>

 - ፖለቲካ እስስት ነው፤ ይለዋወጣል በሃይማኖት የሚኖር ሕዝብና እግዚአብሔር ግን ያው ነው!(ብፁእ አቡነ አረጋዊ/ዶር) 

ቤተ ክርስቲያናችን ማንም እንዳያወርዳት እግዚአብሔር ስሟን ከፍ አድርጎ  የጻፈላት ነች!!!
ብፁእ አቡነ አረጋዊ/ዶር/ 
* ፖለቲካ እስስት ነው፤ ይለዋወጣል በሃይማኖት የሚኖር ሕዝብና እግዚአብሔር ግን ያው ነው!!!
 
ብፁእ አቡነ አረጋዊ/ዶር/ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የውጪ ጉዳይ ኃላፊ ሊቀጳጳስ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለኢ.ኦ.ተ.ቤ ቴሌቪዥን መልአክት አስተላለፉ፡፡ ብፁዕነታቸው ከቴሌቪዥን ጣቢያው ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ የሚከተሉትን ጉልህ ነጥቦች አንሥተዋል፡፡
‹‹እንኳን ቤተክርስቲያን ተቃጥሎ ዐፀዱ እንኳን ጫፉ ከተነካ ምእመናን ምን እንደሚሰማቸው እናውቃለን፡፡››
‹‹መቼም ቢሆን ኦርቶዶክሳውያን ልናፍር አይገባም፤ ቤተ ክርስቲያናችን ማንም እንዳያወርዳት እግዚአብሔር ከፍ ባለ ተራራ ስሟን የጻፈላት ነች፡፡››
‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስያን እንደዚህ ዘመን የታገሰችበት ጊዜ የለም፡፡ ይህም በአንድ በኩል ውለታን ላለመርሳት ነው የተደረገላት በጎ ነገርም አለ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሀገራዊ/ሀገር/የሆነች ቤተክርስቲያን ስለሆነች እንደ ሀገር ስለምታስብ ነው፡፡ ለትውልዱ የሚተርፍ ነገርን ነው የምታስበው፡፡ ሌላው ስሜታዊ ሲሆን ስሜታዊ ልሁን ያላለችብት በዚህ ምክንያት ነው፡፡… ቤተክርስቲያን እንደ እናት ነው እያሰበች ያለችው፡፡››
‹‹አሁን ግን ሕዝባችንን ማበረታታት፣ ማጽናናት፣ መጠበቅ ግዴታ አለብን፡፡ ሕዝቡም ሳይፈራ ሳያፍር በሰላም አምላኩን ማምለክ ይኖርበታል፡፡ አባቶችም ቢሆኑ ከልጆቻቸው ጋር እስከ መጨረሻው አብረው የሚቆሙ መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ ልገልጽ እወዳለሁ፡፡››
‹‹ሰላም ከሁሉም ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር መሆኑን እናውቃለን፤ ለዚህም ስለሰላም ስንሰብክ ኖረናል፡፡ ሕዝብን ስናስታርቅ ስናቀራርብ ኖረናል፡፡››
‹‹ክብር ከእግዚአብሔር ነው፤ ሁሉም ነገር ያልፋል፤ ፖለቲካም ያልፋል፤ ፖለቲካ እስስት ነው፤ ይለዋወጣል፡፡ በሃይማኖት የሚኖር ሕዝብና እግዚአብሔር ግን ያው ነው፡፡ … ሥራ ኃላፊዎችን ዘመን ይገታቸዋል፤ ሕዝብን ግን ዘመን አይገታውም አብሮ መኖሩም ይቀጥላል፡፡ ሥልጣን ወቅታዊ ነው፤ አንድ ባለሥልጣን የሚኖረው ለተወሰነ ጊዜ ነው፡፡ ለሀገር የሚጠቅም ሠርቶ ማለፍ ግን ለሁሉም ይበጃል፡፡››
ቤተክርስቲያናችን የአንድ አካባቢ ቤተክርስቲያን አይደለችም፤ በሁሉም የዓለም ክፍል ያለች ነች፤ ቤተክርስቲያናችን እኮ! በኢየሩሳሌምም ርስት ያላት ቤተክርስቲያን ነች፤ ይህንን እውነት መደበቅ የሚችል ማንም የለም እኛ ብንፈራ እንኳን እውነት ደፋር ነው፡፡ መደበቅ አይችልም፡፡ ኦርቶዶክሳዊ እምነት በዚህች ሀገር ያለ ብቻ አድርጎም ማሰብ ሞኝነት ነው፡፡ ሌሎች ቢሰሙን ይታዘቡናል፡፡››
‹‹በኦርቶዶክሳውያን ዘንድ የዘር ልዩነት የለም፡፡››
Filed in: Amharic