>
1:02 am - Thursday December 1, 2022

መታገድ ያለበት የዘር ፖለቲካ የትኛው ነው?

መታገድ ያለበት የዘር ፖለቲካ የትኛው ነው?
አቻምየለህ ታምሩ
የዘር ፖለቲካ ወይንም Politics of Racism ማለት አንዱ ዘር ከሌላው ይበልጣል ወይም አንደኛው ከሌላው ያንሳል አልያም አንዱ ዘረኛ ከሌላው ዘረኛ ይለያል በሚል እሳቤ የሚካሄድ ፖለቲካ ነው። ዛሬ ስልጣን ላይ ያሉትን ጨምሮ ባገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት 28 ዓመታት እየተካሄደ ያለው የዘር ፖለቲካ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በማኅበራዊ ሜዲያ «የዘር ፖለቲካ ይታገድልን» የሚል  እንቅስቃሴ እየተካሄደ ይገኛል። ይህን እንቅስቃሴ በዋናነት የሚመሩት  ግንቦት ሰባቶች ናቸው። ግንቦት ሰባት «የዘር ፖለቲካ ይታገድልን» የሚል እንቅስቃሴ የጀመረው የዘር ፖለቲካን ተጠይፎ ሳይሆን የአማራው በአማራነት መደራጀትና መጠናከር ስላሰጋው ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ የዘር ፖለቲካ የሚያራምደው በአማራነት የተደራጀው ኃይል ሳይሆን ግንቦት ሰባት ወይም በአዲሱ የዳቦ ስሙ ኢዜማ እየተባ የሚጠራው የነ ብርሀኑ ነጋ ስብስብ ነው። እውነተኞቹ ዘረኞች ናቸው እንግዲህ የዘር ፖለቲካ ይታገድ ብለው ጩኸታችንን የሚቀሙት።
አማራ በአማራነቱ የተደራጀው የዘር ፖለቲካ ሊያካሂድ ሳይሆን በሕገ መንግሥት ተደግፎ፣ በተቋማት ታግዞ፣ በፖሊሲ ታውጆና ሊያጠቁት የሚችሉ ሰዎች ሰልጥነው እየተካሄደበት ያለውን የዘር ማጥፋትና ኅብረተሰባዊ እረፍት ማጣት ለመከላከል ነው። አማራ በአማራነቱ የተደራጀው ኦሕዴድ፣ ኦነግ፣ ሕወሓት፣ ወዘተ ፖለቲካ ደማዊ ነው [politics is primordial] በሚል እሳቤ አይደለም። አማራ በሕገ መንግሥት ተደግፎ፣ በተቋማት ታግዞና ፖሊሲ ተቀርጾ የታወጀበት የዘር ማጥፋትና የአፓርታይድ ፖለቲካ ከተወገደለት በእሴቶች ዙሪያ እንጂ በአማራነቱ በመደራጀት ፖለቲካ አያካሂድም።
የትናንቱ ግንቦት ሰባትና የዛሬው ኢዜማ  የሚታወቀው ፖለቲካ ደማዊ ነው ብለው ከሚያምኑት ከነኦነግ ኦዴግና ከኦሕዴድ ጋር አብሮ በመስራት ነው። ኢዜማ ከነዚህ ድርጅቶች ጋር አብሮ የሚሰራበት የመገናኛና የአንድነት መሠረቱ (Point of Convergance) የዘር ፖለቲካ ነው። ለዚህ አንዱ ማሳያ ግንቦት ሰባት በ2008 ዓ.ም. በልሳኑ ባወጣው መግለጫው ሥልጣንን ወደ ከትግሬና አማራ ወደ ኦሮሞና ደቡብ ለማሸጋገር እንደሚሰራ ማወጁ ነው። አማራ በአማራነቱ ተደራጅቶ የታገለው በሥልጣን ላይ የነበሩት ሰዎች ትግሬዎች ስለመሆኑ ሳይሆን ማንም በመንግሥትነት ይሰየም ወያኔዎች የያዙትን ሀሳብ እምነቱ አድርጎ በመንግሥትነት የሚሰየም አካል ከዘረኛነት ፖለቲካ በስተቀር ሌላ ውጤት ስለማያመጣ ነው።
 ግንቦት ሰባት የሕወሓትን እምነት የያዙትን  ኦሮሞዎችና ደቡቦች ወደ ስልጣን ለማምጣት እንደሚታገል ያወጣውን «አዋጅ» ተከትሎ ከግንቦት ሰባት ጋር ጥምረት መስርቶ አገራዊ ንቅሳቄ ውስጥ የነበረው የኦዴግ ቃል አቶ ሌንጮ ባቲ ባወጣው አንድ ጽሑፍ  «ካሁን በኋላ ኦሮሞ ለሶስት ሺሕ አመት ኢትዮጵያን ይገዛል እርማችሁን አውጡ» አለን። ይህ የሌንጮ እምነት ኦዴግ ከግንቦት ሰባት ጋር ጥምረት ሲመሰርት የተያያዙበት የመገናኛና የአንድነት መሠረት (Point of Convergance) ነው።
ግንቦት ሰባት አገር ቤት ከገባ በኋላ ከትግሬ ዘረኞች የኦሮሞ ዘረኞች ይሻላሉ ወይም ይበልጣሉ  ብሎ የኦሮሞ ዘረኞችን ድርጅትና የዘረኛውን ድርጅት ሊቀመንበር መሪ ዐቢይ አሕመድን የለውጥ መሪ አድርጎ እያመለከ ይገኛል። ቀደም ብዬ የዘር ፖለቲካ ማለት አንዱ ዘረኛ ከሌላው ዘረኛ ይለያል በሚል እሳቤ የሚካሄድ ፖለቲካ ነው ብያለሁ። የሕወሓት እኅት ድርጅት የሆነውን ኦሕዴድ የሚባለውን የዘር ድርጅት የሚመራው ዐቢይ አሕመድ ከሕወሓት የሚለዬው ኦሮሞ በመሆኑ ብቻ ነው። በሌላ አነጋገር የኢዜማ ፖለቲካ ከትግሬ ዘረኛ የኦሮሞ ዘረኛ ይሻላል ወይም ይለያል የሚል ነው። ከዚህ በላይ እውነተኛና የለየለት  ዘረኛነትና የዘረኛነት ፖለቲካ  የለም። ትግሬዎቹ በሕወሓትነት ተደራጅተው አገር አቆረቆዙ  ብሎ እንደተቆጣ የነገረን ኃይል ኦሮሞዎቹ በኦሕዴነትና ኦነግነት ተደራጅተው ሕወሓት 27 ዓመታት የፈጀበትን የነውረኛነት ክብረ ወሰን በአስር ወር ሲቀዳጁት rationalize ለማድረክ ከመሞከር በላይ የኢዜማ  እውነተኛ ዘረኛነት የለም።
ባጭሩ እልም ያሉት ዘረኞች  በሕወሓት ዘመን የአንድ ነገድ የበላይነት አለ ብለው  ሲታገሉ የነበሩትና  ዛሬ ላይ  ግን ተረኛ ነን ባዮቹ  የኦሮሞ ብሔርተኞች የበላይ ለመሆንና ይህንንም  ለሶስት ሺሕ ዓመታት ለማስቀጠል የሚሰሩትን የሚደግፉት የትናንትናዎቹ ግንቦት ሰባቶችና የዛሬዎቹ ኢዜማዎቹ ናቸው።
ስለዚህ በአገራችን መታገድ ያለበት የዘር ፖለቲካ የትግሬ ዘረኞች የመዘረቱትን የሕወሓት አገዛዝ ተቃውመው የኦሮሞ ዘረኞች የመሰረቱትን የኦሕዴድ/ኦነግ አገዛዝ  ለመከላከል rationalize ለማድረክ የሚሞክረው፤ ትግሬውን መለስ ዜናዊን አውግዞ የመለስ ዜናዊን ዙፋን ወራሽና  መዋቅሩን የተካውን ኦሮሞውን ዐቢይ አሕመድን እንደ ለውጥ አራማጅ ቆጥሮ ማምለክን ፖለቲካው ያደረገው የለየለቱ እውነተኛውና ያፈጠጠው  የኢዜማ የዘረኛነትፖለቲካ ነው። የኦሮሞ ዘረኞችን patronize በማረድግ የትግሬ ዘረኞችን የሚያወግዙት እውነተኞቹ ዘረኞች ኢዜማዎች የዘር ፖለቲካን የማውገዝ ሞራል የላቸው።
Filed in: Amharic