>
10:38 am - Wednesday December 7, 2022

ራሱን  የረሳው በቀለ ገርባ  (አቻምየለህ ታምሩ)

ራሱን  የረሳው በቀለ ገርባ 
አቻምየለህ ታምሩ
በቀለ ገርባ የሚባለው ሰውዬ ከኦሮሞ በላይ ኦሮሞ ለመሆን የሚያደርገው መውተርተር ሁሌም ያስገርመኛል። ሰውዬው የበላበትን ወጭት ሰባሪና  የጎረሰበትን እጅ ነካሽ ስለሆነ  ከመቀሌ መልስ በጃዋር ቴሌቭዥን ቀርቦ በሰጠው ቃለ ምልልስ ኦሮሞ ያጠፋውን ማንነቱን ማስመለስ ባይቻላቸውም ከኦሮሞ  ባርነት ነጻ ያወጡትንና ዝቅ ብሎ ሊያመሰግናቸው የሚገባውን  የኢትዮጵያ  ነገሥታት በተለይም ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክን በእጅጉ ሲኮንን ሰማሁት። እንዴት አንድ ጤናማ የሆነ ሰው  ባሪያ ያደረጉትን ጌቶች መርጦ ከባርነት ነጻ ያወጡትን  ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክን ያወግዛል? ጤናማነትስ ነውስ?
ታሪኩን ለማታውቁ በቀለ ገርባ ልክ እንደ  ሐድያው ጁኔይዲ  ሳዶ ሁሉ ኦሮሞ ሳይሆን ኦሮሞ በወረራ ይዞ ባርያ ያደረገው ጰለታ ነው። ኦሮሞ ሲስፋፋ አስገብሮ ጭሰኛና ጭሰኛ ያደረጋቸውን ነባር ነገዶች ከመሬታቸው ከነቀለ በኋላ «ገርባ» ይላቸዋል። ገርባዎች የኦሮሞ  ጭሰኞች ናቸው። ገርባ የሚለው የኦሮምኛ ቃል የአማርኛ ፍቺው ባርያ ወይንም አገልጋይ ማለት ነው። የበቀለ አባት አቶ ገርባ ኦሮሞ ያስገበራቸው የምዕራብ ኢትዮጵያ ነባር ነገድ መሆን አለባቸው። አንድ ሰው ወዶ ለልጁ ባርያ ወይንም አገልጋይ የሚል ስም ሊያወጣ አይችልም። ጰለታ ማለት ኦሮሞ ገርባ ያደረገው ወይንም በሞጋሳና ሜዴቻ ማንነቱን ወደ ኦሮሞ የቀየረው ሰው ልጅ ማለት ነው። ባጭሩ በቀለ ገርባ ኦሮሞ ሳይሆን ኦሮሞ ባሪያ ካደረጋቸው ቤተሰቦች የተወለደና ኦሮሞ ማንነቱን ያጠፋበት ሰው ነው። ኦሮሞ ያስገበራቸው ነባር ነገዶች ገርባ እያለ እንደሚጠራቸውና ጭሰኛ አድርጓቸው እንደኖረ ማወቅ የሚሻ በኦሮሞ ታሪክ ጥናት ጥርሱን የነቀለው አሌክሳንድሮ ትሪውልዚ “Boorana and Gabaro among the Macha Oromo in Western Ethiopia” በሚል ያሳተመውን ድንቅ ምርምር ያንብብ።
ጰለታዎችና ገርባዎች የሆኑት የበቀለ ገርባ ዘሮች ከኦሮሞ ባርነት የተላቀቁት ዳግማዊ ዐጤ ምኒልክ ለደጃዝማች ጆቴ ቱሉ፣ለወንድማቸው ለደጃዝማች ቲባና ለደጃዝማች ቁምሳ ሞሮዳ በ1902 ዓ.ም.  ኦሮሞ ጰለታና ገርባ ያደረጋቸውን  ባሪያ እያሉ  እንዳይሸጡ ባወጡት ደንብ ነው። በነገራችን ላይ ደጃዝማች ቲባ ቱሉ የደጃዝማች ጆቴ ቱሉ ታናሽ ወንድም ሲሆኑ የኢማሌድኅ አባል የነበረው የወዝሊግ ሊቀ መንበር የነበረው የዶክተር ሰናይ ልኪ አያት ናቸው። የዶክተር ሰናይ ልኪ አባት ልኪ ቲባ ቲሉ ይባላሉ። ዶክተር ሲናይ ልኪን አሜሪካን ልከው ያስተማሩት  በንጉሡ ዘመን የወለጋ ጠቅላይ ግዛት እንደራሴና  የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት የነበሩት ዘመዱ ዶክተር ደጃዝማች ካሣ ወልደ ማርያም ደግሞ የደጃዝማች ቲባ ቱሉ ታላቅ ወንድም የደጃዝማች ጆቴ ቱሉ ሴት  ልጅ የአስካለ ጆቴ ልጅ ናቸው።
ደጃዝማች ጆቴ ቱሉ በዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ዘመን  ጊምቢን ዋና ከተማቸው አድርገው የዛሬውን ምዕራብ ወለጋን ሲገዙ ታናሽ ወንድማቸው ደጃዝማች ቲባ ቲሉ ደግሞ አሶሳን ማዕከላቸው  አድርገው ከአሶሳ እስከ ኦምዱርማን ድረስ የተዘረጋውን ትሪያንግል ይገዙ ነበር። የደጃዝማች ካሳ ወልደ ማርያም እናት ወይዘሮ አስካለ ጆቴ የልጅ እያሱ ባለቤት የነበሩ ሲሆን አባታቸው ደጃዝማች ጆቴ ቱሉ ልጃቸውን አስካለን ለልጅ ኢያሱ ሲድሩ ስምንት መቶ ጋሻ ቡና ጥሎሽ ለልጅ እያሱ ሰጥተው ነበር።
ልጅ ኢያሱ ፍቼ ራስ ካሳ ቤተ መንግሥት በታሰሩበት ወቅት ይጎበኟቸው ከነበሩ ሁለት የቀድሞ ሴት ወዳጆጃቸው መካከል ወይዘሮ አስካለ ጆቴ አንዷ ነበሩ። ፋንታሁን እንግዳ የተባሉ የታሪክ ተመራማሪ በ1997 ዓ.ም. «በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አስተዳደር ጎልተው የወጡ የፖለቲካ  ችግሮችና ትግሎት በቅርብ ባለሟሎች ሲገመገሙ» በሚል ባሳተሙት መጽሐፋቸው ወይዘሮ አስካለ ጆቴ ዶክተር ደጃዝማች ካሳ ወልደ ማርያምን ያረገዙት እስር ቤት ከነበሩት ከልጅ ኢያሱ እንደሆነና መልካቸውም ልጅ ኢያሱን እንደሚመስል እንዲሁም ወይዘሮ አስካለ ጆቴ  ዶክተር ደጃዝማች ካሳ  እንደ አባት የሚጠሩባቸውን ታላቁን አርበኛ ደጃዝማች ወልደ ማርያምን ያገቡት ዶክተር ደጃዝማች ካሳ ከተወለዱ በኋላ ነው የሚል የቤተ ዘመድ መረጃ እንዳለ ጽፈዋል።
ወደ ዋናው ጉዳይ ስለመለስ በቀለ ገርባ ቤተሰቦቹን ወርሮና መሬታቸውን ቀምቶ ጭሰኛ  ካደረጋቸው ኦሮሞ ነጻ እንዲወጡ ያደረጉትንና  አያቶችና ቅድመ አያቶቹን  ባርያ ሆነው ከመሸጥ ያዳኗቸውን ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክን ምን ያድርጉ ነው የሚላቸው?  ዳግማዊ ምኒልክኮ እነ ጆቴ፣ ቲባና ሞሮዳ ባሪያ፣ ገርባና  ጰለታ ያደረጓቸውን ነጻ ማውጣት ብቻ ሳይሆን እነዚህ ደጃዝማቾች ባሪያ አድርገው የሸጧቸውን የበቀለ ገርባን ዘሮች እስከ ደቡብ አፍሪካ ድረስ እየተላላኩ የሚከፈለውን በመክፈል ከባርነት ነጻ እንዲወጡና ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ያደረጉ አባት ናቸው!
ሳንድራ ሼል የሚባሉ ተመራማሪ  «From slavery to freedom : the Oromo slave children of Lovedale, prosopography and profiles» በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ. በ2013 ዓ.ም. ባሳተሙት መጽሐፍ የኦሮሞ ባላባቶች ባሪያ አድርገው የሸጧቸውን የምዕራብ ኢትዮጵያ  ነገዶች አባላት ዝርዝርና ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ደቡብ አፍሪካ ድረስ በመላላክ  ገንዘብ ጭምር እየከፈሉ ነጻ እንዲወጡና ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ስላደረጓቸው ገርባዎች፣ ጰለታዎችና ባሮች ይናገራል። ጥናቱ የኦሮሞ ባላባቶች ከወለጋ  ባሪያ አድርገው ወደ ደቡብ አፍሪካ የሸጧቸውን ሰዎችና ዳግማዊ ምኒልክ ገንዘብ እየከፈሉ ያስለቀቋቸውን ባሮች ትውልዶች ጭምር አካቷል።   በኦሮሞ ባላባቶች ከተሸጠበት ከደቡብ አፍሪካ ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ገንዘብ ከፍለው ነጻ ያወጡት ያንዱ ሰው ትውልዶች  በደርግ ዘመን ከኢትዮጵያ ወደ  ካናዳ ተሰደው አሁንም ድረስ ካናዳ ውስጥ  እንደሚኖሩ ጥናቱ ያሳያል።
በዐፄ ምኒልክ በባርነት ከመሸጥ የተረፉት ውለታ ቢሶቹ እነ በቀለ ግን ይህን እውነት ማወቅም መናገርም አይፈልጉም። በቀለ ስለቋንቋ መጨፍለቅ አብዝቶ ያወራል። ሆኖም ግን ኦሮሞ ገርባ ያደረጋቸውን የሱ ዘሮች ቋንቋ ኦሮሞ ጨፍልቆ እንዳጠፋውና ማንነታቸውን እንደቀየረው መናገር አይፈልግም። በቀለ ራሱን ሳያውቅ እስከመቼ ነው  ነጻነትን የማያውቅ ነጻ አውጭ ሆኖ የሰው ማንነት ተጭኖበት የሚዘልቀው? በእውነቱ  የበቀለን ዘሮች ኦሮሞ  በባርነት ሰንሰለት ካሰረበት ጨለማ ወደ ብርሀን እንዲወጡ ያደረጉትን  ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ «ጭራቅ» አድርጎ  ሊያቀርብ  የሚችል ቢኖር ራሱን የረሳና ነጻ በመውጣቱ የሚቆጭ ኢሰብአዊ ፍጡር ብቻ ነው።
በቀለ  ገርባ ከመቀሌ እንደተመለሰ በሰጠው ቃለ ምልልስ ያነሳው ሌላው ውሸቱ  ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ የሚወስደው መንገድ ለአንድ ዓመት [በአማሮች] እንደተዘጋ የተናገረው ነው። በትናንትና እለት አባይ ሜዲያ ያቀረባቸው  ከአዲስ አበባ  ወደ መቀሌ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አራት የአገር አቀፍ የሕዝብ ማመላለሻ ድርጅቶች ኃላፊዎች እንደነገሩን ከአዲስ አበባ   ወደ መቀሌ የሚወስደው መንገድ እንዳልተዘጋና በአፋር አድርገው ወደ መቀሌ የሚሄዱትም  ከደብረ ብርሀን  በኋላ የተተከሉት የፍጥነት መቆጣጠሪያዎች መንገዱን ለመኪኖቻቸው ምቹ እንዳይሆን በማድረጋቸው መሆኑን አስተድተዋል። በርግጥ የአራቱም አገር አቀፍ የአሽከርካሪ ድርጅቶች ኃላፊዎች ግርግር በነበረበት ወቅት አላማጣ ላይ መንገድ ተዘግቶ እንደነበር አልሸሸጉም። ሆኖም ግን አላማጣ በዛሬዋ ኢትዮጵያ የሚገኘው ትግራይ ውስጥ እንጂ አማራ ክልል በሚባለው አካባቢ በመሆኑ የአላማጣው መንገድ ለተወሰነ ጊዜ ቢዘጋ እንኳ የተዘጋው በቀለ ሊነግረን እንደፈለገው በአማሮች ሳይሆን በቀለን መቀሌ በጋበዙት በሕወሓቶች ነው። በቀለ ገርባ ያልተዘጋ መንገድ አንድ ዓመት እንደተዘጋ የውሸት ወሬ የሚያሰራጨው  የአማራንና የትግሬን ሕዝብ ለማቃቃርና ለማዋጋት ፕሮፖጋንዳ መስራቱ ነው፤ ሆኖም ይህ  አይሳካለትም።
የአራቱም አገር አቀፍ የአሽከርካሪ ድርጅቶች ኃላፊዎች አንድ አመት ሙሉ  አገልግሎት የማይሰጡባቸውና የተዘጉ መስመሮች ያሏቸውን ግን ተናግረዋል።  አገልግሎት የማይሰጡበትና የተዘጋ ያሉት ዋናው መስመር ከአዲ አበባ ወደ ጋምቤላ የተዘረጋው መስመር ነው። ይህም መስመር  ወለጋ  ላይ የተዘጋ ሲሆን የተዘጋውም ወለጋ በተፈጠረው የሰላም መደፍረስ መሆኑን አስረድተዋል። ወለጋ ሰላም የደፈረሰው በኦነግ ጦር ምክንያት ነው። በቀለ ገርባ ግን ስለዚህ መንገድ መዘጋት ሊነግረን አይፈልግም!
ከአዲስ  አበባ ወደ ጋምቤላ  የተዘረጋውን መንገድ ወለጋ ላይ  የዘጋውንና ንጹሐንን የሚጨፈጭፈውን ኦነግን ለመውጋት  ጦር  ለምን ተላከ፣ ጦሩ ወደ ካምፑ ይግባ እያለ  የአደባባይ ንግግር ሲያደርግ የምናውቀው በቀለ ነው እንግዲህ  በገረፉት ሕወሓቶች ለመወደድ ሲል ያልተዘጋውን የአዲስ አበባ መቀሌ መስመር እንደተዘጋ አድርጎ  በመዋሸት  ያልተዘጋውን  የአዲስ አበባ መቀሌ መንገድ  «መንግሥት ጦር ልኮ  እንዲያስከፍተው» ሲል  ለአገዛዙ ጥሪ የሚያቀርበውና ሰብዓዊና ሞራላዊ ሰው ለመሆን የሚቃጣው!
ከአዲስ  አበባ ወደ ጋምቤላ  የተዘረጋውን መንገድ ወለጋ ላይ  የዘጋውንና ንጹሐንን የሚጨፈጭፈውን ኦነግን ለመውጋት የተላከው ጦር ወደ ካምፑ ይመለስ እያለ ሲላዝን የምናውቀው በቀለ በምን ሞራሉ ነው በኦነግ ምክንያት  ወለጋ ላይ የተዘጋውን መንገድ  እንዲከፈት አገዛዙን ሳይጠቅ ያልተዘጋው መንገድ በጦር እንዲከፈት አገዛዙን የሚጠይቀው? ጥላቻስ ከዚህ በላይ ምንድነው? ምነው ሰውዬው ራሱን ፈጽሞ ረሳ?
Filed in: Amharic