>
11:14 pm - Wednesday November 30, 2022

ሕገ መንግስታዊ መሻሻልን የሚጠይቁት የቋንቋ እና የክልል ጥያቄዎች (ያሬድ ሀይለማርያም)

ሕገ መንግስታዊ መሻሻልን የሚጠይቁት የቋንቋ እና የክልል ጥያቄዎች
ያሬድ ሀይለማርያም
ሕገ መንግስቱ እንዲሻሻል ምክንያት ከሚሆኑት በርካታ ጉዳዮች መካከል ሁለቱ የቋንቋ እና የክልል ጥያቄዎች ናቸው። በርካታ ቋንቋዎች እና እጅግ የተሰባጠረ ሕዝብ ባለባት እንደ ኢትዮጵያ አይነት አገር ውስጥ አማሪኛ ብቻ የፌዴራሉ ሥራ ቋንቋ እንዲሆን የሚደነግገው ሕገ መንግስት የአገሪቱ ሌሎች ሁለተኛ እና ሦስተኛ ቋንቋዎች አብረው እንዳያድጉ አድርጓል። አማርኛ የአገሪቱ የሥራ ቋንቋ እንዲሆን አድርጎ በተጨማሪ ኦሮሚኛን፣ ትግሪኛን እና ሱማሊኛን የብሄራዊ ቋንቋ ማድረግ ይቻል ነበር።
ከሃያ አመታት በፊት ኦሮሚኛን ጨምሮ ሌሎች የተወሰኑ ቋንቋዎች ብሔራዊ ቋንቋ ተደርገው እንዲበለጽጉ ሁኔታዎች ቢመቻቹ ኖሮ ዛሬ ብዙዎች ከሁለት ቋንቋ በላይ ወይም ቢያንስ ሁለት ቋንቋ የመናገር ክህሎት ማዳበር ይችሉ ነበር። ከ178 የአለም አገራት ውስጥ 101 አገራት በሕገ መንግስታቸው ውስጥ ከአንድ በላይ ቋንቋዎችን እንደ ብሔራዊ ቋንቋ እውቅና ሰጥተው ይገለገሉባቸዋል። ሌሎች ቋንቋዎቻቸውን ደግሞ በየሚነገሩበት ሥፍራ ወይም ክልል ውስጥ የሥራ ቋንቋ ሆነው እንዲያገለግሉ ፈቅደዋል።
እኔ የምኖርባት እና የ11.4 ሚሊዮን ሕዝብ መኖሪያ የሆነቸው ትንሿ ቤልጂየም ሦስት ብሔራዊ ቋንቋዎች አሏት። ወደ አፍሪቃም ወረድ ያልን እንደሆነ አብዛኛዎቹ የአፍሪቃ አገራት ሁለት እና ከዚያ በላይ ቋንቋዎችን እንደ ብሔራዊ ቋንቋ እውቅና ይሰጣሉ። ለምሳሌ ደቡብ አፍሪቃን የተመለከትን እንደሆነ አሥራ አንድ ቋንቋዎችን ብሄራዊ ቋንቋ አድርጋና እውቅና ሰጥታ የቀሩት ቋንቋዎች ደግሞ በክልል ደረጃ የሥራ ቋንቋ እንዲሆኑ አድርጋለች። አንድ ቋንቋ ብቻ ተናጋሪ ከሆኑ አገሮች በስተቀር አብዛኛዎቹ የብዙ ቋንቋ ተናጋሪ ሕዝብ ያላቸው አገሮች በርካታ ሕዝብ የሚጠቀምባቸውን ቋንቋዎች በብሔራዊ ደረጃ እውቅና በመስጠት የመንግቱ ዋና መገልገያ ሲያደርጉ የቀሩትን ቋንቋዎች ደግሞ በሚነገሩባቸው አካባቢዎች ሥራ ላይ እንዲውሉ ሁኔታዎችን በማመቻቸው ለቋንቋዎቹ መበልጸግ ምቹ ሁኔታዎች ይመቻቻሉ።
ወደ አገራችን ሁኔታ ስመለስ  የዛሬዎቹ ከቋንቋ ጋር ተያይዘው የሚነሱት መነታረኪያ ሃሳቦች ሕገ መንግስቱ ሲረቀቅ ምላሽ ሊያገኙ ይገባቸው የነበሩ ናቸው። ሁለት እና ከሁለት በላይ ቋንቋዎችን እንደ ብሔራዊ ቋንቋ መጠቀም ለቋንቋዎቹ መበልጸግ ከሚፈጥረው ሙቹ ሁኔታ ባሻገር በሕዝቦች መካከል ቅርርብን በመፍጠርም ሆነ የዜጎችን ተንቀሳቅሶ እንደልብ የመስራት እድልን በማስፋት እረገድ ትልቅ ጠቀሜታ አለው።
ኢትዮጵያ ውስጥ አማርኛን ጨምሮ ቢያንስ ኦሮሚኛን ከተቻለም ትግሪኛን እና ሱማሊኛን የጨመረ አራት ብሔራዊ ቋንቋ ቢኖር ማንን ይጎዳል? የእነዚህ አራት ቋንቋዎች በብሔራዊ ደረጃ እንደ የፌደራል መንግስቱ የሥራ ቋንቋ መሆን ከቋንቋዎቹ እድገት በተጨማሪ ሁለት ጠቀሜታዎች ይኖሩታል፤
+ የኦሮሚኛ ቋንቋ ብዙ ተናጋሪ ሕዝብ ስላለው ብቻ ሳይሆን ተናጋሪው ሕዝብ የሰፈረበት ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ አብዛኛውን የአገሪቱን ክልሎች የሚያዋስን ስፍራ ስለሆነ ኦሮሞ ያልሆኑ የአገሪቷ ዜጎች ቋንቋውን በቀላሉ ለመማር እና በሚኖራቸው ኢኮኖሚያዊና እና ማህበራዊ መስተጋብሮች በቀላሉ ሊገለገሉበት እንዲችሉ እድል ይፈጥራል። ይህም በሕዝቦች መካከል መቀራረብን ይፈጥራል። ቋንቋውም ይበልጽጋል።
+ ትግርኛ እና ሱማሊኛን የወሰድን እንደሆነ ደግሞ ከኢትዮጵያ ውጪም ባሉ ሁለት ጎረቤት አገሮች፤ በኤርትሪያ እና በሶማሊያ የሚነገሩ ቋንቋዎች ናቸው። ሁለቱም አገሮች ደግሞ የወደብ ባለቤቶች ናቸው። የራሷን ወደብ አስረክባ አንገቷን ብቅ የምታደርግበትን የአለም አቀፉ መስኮት የጠረቀመች አገር ወደብ ካላቸው ከሁለቱ አገሮች ጋር በቋንቋ ጭምር የምታደርገው ሰፊ ቁርኝት ለንግድ እንቅስቃሴም ሆነ ለአካባቢው ሕዝብ ውህደት ሰፊ እድሎችን ያመቻቻል።
ከዚህ በተጨማሪ ግን ጉዳዩ ሕገ መንግስታዊ መሻሻልንም የሚጠይቅ ስለሆነ ቋንቋን፣ የክልል ጥያቄን እና የአንዲስ አበባን ባለቤትነት ጉዳይ አብሮ በጥንቃቄ ማየት ያስፈልጋል።
፩/ ሕገ መንግስቱ እና ቋንቋ 
ሕገ መንግስቱ እንዳይነካብን እያሉ ያዙኝ ልቀቁኝ የሚሉ ቡድኖች መልሰው ሕገ መንግስቱን የሚጥስ ወይም የሕገ መንግስቱን መሻሻል የግድ የሚሉ ጥያቄዎችን ሲያነሱ ሳይ ይገርመኛል። በሕገ መንግስቱ አንቀጽ ፭ ንዑስ አንቀጽ ፪ ላይ በግልጽ እንደተደነገገው የአገሪቱ ብሔራዊ ቋንቋ አማርኛ ብቻ እንደሆነ ይገልጻል። ስለዚህ ኦሮሚኛን ጨምሮ ሌሎች ቋንቋዎችን ብሔራዊ ቋንቋ ለማድረግ የመጀመሪያው እርምጃ ሕገ መንግስትቱን ማሻሻል ነው።
፪/ ሕገ መንግስቱ እና የክልል ጥያቄ
በተመሳሳይ መልኩም የክልል ጥያቄ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 47 ንዑስ አንቀስ ሁለት ላይ በግልጽ ተደንግጓል። ይሁንና በንዑስ አንቀጽ አንድ ላይ ደግሞ እውቅና የተሰጣቸውን ክልሎች በስም ዘርዝሮ ያስቀምጣል። ሕገ መንግስቱ በግልጽ ያላስቀመጥው አንድ ዋና ፍሬ ነገር በዚህ አንቀጽ መሰረት የክልልነት ጥያቄ ያነሱ የህብረተሰብ ክፍሎች ጥያቄያቸው ምላሽ ቢያገኝ እና የክልልነት ስያሜ ቢያገኙ በሕገ መንግስቱ ውስጥ ቀድመው እንደተዘረዘሩት ዘጠኝ ክልሎች ስማቸው መካተት የለበትም ወይ? በሕገ መንግስቱ ውስጥ ስማቸው ባይጠቀስም ክልል ሆነው መቀጠል ይችላሉ ወይ? እንደዛ ከሆነ በሕገ መንግስቱ ላይ የክልሎችን ስም መዘርዝር ለምን አስፈለገ? ወይስ ክልሎች በተጨመሩ ቁጥር ይህ የሕገ መንግስት አንቀጽ ማሻሻያ ይደረግበታል? ለምሳሌ የሲዳማ የክልል ጥያቄ ነገ ምላሽ ቢያገኝ እና ሲዳማ ክልል ብትሆን በሕገ መንግስቱ ውስጥ እንደ አሥረኛ ክልል ስሟ መጠቀስ የለበትም ወይ? ያ ከሆነ ወደ ሕገ መንግስት ማሻሻል ቅድሚያ መኬድ አለበት ወይስ ምን ሊደረግ ነው? ሕገ መንግስቱ ይህን ሁኔታ በተመለከተ የሚያስቀምጠው ግልጽ ነገር የለም።
፫/ ሕገ መንግስቱ እና የአዲስ አበባ ባለቤትነት ጥያቄ
እንዲሁም የሕገ መንግስቱ አንቀጽ 49 ላይም እንዲሁ በግልጽ እንደተቀመጠው አዲስ አበባ የፌደራሉ መንግስት ዋና መቀመጫ፣ እራሷን በራሷ የምታስተዳድር እና የከተማዋም መስተዳድር ተጠሪነቱ ለፌደራሉ ምክር ቤት ብቻ እንደሆነ በግልጽ ይደነጋል። ይህን ድንጋጌ በሚጥስ መልኩ ከወራቶች በፊት ኦዴፓ በደብዳቤ በአዲስ አበባ ላይ ያለውን የባለቤትነት ጥያቄ በድፍረት አቅርቧል። እንግዲህ አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል ከሆነች መስተዳድሩም ተጠሪነቱ ለክልሉ ሊሆን ነው ማለት ነው። ኦዴፓ በአንድ መልኩ ይህ ሕገ መንግስት ይነካና እንተያያታለን እያለ ይፎክራል፤ በሌላ መልኩ ደግሞ ሕገ መንግስቱን የሚጥስ እርምጃ በሰነድ አስደግፎ እና አልፎ አልፎም በተግባር በተደገፉ እንቅስቃሴዎች ያደርጋል። ይህ አይነቱ ኢ ሕገ መንግስታዊ አካሄድ በራሱ በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ውስጥ ተቀባይነት እንደሌለው ሌሎቹ አባል ድርጅቶች በወቅቱ ሁኔታውን ተቃውመዋል። ይሁን እና ሕገ መንግስቱ ሳይሻሻል የአዲስ አበባን ህልውና ጥያቄ ውስጥ የሚከት እንቅስቃሴ በመሪ ድርጅቱ በኦዴፓ በኩል መታየቱ አዲስ አበባን ሌላ የንትርክ አጀንዳ እንድትሆን አድርጓታል።
ማጠቃለያ
ለውጡ ብዙ ተስፋዎችን እንዳጫረው ሁሉ ከባድ ስጋትንም በአገር አንድነት እና ሰላም ላይ ጋርጧል። በርካታዎቹ አደጋዎች በለውጡ ላይ ቅሬታ ወይም እነሱ በቀደዱት ቱቦ አለመፍሰሱ ያበሳጫቸው ሰዎች የፈጠሩት ቢሆንም ባልተናነሰ ሁኔታም ለውጡን ይመራሉ የተባሉት ሰዎችም አደጋዎቹን በማባባስ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው። ዛሬ ብዙ ፈተናዎች ከፊታችን ተደቅነዋል። አንዳንዱ ችግር ጊዜ የሚሰጥ ቢሆንም በአግባቡ መመለስን ይጠይቃል። አንዳንዱ ችግር ግን ጊዜ ከተሰጠው አገር ሊያሳጣን ወይም ወደ ኋላ ሊመልሰን ሁሉ ይችላል። ወደ ኋላ ሊመልሱን ከሚችሉት አደጋዎች መካከል አንዱ እና ዋነኛው አብጦ እና አፍጦ የወጣው የግለሰቦች እና የአንዳንድ ቡድኖች አንባገነናዊነት እና ከሕግ በላይ ሆኖ የመታየት አዝማሚያ ነው። መንግስት እነዚህን አካላት ወደ ሕግ መስመር በጊዜ እንዲሰተሩ ካላደረገ ፖሊሲ አውጥቶ ማስፈጸም እንኳን የማይችልበት አደጋ ከፊቱ እየተጋረጠ ይመጣል።
የትምህርት ፍኖተ ካርታ በፌደራል መንግስት ደረጃ ጸድቆ የወጣ መሆኑ በተነገረ ማግስት  በሚኒስትር መስሪያቤቱ እና በፌደራል መንግስት ላይ ዛቻ እና ማስፈራሪያ በግልጽ ተሰንዝሯል። አቶ ጃዋር በትላንትናው እለት በራሱ ሚዲያ ላይ በሰጠው መግለጫ ይህን የትምህርት ፖሊሲ መንግስት በመስከረም ወር ለመተግበር ከተነሳ ይች አገር ወደ መበታተን ትሄዳለች ብሎ አስጠንቅቋል። ‘እቅዱን ያጠኑት ሰዎች የአገሪቱን ፖለቲካ የማይመጥኑ፣ ድብቅ የፖለቲካ ተልዕኮ ያላቸው እና ወደ አንድ ወገን ያደሉ ናቸው’ በማለትም አቶ ጃዋር የፌዴራል መንግስቱን ይከሳል። አክሎም ይህ ፖሊሲ በኦሮሚያ ክልል በምንም ተአምር ሊተገበር የማይችል መሆኑን እና ይህን እንሞክራለን ካሉም የትምህርት ቢሮም ሆነ የፌደራሉ መንግስት ውርደት ሊገጥማቸው ንደሚችል በዛቻ መልክ አስጠንቅቋል።
አንዳንድ ጥያቄዎችን አንስቼ ጽሁፌን ልደምድም፤
፩ኛ/ የፌደራሉ መንግስትም ሆነ የትምህርት ሚንስቴት ይህን ብሄራዊ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ሲቀርጽ ክልሎችን አላማከረም ወይ? ከሕዝብ እና ከምሁራን ጋር አልተመካከረም ወይ? ካልሆነ ለምን?
፪ኛ/ የትምህርት ፍኖተ ካርታው በቂ ውይይት ተካሂዶበት እና ምሁራን መክረውበት የወጣ ከሆነ አንድ ግለሰብ ወይም ቡድን ተነስቶ መቃወም ቢችልም ከተተገበረ ደም እንፋሰሳለን ብሎ በአደባባይ መደንፋት እና ተማሪዎች ትምህርት ሊጀምሩ ሳምንታት በቀሩበት በዚህ ጊዜ ውስጥ ይህ አይነት ጥሪ ማካሄድ ሌላ አመጽ እና ግጭትን አይጋብዝም ወይ?
፫/ የመንግስትን ስህተት ማረም እና መንግስትን በአግባቡ መሞገት የሚቻልበት ሰፊ እድል ካለ ወደ አመጽ እና ግጭት ቅስቀሳ ማምራት ለምን አስፈለገ? ይሔው ግለሰብ የሲዳማ ወጣቶችን ለወንጀል እና ለአመጽ በአደባባይ ጥሪ አድርጎ በልቡዝ ከሃምሳ ሰዎች በላይ ሕይወት አልፏል፤ ቀላል ግምት የማይሰጠው የሕዝብ ንብረት የወደመበትንም ግጭት አስተናግደናል።
በቸር እንሰንብት!
Filed in: Amharic