፈጦ ታይቷል። ይህ ባህሪያቸው ነው።
ለምሳሌ በቅንጅት ድል ዋዜማ እንደለመዱት የትግራይ ተወላጆችን ማስደንገጥና ከቅንጅት ካምፕ እንዲወጡ ማድረግ ነበረባቸው። ወድያው “ትግሬ ወደ መቀሌ፣ ዕቃ ወደ ቀበሌ” የሚል በቴዎድሮስ ሓጎስ የተፈበረከ አስደንጋጭ መልእክት እንደ እሳት ሰደድ ለቀቁበት። የትግራይ ተወላጅም እውነት መስሎት በርግጎ ህወሃት ጉያ ውስጥ ገብቶ ቀረ። ቀረ! ቀረ!
ቀደም ሲል በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነት ቆመ። እነ መለስ/በረከት እንቅልፍ አጡ። መላ ሲፈልጉ በተለይ የአማራው ህዝብ እንዲከፋ ለማድረግ በጦርነቱ መሃል ህዝቡ ይፈታሉ ብሎ፣ ተስፋ ሰንቆ ሲጠብቅ በ15 ከፍተኛ የመኢሕድ (መላው አማራ) አመራር አባላት ላይ ከ10 አመት በላይ እስራት ተፈርዶባቸው ወህኒ ተወረወሩ። ከፍተኛ ሀዘን ሰፈነ። መከፋፈል ተከሰተ። የሚያጠፋው ያጣው ቅጥረኛው የህወሃት አመራር ጊዜ ጠብቆ የኢትዮጵያ ህዝብ ልጆች የተሰውለትን ድል አራት ኪሎ ሆኖ አከሸፈው።
አሁንም መቀሌ መሽጎ ያለው የመለስ ዜናዊ ወራሽ መርስነሪ ቡድን መሆኑ ላፍታም መዘንጋት የለበትም። ያ ቡድን የኢትዮጵያ አንድነት የሚሰብኩ ኢትዮጵያውያንን ሊጋብዝ አይችለም። አጀንዳው አይደለም። የሚፈልገው “በሰላም መኖር ካልተቻለ አንቀጽ 39 ተጠቅመን እንበታተን” የሚሉ የድርጅት መሪዎችን ነው። እነ ህዝቅኤል ጋቢሳ መቀሌ ተጋብዘው ቢሄዱ ፈጽሞ አይገርምም። ሊገርም የሚችለው ህወሃቶች እስክንድር ነጋን ወይም ኤርሚያስ ለገሰን የጋበዙ እንደሆን ነበር”
Filed in: Amharic