>
8:18 am - Tuesday December 6, 2022

ትንሽ ስለአማርኛ ቋንቋ...መራራ ሃቅ   (ታደለ ጥበቡ)

ትንሽ ስለአማርኛ ቋንቋ…መራራ ሃቅ
ታደለ ጥበቡ
1.የአማርኛ ቋንቋ ከክርስቶስ ልደት በፊት ነበረ።
በሁለተኛው ክፍለ ዘመን (200-130 ዓ.ዓ) የግብጹ ንጉሥ ጥሊሞስ 7ኛ መምህር የነበረውና   የግሪክ መልክዓ ምድር ተመራማሪ አጋታርከስ  በሰሜን ኢትዮጵያ የሚኖሩ  ህዝቦች የሚናገሩት የአማርኛ ቋንቋ እንደሆነ ጽፏል፥ተረጋግጧል። በአርኪኦሎጂያዊ ምርመራ ሂደት በአማርኛ የተቀረጹ ጥንታዊ የድንጋይ ላይ ጽሁፎች ተገኝተዋል (አምሳሉ 1976)
2.አማራዎች ከ3 ሺህ አመት በፊት በአማርኛ ቋንቋ ለንግሥት ሳባ ልጅ “ምኒልክ”ብለው ስም ከአወጡ በኋላ ይሁን በፊት በርካታ ስሞችን በአማርኛ  እናገኛለን።
3.አሜሪካዊው ቤንደር  በ1966 ዓ.ም በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ባሳተመው /Language in Ethiopia/ በሚሰኘው መፅሐፉ  በ9ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አማርኛ በቤተ-አምሓራ እንደተስፋፋ ጽፏል።ኩፐር የተባለው ጽሐፊ በንጉስ ላሊበላ ዘመን አማርኛ   ከአገወኛ ጋር በህዝቡ ይነገር ነበር ብሏል።
4.በ12ኛው መክዘ  አጼ ይኩኖ አምላክ  ዘመን ዐማርኛ ቋንቋ  ፈጽሞ ሠለጠነ ፤ ያማረ የተወደደ ፥ ጉሮሮ የማያንቅ ፥ ለንግግር የማያውክ ሁኖ ስለ ተገኘ ፣ የቤተ መንግሥት ቋንቋ ሆነ።ለአማርኛ  ዕድገት የማይናቅ አስተዋፅኦ ያደረገው የሀገራዊ ትምህርት ማዕከል ወደ አምሐራ  ተቀይሮ አቡነ ኢየሱስ ሞዓ ሐይቅ እስጢፋኖስ ላይ ከፈቱ።በዚህም የተነሣ ሐይቅን ተከትሎ ወለቃ ሌላው የትምህርት ማዕከል ሆነ።ወለቃ-ሐይቅም ደቡቡን ከሰሜን የሚያገናኝ የትምህርትና የባሕል ድልድይ ሆነ።13፣የ14ና 15ኛው መክዘ ቅዱሳን ገድላትን ስንመለከት ይህን ይገልጡልናል።የአማራ የትምህርቱ ኀላፊዎች፥ ማለትም አስተማሪዎቹና ደራሲዎቹ፥የግዕዝ ፊደል ኆኅያት ለአማርኛ ቋንቋ አልበቃ ስላለ የሚያባቁ ኆኄያት ፈጠሩለት።እነርሱም “ጀ”፥ “ጨ”፥ “ሸ” ፥ “ኘ”፥ “ቸ” ናቸው።አማሮች የነዚህ ኆኄዎች ምንጮች የቶቹ የግዕዝ ኆኄዎች እንደሆኑ አጥንተው፥ “ጀ”ን ከ “ደ”፥ “ጨ”ን ከ “ጠ”፥ “ሸ”ን ከ “ሰ”፥ “ኘ”ን ከ ”ነ”፥ “ቸ”ን ከ “ተ” አስወለዱ።
5.በይኩኖ አምላክ፣በአጼ አምደፅዮን፣በአጼ ዳዊት፤በአጼ ይስሐቅ፣በአጼ ዘርዓያዕቆብ፣በአጼ ገላውዴዎስ፣በአጼ ዘድንግል፣በርጉም ተክለሃይማኖት፣በአጼ ዮስጦስ እና ቴዎፍሎስ  የግዕዝ መጽሐፍ ወደ አማርኛ መተርጉም ጀመሩ።በአጼ ይኩኖአምላክ የወንጌላዊው እጨጌ ተክለሃይማኖት ታሪክ በአማርኛ ተጻፈ።በዐፄ አምደ ፅዮን በተገጠመው የ14ኛው መክዘ መጀመሪያ የአማርኛ ግጥም መካከል,   “አስመስሎ ገበሬ ሐርድ
               ዣን ይስሐቄ የግድ
                የዣን ሐርበይ ወልድ፤”የሚል ይገኛል።በተለይም በአጼ አምደፅዮንና በአጼ ይስሐቅ ዘመነ መንግሥት ማለትም በ14ኛው እና በ15ኛው ክፍለ ዘመናት ውስጥ ወደ ጽሁፋዊ ቋንቋነት በመሸጋገር ሰፊ አገልግሎት ሰጠ።የነገሥታት ወታደሮች የዘፈኗቸውና “የወታደሮች ዘፈኖች”የሚባሉትን ግጥሞች ስናይ አማርኛ በመካከለኛው ዘመን ይበልጥ እየዳበረ መምጣቱን ያሳያል።
6.በ16ኛው መክዘ አካባቢ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የካቶሊክ ሚስዮናውያን ከኦርቶዶክስ ሊቃውንት ጋር የነበራቸው ክርክር አማርኛ ቋንቋን በ2 መንገድ ጠቅሞታል።በአንድ በኩል ሚስዮናውያኑ ከነባሩ ግዕዝ ይልቅ አማርኛ ቋንቋን ለሃይማኖት ትምህርት ማስተማሪያነት ስለተጠቀመበት በዚህም አማርኛ የማስተማሪያ ቋንቋ ሆነ።ሚስዮናውያን መልእክቶቻቸውን በአማርኛ እየጻፉ ማስተላለፍ ጀመሩ።በተለይ ፓኤዝ ብዙ የካቶሊክን እምነት የሚገልጡ መጻሕፍት ወደ አማርኛ እንዲተረጎሙ አደረገ።(the missionary Factor,Merid Wolde Aregay,47,1996)።ይኼ ሂደትም አማርኛን የሃይማኖት ትምህርት መጻፊያ ቋንቋ እንዲሆን አስቻለው።
7.የተዋህዶ ሊቃውንቶች በበኩላቸው አማርኛን ከማስተማር ጎን ለጎን ለሚስዮናውያን መልስ ለመስጠት መጻሕፍ ወደ አማርኛ ተረጎሙ።ከእነዚህ መካከል፦
*አንቀጸ አሚን፣
*ጠቢበ ጠቢባን፣
*ሥነ ፍጥረት፣
*ምሥጢረ ጽጌያት ተተረጉሙ።
*ነገረ ሃይማኖት
*ትምህርተ ሃይማኖት ተጻፉ።
8.በጀርመን ሚሲዮናውያን አማካኝነት የዮሐንስ ወንጌል ወደ አማርኛ ተተርጉሞ በ1647 ታተመ።ሉዶልፍም የአማርኛ ሰዋስውን በ1698 አሳተመ።ርዕሱ “መጽሐፈ፡ትምህርት፡ዘልሳን፡አምኅራ” ይሰኛል። በጀርመናዊው ጸሐፊ እዮብ ሉዶልፍ እና ኢትዮጵያዊው አባ ጎርጎርዮስ ትብብር የተደረሰ የአማርኛ ሰዋሰው ነበር። አባ ጎርጎርዮስ ከቤተ አምሓራ ወደ ጣሊያን የሄዱ አባት ናቸው።መጽሐፉ፣ ከተለያዩ የሰዋሰው ጥናቶች በተጨማሪ የሉቃስ11፡1-13 ትርጓሜን፣ አባ ጎርጎሪዮስ ስለ ቅድስት ማርያምየደረሱትን ምስጋና፣ ግጥሞችና የለተ ተለት ንግግሮችን መዝግቦ ይገኛል።
9.ከ16ኛው መክዘ ወዲህም በኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ዘንድ የአማርኛ ሰዋስውን መጻፍ ተጀመረ።አማርኛ በ17ኛው መክዘ  በስነፁሁፍ ቋንቋነት የበለጠ አደገ።
*.ሀይማኖተ አበው፣
*.መፅሀፈ ንስሃ፣
*.መፅሃፈ ቀንዲል እና ሌሎችም ብራና መጽሐፍት  ከግዕዝ ወደ አማርኛ የተተረጎሙ። እንዲሁም በ17 ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የአባጊዮርጊስ ‹‹ድርሰት በአምሃርኛ›› የሚል ግጥም ተጻፈ፡፡
10.ከ17ኛው መክዘ በኋላ አማርኛ  የዕለት ተዕለት ማኅበራዊ ኑሮውን ቦታ ያዘ።በጎንደር ዙሪያ አድባራት የምናገኛቸው የ17ኛው፣የ18ኛውና ከዚያ በኋላ ያሉት መጻሕፍት በኅዳጋቸው የሚጽፉት የውርስ፣የርስት፣የሽያጭና ግዥ፣የውልደት፣መዛግብት በአማርኛ ቋንቋ የሚጻፉ ነበሩ።
ለመጀመሪያ ጊዜ በ1840 ዓ.ም. መፅሀፍ ቅዱስ በአባ አብርሃም/አባ ሮሜ/ ከግዕዝ ወደ አማርኛ ተመለሰ።(የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣30,32)
11.ንጉሥ ሣሕለ ሥላሴም በአማርኛ የመንግሥቱን የመጻጻፍ ሥራ በአማርኛ አደረገ።በዘመነ መሳፍንት የነበሩት እነ ራስ ዓሊ፣ደጃች ውቤ፣ደጃች ጎሹ፣ይጻጻፉ የነበረው በአማርኛ ነበር።የአጼ ቴወድሮስ  ዜና መዋዕል  በአማርኛ ተጻፈ።የአጼ ዮሐንስ ደብዳቤዎቻቸው በአማርኛ ይጻፉ ነበር።ጥቂቶችን ለመጥቀስ ያህል፦
*.የደብተራ ዘነብ “መጽሐፈ ጨዋታ ሥጋዊ ወመንፈሳዊ’ም”
*.ደብተራ ዘነብ የጻፉት የቴዎድሮስ ታሪክ፣
*.የኢዘንበርግ የዓለም ታሪክ (1842) እና
*የአማርኛ የጂኦግራፊ መጽሐፍ (1842) የዚህ ዘመን ማስታወሻዎች ናቸው።
*.የእንግሊዝ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበረም በ1842 የአርባዕቱን ወንጌል የግዕዝና አማርኛ እትም አሳተመ።
12.የዳግማዊ አጼ ምኒሊክ  አዋጆችን፣ደብዳቤዎቻቸውን እና የዘመኑን ፍርዶች በአማርኛ ነበሩ። የፕሮፊሰር አፈወርቅ ገብረእየሱስ የመጀመሪያው ልቦለድ “ጦቢያ” በ1900 ዓ.ም በሮም በአማርኛ ታትሟል።በ1908 ዓ.ም የዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ሲከፈት አማርኛ በስርዓተትምህርቱ ውስጥ ተካቶ እንደ አንድ የትምህርት አይነት መሰጠት ጀመረ።ይህ ተግባር በቀጣይነት በተከፈቱት ሀይማኖታዊም ሆነ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ቀጥሏል።በዚሁ ዘመን በኢትዮጵያ የመጀመሪያው  አእምሮ ጋዜጣ ተመሰረተ።በአማርኛም ታተመ።ለጋዜጣው አእምሮ ብለው ስም ያወጡለት ምኒልክ ናቸው።በየሳምንቱ ቅዳሜ ዕለት ይታተም ነበር።
13. መይሳው ካሳ (አፄ ቴዎድሮስ)  ለእንግሊዝ ማስጠንቀቂያ የሰጠው በአማርኛ ነው።
አፄ ዮሀንስ አዋጅ ያስነገረው በአማርኛ ነው።
አፄ ምኒልክ  አለምን ያስደነቀ አመራር የሰጠው በአማርኛ ነው።
አፄ ሀይለስላሴ ጀኔቫ ላይ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ንግግር ያደረጉት በአማርኛ ነው።
መንግስቱ ሀይለማሪያም 17  አመታት አንቀጥቅጦ የገዛህ በአማርኛ ነው።
መለስ ዜናዊ እድሜ ልኩን አገር የመራው በአማርኛ ነው።
የታላቋ አሜሪካ መሪ ፕሬዚደንት ኦባማ በአፍሪካ ህብረት ንግግር ሲጀምር በአማርኛ << ሰላም ናችሁ?>>  በማለት ነው የጀመረው።
*ዛሬ አማርኛ  በUS አሜሪካ የመንግስት ቋንቋ ነው።ከጀርመን ታዋቂ ከሆኑት ዩኒቨርስቲዎች አንዱ የሆነው ሀምቡርግ ዩንበርሲቲ የአማርኛ ት/ ት ማስተማር ከተጀመረ መቶ ዓመት አስቆጥሯል።
Filed in: Amharic