>

አነጋጋሪው የጠ/ሚ/ር አብይ እና የአቶ አንዳርጋቸው ነገር... (በታምሩ ገዳ -ሕብር ሬዲዮ)

አነጋጋሪው የጠ/ሚ/ር አብይ እና የአቶ አንዳርጋቸው ነገር…
በታምሩ ገዳ- ሕብር ሬዲዮ
* ”  ከፕ/ት ኢሳያስ/ከሻቢያ  ጋር ለመታረቅ በፕሬዜዳንቶች፣ በንጉሶች ፣በኤሚሮች፣በሼኮች ሞክሪያለሁ። አሁን ግን  ልታስታርቁን የምትችሉት እናንተ ግንቦት ሰባቶች በተለይ አንተ ነህ፣ ቀልቤም ቢሆን አንተን ብሎኛል እና እባክህን አስታርቀን” ሲሉ  ተማጸኑኝ ።እኔም “እስቲ  የተቻለኝን  ልሞክር” ብዬ  በቀጥታ ወደ ኤርትራ በማምራት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂን  ስለጉዳዩ አነጋገርኳቸው።ፕ/ቱም ‘ይሔ  በወያኔ ስር ያደገ፣ ግልገል ወያኔን እንዴት ታምነዋለህ?’ ሲሉ ጥርጣሬያቸውን ገለጹልኝ….
….
ጠ/ሚ/ር አብይ አሕመድ “ለግንቦት ሰባት ቁልፍ መረጃዎችን  በመስጠት አንገታቸውን ለካራ ፣ግንባራቸውን ለጥይት ፣ቤተሰቦቻቸውን ለስደት  ሰጥተው እንደ ነበር  እጫውተውኛል “ሲሉ አንድ የቀድሞው የግንባሩ ከፍተኛ አመራር ሰሞኑን ይፋ አደረጉ ።
ይህ የተገለጸው  ባለፈው ሐምሌ 20,2019 እኤአ በካናዳ ቶሮንቶ ከተማ  ውስጥ   የኢዜማ የድጋፍ ሰጪ በጠራው ስብሰባ ላይ የተገኙት ግንቦት ሰባትን ከመሰረቱ  አንዱ  የሆኑት  እና በዋና ጸሐፊነት የገለገሉት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ለተሰብሳቢዎቹ ባሰሙት ንግግር ላይ ነበር ።
በወቅቱ በስብሰባው ላይ ከታደሙት መካከል እንዱ የነበረው የዋሊያ  ኢንፎርሜሽን   ጋዜጠኛ ኤልያስ አወቀ ሰሞኑን እንደ ዘገበው  እና  የስብሰባውን ድባብም በተመለከተ  ለህብር ራዲዬም  በስልክ እንዳረጋገጠው  ለሰላሳ  አራት ደቂቃዎች  ንግግር ያደረጉት አቶ አንዳርጋቸው ከአራት አመታት የእስራት ቆይታ  በወጡ ማግስት ጠ/ሚ/ር አብይ አሕመድን በጽ/ቤታቸው ሲያነጋግሯቸው” አንተ ለአራት አመታት  ታስረሃል፣ እኔ ደግሞ ለስድስት አመታት በመታሰሬ  አንተ የሁለት አመት እዳ አለብህ አሉኝ፣እኔም እንዴት?ስል   ዶ/ር አብይን ጠየኳቸው”ሲሉ አቶ አንዳርጋቸው አውስተዋል።
ከጠ/ሚ/ር አብይ ጋር ለሶስት ሰዐታት የዘለቀ ንግግር ማድረጋቸውን ለታዳሚዎቹ የተናገሩት አቶ አንዳርጋቸው”እኔ ለእናንተ መረጃ ለማቀበል ስል አንገቴን ለካራ፣ግንባሬን ለጥይት ፣ቤተሰቦቼን ለስደት ዳርጌ  ፣በህይወቴ ላይ ቁማር ተጫውቼበት ነበር።የዚያ መረጃ ምንጩ እኔ መሆኑ ቢታወቅ    ኖሮ ጨካኙቹ  ወያኔዎች ስጋዬን ይዘለዝሉት ነበር ሲሉ ዶ/ር አጫውተውኛል። “በማለት   አቶ አንዳርጋቸው    ስለ ምስጢራዊ ውይይታቸው  ለተሰብሳቢዎቹ በግርድፉ ገልጸዋል። የመረጃው ይዘት ፣እንዴት እና መቼ  ከወያኔ እጅ ሾልኮ ለግንቦት ሰባት እንደተሰጠ ከመዘርዘርም አቶ አንዳርጋቸው  ተቆጥበዋል።
የፕ/ት ኢሳያስ አፈወርቂ  ጥርጣሬ እና ውሳኔ :-
እንደ አቶ አንዳርጋቸው  የቶሮንቶው  የኢዜማ ስብሰባ  ገለጻ  ከሆነ  በኤርትራው ፕ/ት በአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ እና በ ጠ/ሚ/ር አብይ መካከል የተደረገውን  ስምምነት መንገድን የጠረጉት እርሳቸው መሆናቸውን የተናገሩ ሲሆን ”  ከፕ/ት ኢሳያስ/ከሻቢያ  ጋር ለመታረቅ በፕሬዜዳንቶች፣ በንጉሶች ፣በኤሚሮች፣በሼኮች ሞክሪያለሁ። አሁን ግን  ልታስታርቁን የምትችሉት እናንተ ግንቦት ሰባቶች በተለይ አንተ ነህ፣ ቀልቤም ቢሆን አንትን ብሎኛል እና እባክህን አስታርቀን ሲሉ  ተማጸኑኝ ።እኔም እስቲ  የተቻለኝን  ልሞክር ብዬ  በቀጥታ ወደ ኤርትራ በማምራት አቶ ኢሳያስ አፈወርቅን  ስለጉዳዩ አነጋገርኳቸው።ፕ/ቱም ‘ይሔ  በወያኔ ስር ያደገ፣ ግልገል ወያኔን እንዴት ታምነዋለህ?’ሲሉ ጥርጣሬያቸውን ገለጹልኝ።እኔም  በመቀጠል አይ ሰውየውንስ አምናቸዋለሁ አልኳቸው።ፕ/ት ኢሳያስም ‘ምን የሚያሳምንህ ምክንያት አለህ?’ሲሉኝ ተከታይ ጥያቄ አቀረቡልኝ።እኔም  አንተ የምታውቀው አንዱን ምስጢር ጨምሮ እነዚያ ስለ ሻቢያ የተነገሩት   እና ከወያኔ አፈትልከው የወጡት አራቱ  ምስጢሮችን  እንድናገኛቸው  የርዳን ዶ/ር አብይ እኮ ነው  አልኳቸው።
 አቶ ኢሳያስም ሳያንገራግሩ  ‘ይሄንን ያደረገው እርሱ ከሆነማ ጉዳዩን ለእኔ ትውልኝ  በማለት የፓለቲካ ጉዳዬች  ሐላፊ እና አማካሪያቸው የሆኑት  አቶ የማነ ገ/አብን ወደ አ/አ በአስቸኳይ እንደሚልኳቸው ቃል  ገቡልኝ።ውሎ ሳያድርም  የእርቀ ሰላሙ ስምምነት ተፈረመ” በማለት  አቶ አንዳርጋቸው  በኢትዬ-ኤርትራ  ስምምነት ላይ የእርሳቸው ስውር  እጆች እንዳሉበት ለቶሮንቶ የኢዜማ ደጋፊዎች ተናግረዋል ። ስለ አራቱ ምስጢሮች ምንነት በተመለከት  ግን ለማብራራት አልፈለጉም ፣የጠየቃቸውም አልነበረም። ከጠ/ሚ/ር አብይ አሕመድ ጋር አድርገናል ያሉት  የቤ/መንግስት ውይይትም ቢሆን ለሶስተኛ ወገን የማይነገር (off the record) ስለመሆነ እና  አለመሆኑ በውል አልታወቀም።
ሰለሰኔ 15ቱ የባለስልጣናት ግድያ  ቅድሚያ ትንበያ :-
የዶ/ር አብይ አሕመድ ኢትዬጵያ ውስጥ  ከሚታየው የፖለቲካ ትኩሳት አኳያ ምን ማደረግ እንዳለበት እና የተያያዘውን የሽግግር ወቅትን እንዲያሳካ   ከተሞክሯቸው አኳያ ፍኖተ ካርታ (ሮድ ማፕ) ቀርጸው  ለጠ/ሚ/ሩ እና ለባለስልጣናቱ መስጠታቸውን   እና የአክራሪ ብሔርተኝነት በአገሪቱ መንሰራፋቱን በቶሮንቶው ስብሰባ ላይ የጠቀሱት አቶ አንዳርጋቸው  ባለፈው  ሰኔ 15 ,2011 ዓም በባሕር ዳር  ከተማ ውስጥ የክልሉ ፕ/ት የነበሩት ዶ/ር አምባቸው መኮንን  ጨምሮ ከፍተኛ ባለስልጣናት የተገደሉበትን አሳዛኝ ክስተት በተመለከተ”ማ ማንን እንደሚገድል  ስም ዝርዝራቸውን ሳይቀር  ጽፌ    በቅድሚያ ሰጥቼው ነበር(ለጠ/ሚ/ሩ?)”ሲሉ መናገራቸውን ፣ ነገር ግን የገዳዬቹን ሆነ የሟቾቹን  ስም ዝርዝሮችን  ለቶሮንቶ የኢዜማ ታዳሚዎች ይፋ ያለማድረጋቸውን የታዘበው ጋዜጠኛ ኤሊያስ “አባባላቸው ፖለቲካዊ ትንግርት? ወይስ ፖለቲካዊ ሟርት?”ሲል በሰሞነኛ ዘገባው ላይ  ጠይቋል።
 የኢትዬጵያ እጣ ፈንታ፣ማንንስ እንደ ግፍ?:- 
ኢትዬጵያ ከተደቀነባት የጎሳ ፖለቲካ ቁርቋሶ የተነሳ” 80%የመበታተን እድል አላት” ያሉት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ “ኢትዬጵያን ከመበታተን ለመታደግ  ከተፈለገ በቀሪው 20% ላይ ትኩረት አድርገን  ዶ/ር አብን ከመደገፍ ውጪ ሌላ አማራጭ የለንም፣ዶ/ር አብይ ከስልጣን ቢወርዱ መከላከያውን  የሚቆጣጠር ፣የስልጣን ክፍተቱን የሚሞላ አንዳችም የፖለቲካ ሀይል  በአሁኑ ሰአት አይኖርም  ” በማለት  ለታዳሚዎቹ አቋማቸውን እና ስጋታቸውን አካፍለዋል።
“ከማንም መንግስት ጋር በፍቅር  አድሬ አላውቅም ፣ተወዳጅቼም  አላውቅም ፣አደርባይም ሆኜ አላውቅም።” ያሉት አቶ አንዳርጋቸው   ስለ ጠ/ሚ/ር አብይ አህመድ ስብእና በተመለከተ ሲናገሩ ” ዶ/ር አብይን በተመለከተ ልናገር የምችለው አንድ ትልቅ  ነገር ቢኖር  እርሱ ውስጥ ያለውን ኢትዬጵያዊነት  ስሜት ማንም የአንድነት ሀይል ነኝ  ብሎ ከሚዘምረው ፣ በእየአደባባዩ ከሚለፍፈው እና ከሚጮኸው ቡድን ሆነ ግለሰብ  መካከል ከዶ/ር አብይ አሕመድ ጋር በጭራሽ  የሚስተካከል    የለም ” ሲሉ አቶ አንዳርጋቸው በዶ/ር አብይ አሕመድ ላይ  ያላቸው ጽኑ እምነትን ተናግረዋል።
ስለ የትግራይ ክልላዊ መንግስት ጉዳይ:-
በአሁኑ ወቅት በኢትዬጵያ ውስጥ የተወሰኑ ክልሎች በተለይ ደግሞ የኦሮሚያ፣የትግራይ እና የአማራ ክልሎች  ከፌደራሉ መንግስት ያልተናነሰ  ሚሊሻዎችን  ማሰልጠናቸው እና የጦር መሳሪያዎችን ማጋበሳቸውን የመከላከያ ባለስልጣናት ሳይቀሩ በአደባባይ ሲናገሩ ተደምጠዋል።
እንደ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የቶሮንቶ ኢዜማ ስብሰባ  ገለጻ ግን የትግራይ   ክልላዊ መንግስት  “የሚሳየል ባለቤት ነው፣ የጦር መሳሪያው የተገዛውም ከመንግስት ካዝና ሳይሆን ህወሃት በሚያስተዳድራቸው በእነ ኤፈርት አማካኝነት  ከሕዝቡ እጅግ ብዙ ገንዘብ ስለዘረፈ   የሚሳየሉ ግዢ የዚያ ውጤት  ነው” ማለታቸውን እና ወደፊትም ቢሆን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አዳዲስ መረጃዎችን በስፋት ይዘው እንደሚመጡ  ቃል መግባታቸው ታውቋል።
ስለ የቶሮንቶው ስብሰባ ለመዘገብ  በስፍራው የተገኙ  ከሁለት በላይ  ሚዲያዎች   እንደነበሩ  እና  ከዚና ሽፋን ውጪ ሙሉ ዘገባውን ያለማውጣታቸው ሌላኛው አስገራሚ እና አነጋጋሪ ጉዳይ መሆኑ ተመልክቷል። አቶ አንዳርጋቸው ሆኑ ፣ የዶ/ር አብይ አሕመድ አስተዳደር በቶሮንቶው  የኢዜማ ስብሰባ  ላይ ተነስተዋል ስለተባሉትጉዳዬች ዙሪያ  እስከአሁን ድረስ ተጨማሪ ማብራሪያ አሊያም ማስተባበያ  አለመስጡበትም ።
Filed in: Amharic