>
5:13 pm - Saturday April 20, 5669

ኢትዮጵያ የማን ናት ?! (ተስፉዬ እሸቱ)

(በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትያትር ጥበባት መምህር፣ የባህል ተመራማሪና ተዋናይ)
• እኔ ምለው ይሄ የኛን አገር የአማራ፣ ኦሮሞ እና ትግሬ… ወይም የኦሮሞ፣ ትግሬና የአማራ… ወይም የትግሬ፣ አማራና ኦሮሞ ብቻ ያደረገው ማን ነው?!
 
በአገሬ  የተሳከረ ነገር አለ፣
”አማራ ብሎ ጽሑፉን የጀመረው ጸሐፊው አማራ ሰለሆነ ነው፤“  ወይም “ በጽሑፉ ኦሮሞን መሀከል ያደረገው ለኦሮሞ ያለው አመለካከት መካከለኛ ስለሆነ ነው፤” ወይም ” ትግሬን ደግሞ መጨረሻ ያደረገው ትግሬ ጠል ስለሆነ ነው፤” ከሚል አስተሳሰብ ለመሸሽ (ዳሩ  ካለንበት የተንሸዋረረ ሁናቴ አንጻር መሸሽ ባይቻልም) እና በተቻለ መጠን አካታች ለመሆን ታስቦ የተደረገ ነው፡፡
አሁን አሁን  ብዙ ነገሮችን ስታዘብ “አገሬ ከላይ የጠቀስኳቸው የሦስቱ ብሄሮች አገር ብቻ ናት እንዴ?”  ብዬ እንድጠይቅ እገደዳለሁ፡፡
ለምሳሌ:- በአገር ደረጃ ከሦስቱ ብሄሮች የሆነ ሰው ከተሾመ፣ እርግጠኛ ሁኑ የተቀሩት ሁለቱ ብሄሮች ይጮሀሉ፡፡ ማህበራዊ ሚዲያው ይጮሃል፡፡ በአማርኛ “አክቲቪስቲ” ማለት ምን ማለት እንደሆነ ስለጠፋብኝ ነው፡፡ ምክንያቱም  ቃሉን ብቻ ከእንግሊዘኛ ኮርጀን ተግባሩን አምጥተነዋል ብዬ ስለማላስብ ነው፡፡
“አክቲቪስቶቹ” ይጮሓሉ፡፡ ምን አለፋችሁ ሳር ቅጠሉ ይጮሃል፡፡ ጩኸቱ የተሾመው ሰው ለቢሮው ‘ይመጥናል? አይመጥንም?’ ሳይሆን “የእኔ ብሄር እንዴት ሳይሾም ቀረ? ብሔሬ ተገለለ፤ ብሔሬ ተነካ፤ ብሔሬ ተደፈረ፤” እና ወዘተ… መሆኑ ግን ያሳዝናል፡፡ የፍጥነት ባቡር ወይም መንገድ ወይም መብራት ወይም ሌላ ነገር ለአንዱ ብሄር ተሰጠ ቢባል እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል ሁለቱ ይጮሃል፡፡
 ሌላው ቢቀር  “ሳጥናኤል ተይዞ ከሦስቱ ብሄሮች  ለአንዱ ተሰጧል” ቢባል፣  ሳጥናኤልን ያላገኙት ሁለቱ ብሄሮች ላለመጮሃቸው እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ በአገሪቱ አቧራ ላለመነሳቱም እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ የሁለቱ ብሔር ምሁራን “ሳጥናኤል ለብሄር ያለው ጠቀሜታ፣ የሳጥናኤል እና ብሄር ታሪካዊ ግንኙነት” እና መሰል ሀሳቦች በየክልሉ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ላለመቅረበቸው  አሁንም እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ ኧረ ጎበዝ ሰው መሆን ማለት በቀላሉ ስሟንና ብሄሯን ስለማናውቃት ኢትዮጵያዊት እናት መቆርቆር ማለት ይመስለኛል።
እንዴ ይሄ የእኛ አገር ግን የሦስቱ ብሄሮች ብቻ ነው ማለት ነው?! እንዴት ነው ነገሩ…. ኢትዮጵያ እኮ… ጋምቤላ እየኖረ፣ ከባሮ አሳ እያወጣ “ወደፊት በአሳ ምርት አገሬ ኢትዮጵያን አሳውቃታለሁ፤” ብሎ የሚያልመውም አገሩ ናት፡፡ ሶማሌ ክልል ሽርጡን ሸርጦ ፍየሎቹን እየጠበቀ “ወደፊት የኢትዮጵያን አውሮፕላን ኒው ዮርክ አሳርፌ፣ አገሬን ትርፋማ አደርጋታለሁ፤”  ብሎ ተስፋ ለሰነቀውም  ኢትዮጵያ አገሩ ናት፡፡
አገሬ፣ ኢትዮጵያ እኮ የሦስት ብሄሮች አገር ብቻ አይደለችም፡፡ ኢትዮጵያ እኮ… ቤንሻንጉል  ወርቁን እያወጣ “ወደፌት በኔ ወርቅ አገሬን በንግዱ ዘርፍ ተወዳዳሪ አደርጋታለሁ፤” ለሚለው ባለተስፋም አገሩ ናት፡፡ የአፍዴራ ጨው እያወጣ “አገሬማ ጨው ከውጭ አታስገባም!” ብሎ ለሚተጋውም ለጋስ አፋር ኢትዮጵያ አገሩ ናት፡፡ እንዴ ኢትዮጵያ እኮ….. ወይ ሲዳማ ወይም ሀረሪ ወይ ሌላ ጫፍ ተወልዳ፣ ምን መሆን እንደፈለገች ስትጠየቅ “ ትምህርቴን ስጨርስ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር  መሆን እፈልጋለሁ፤” ለምትል ተስፈኛም ኢትዮጵያ አገሯ ናት፡፡
አዎ!! እደግመዋለሁም ይህች ትልቅ የእኛ አገር የሁላችንም ናት፡፡
ለማንኛውም… ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሬ ሆይ…… እስኪ ካቢኒዎን ከሦስቱ ጉምቱ ብሄሮች ውጭ አዋቅረው ደግሞ ይሞክሩት!
Filed in: Amharic