>

ይህ ዐይን ያወጣ ነውረኛነት ነው፤ ፍትሐዊም፣ ሞራላዊም፣ ተገቢም አይደለም!  ( አቻምየለህ ታምሩ)

ይህ ዐይን ያወጣ ነውረኛነት ነው፤ ፍትሐዊም፣ ሞራላዊም፣ ተገቢም አይደለም!  
አቻምየለህ ታምሩ
«የፌዴራል መንግሥት» ተብዮውን  ቋንቋ ማለትም አማርኛን  በክልሉ እንዳይሰራበት በሕግ የከለከለው «ኦሮምያ  ክልል»  ቋንቋዬ  የሚለው ማለትም «አፋን ኦሮሞ» የፌዴራል መንግሥት የስራ ቋንቋ ይሁን ብሎ የመጠየቅ የሞራል ልዕልና ከቶ የለውም!
«ኦሮምያ ክልል» ኦሮምኛ በፌዴራል መንግሥቱ ውስጥ  የመስሪያ ቋንቋ ሆኖ  እንዲሰራበት ጥያቄ ከማቅረቡ በፊት የፌዴራል መንግሥት ተብዮው የሚገለገልበትን የፌዴራል  ቋንቋ አማርኛን  ቅድሚያ የክልሉ  ተደራቢ የስራ ቋንቋ ማድረግ አለበት! ክልሉ ይህንን ሳያደርግ በ«ኦሮሚያ ክልል» ያልተደረገን  ነገር በፌደራል መንግሥቱ እንዲረደግ መጠየቁ ዐይን ያወጣ ነውረኛነት ነው፤ ፍትሐዊም፣ ሞራላዊም፣ ተገቢም አይደለም!
የፌዴራል ስርዓት የድርድር፣ የሰጥቶ መቀበል ስርዓት ነው። በፌዴራል ስርዓት ዝም ብሎ መቀበል ብሎ ነገር የለም።  ኦሮምያ የሚባለው ክልልን ቋንቋ  የፌዴሬሽኑ አባል «ክለሎች»፣ የፌዴራል መንግሥቱ  ተጨማሪ የስራ ቋንቋ እንዲሆን ሲጠይቅ  በምላሹ ለፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች መስጠት ያለበት ነገር አለ። ቋንቋው የፌዴራል መንግሥቱ የስራ ቋንቋ እንዲሆን የፌዴሬሽኑ አባል ከልሎች የሚጠይቀው ኦሮምያ የሚባለው ክልል ለፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች ሊሰጥ የሚገባውን ማሰብ አለበት።
በመሆኑም የድርድር ውጤት የሆነው የፌዴራል መንግሥት ቋንቋ ጉዳይ የሚመለከተው ሁሉ  ኦሮምያ የሚባለው ክልል የክልሌ  ቋንቋ  የሚለው ኦሮምኛ በኢትዮጵያ የፌዴራል መንግሥት ውስጥ  የመስሪያ ቋንቋ ሆኖ  እንዲሰራበት  የተጡቁት የፌዴሬሽኑ አባል «ክልሎች»  ኦሮምያ የሚባለው ክልል  የፌዴራሉ መንግሥት ኦሮምኛን የፌዴራል መንግሥት ቋንቋ እንዲደረግለት  ከመጠየቁ በፊት «የፌዴራል»  መንግሥቱ  የሚገለገልበትን የፌዴራል ቋንቋ  የሆነውን አማርኛን ተደራቢ የክልሉ  የስራ ቋንቋ ሆኖ እንዲሰራበት ማድረግ እንዳለበት እንደ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጥ  አለባቸው!
በሕገ መንግሥት  ተብዮው መሰረት ኦሮምኛ ተጨማሪ የፌዴራል መንግሥቱ የስራ ቋንቋ ይሁንልኝ የሚለውን ጥያቄ የሚያቀርበው ኦሮምያ የሚባለው ክልል የፌዴሬሽኑ አባል የሆኑ ክልሎች የሚያቀርቡትን የመደራደሪያ ነጥብ ካልተቀበለ  ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ እንዲሉ ኦሮምኛን የፌዴራሉ መንግሥቱ የስራ ቋንቋ ማድረግ አይችልም። ለምን ቢሉ ተጨማሪ የስራ ቋንቋን ሕገ መንግሥታዊ ለማድረግ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ስለሚጠይቅና ሕገ መንግሥት ለማሻሻል ደግሞ እያንዳንዱ የክልል ምክር ቤት veto power ስላለው ኦሮምያ የሚባለው ክልል የሚያቀርበውን ኦሮምኛ የፌዴራል መንግሥቱ ተጨማሪ  የስራ ቋንቋ ይሁንልኝ  የሚለውን ጥያቄ  አንዱ  ቅድመ ሁኔታው ያልተሟላለት የፌዴሬሽኑ አባል ክልል ብቻ veto ፓወሩን ተጠቅሞ  ኦሮምያ የሚባለው ክልል ያቀረበውን  ቋንቋዬ ተጨማሪ የፌዴራል መንግሥቱ የስራ ቋንቋ ይሁንልኝ  የሚለውን  ጥያቄ ውድቅ ማድረግ ይችላልና።
Filed in: Amharic