>
5:13 pm - Monday April 18, 2072

ፍትሕ ለጋዜጠኛ በሪሁን አዳነ (ጋዜጠኛ በላይ ማናዬ)

ፍትሕ ለጋዜጠኛ በሪሁን አዳነ
ጋዜጠኛ በላይ ማናዬ
 
በሪሁን አዳነ በዋናነት የሚታወቀው በጋዜጠኝነቱ ነው፡፡ በሪሁን በእንቁ እና ውይይት መጽሄቶች፣ ቀለም ቀንድ እና በረራ ጋዜጦች ላይ በአዘጋጅነት ሰርቷል፡፡ በእነዚህ የህትመት ውጤቶች በሳል ጽሁፎቹን በመጻፍ የሚታወቀው ጋዜጠኛ በሪሁን አዳነ፣ በሰራባቸው የሚዲያ ውጤቶች ሁሉ ከባልደረቦቹ ጋር ተግባብቶ በመስራት የሚታወቅ ሲሆን፣ ጀማሪ ጋዜጠኞችን በማብቃትም ስሙ ይነሳል፡፡
በሪሁን አዳነ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፖለቲካል ሳይንስ አጥንቷል፡፡ አሁንም በዚሁ ተቋም ትምህርቱን የቀጠለ ሲሆን፣ ፖለቲካል ሳይንስ ትምህርትንም ያስተምራል፡፡ በቅርብ የተመሰረተው የአማራ ሳተላይት ራዲዮ እና ቴሌቪዥን (አሥራት ሚዲያ) ላይም ጉልህ ሚና አለው፡፡ በሪሁን ከአሥራት መስራቾች አንዱ እና የአዲስ አበባ ስቱዲዮ አስተባባሪም ነው፡፡
ጋዜጠኛ በሪሁን አዳነ እነዚህን ኃላፊነቶች እየተወጣ እያለ ነው ሰኔ 17 ቀን 2011 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ በፖሊስ ተይዞ መታሰሩ የታወቀው፡፡ ፖሊስ ጋዜጠኛ በሪሁን ከሰኔ 15ቱ ክስተት ጋር በተያያዘ እንደተጠረጠረ በመጥቀስ ለፍርድ ቤት ቀጠሮ ጠይቆበታል፡፡ እስካሁን አምስት ጊዜ ፍርድ ቤት በቀጠሮ ተመላልሷል፡፡ ጋዜጠኛ በሪሁን በእስር በሚገኝበት አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጠያቂ ተከልክሎ፣ ጨለማ እና ቀዝቃዛ ክፍል ውስጥ እንዲቀመጥ መደረጉን በመግለጽ፣ ሰብዓዊ መብት ጥሰቱ እንዲቆም ለፍርድ ቤት ጠይቋል፡፡
Filed in: Amharic