>
5:17 pm - Sunday July 3, 2022

" ወደር የሌለውን ጀግና ወታደራዊ ሜዳሊያ ተሸላሚው ብርጋዲየር ጄኔራል ተስፋዬ ኃብተማርያም!!!

” ወደር የሌለውን ጀግና ወታደራዊ ሜዳሊያ ተሸላሚው ብርጋዲየር ጄኔራል ተስፋዬ ኃብተማርያም!!!
ፍሬሰናይ ከበደ
ብርጋዲየር ጄኔራል ተስፋዬ ኃብተማርያም ( በኢትዮጵያ የጦር ኃይሎች ታሪክ፡ ወደር የሌለው የጀግና ሜዳሊያ ከተሸለሙት ከሁለቱ ትክክለኛው የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች  አንዱ የኢትዮጵያ ጀግና  ናቸው።) ሌላኛው ወደር የሌለው ዋናውን የኢትዮጵያ ጀግና ሜዳሊያ ተሸላሚ ደግሞ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የጦር አይሮፕላን አብራሪው ” ብርጋዲየር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ናቸው “
ብርጋዲየር ጄኔራል ተስፋዬ ሃብተማርያም፡ የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ካፈሩዋቸው ወደር የሌለው የጀግና ሜዳይ ከተሸለሙት ሁለቱ ጄኔራሎች አንዱ ናቸው። የተወለዱት በቻኃ ወረዳ ሲሆን የጀግናው ኢትዮጵያ አየርወለድ ኮማንዶ አዛዥና አሰልጣኝ ናቸው። የወታደራዊ ሳይንስና የመኮንንነት የ 4 ዓመት ወታደራዊ ሳይንስና የአካዳሚ ትምህርታቸውን የአጠናቀቁት በስመጥሩው የምርጥ መኮንኖች ማፍሪያ ትምህርት ቤት በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጦር አካዳሚ ነው።
 የአመራርና የውጊያ ብቃታቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁትና ያነበብኩት በኢትዮጵያ የባሕር ኃይል የአገልግሎት ዘመን፡ በሁለት መጽሃፎች ማለትም ” የናቅፋው ደብዳቤ ” እና የጀግናው ገድል” ከተባሉት መጽሃፎች ነበር። በወሬ ከሰማሁት ይልቅ በገስጥ ተጫኔ ከተጻፈው መጽሃፍ ” የናቅፋው ደብዳቤ ” በሚል ርእስ መጽሃፍ ላይ ነው።
በዚያን ወቅት ለኒህ ጄኔራልና አብረዋቸው ለተዋጉት የጀግናው አየር ወለድ ኮማንዶ ክፍለጦር ወታደሮች ታሪኩን ያነበቡ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል አባላት ለጦር ኃይሎች ፕሮግራም የወታደራዊ አክብሮትና ሠላምታ እንዲደርስ መደረጉ ምንጊዜም አይረሳኝም።
  91 የሚሆኑ የአየር ወለድ አባላትን ናቅፋ ለነበረው የ15ኛ ሻለቃ ረዳት ለመሆን በጦርነት ወረዳው ላይ በዓለም ተደርጎ በማይታወቅ በጣም ከፍታ ካለው ርቀት በጄኔራል ተስፋዬ መሪነት ከአይሮፕላን በፓራሹት ወርደው፡ የጠላት ሻቢያን ጦር ለሰባት (7) ወር ተከበው ሲያርበደብዱ፡ ቀለብ፤ ጥይት፤ አስፈላጊ ቁሳቁስ በአየር ፓራሹት(ዣንጥላ) እየተጣለላቸው፡ ከአየር የሚወረወረው ንብረት ግማሹ ወደጠላት ወረዳ በንፋስ ኃይል እየሄደባቸው በዓለም ላይ ተደርጎ የማይታወቅ የጀግንነት ተጋድሎ ማድረጋቸው በመጽሃፉ እያንዳንዱ የዘመቻ ተጋድሎ ተጽፎ አንብበናል፤  እያንዳንድዋ ቀን ያለ ውጊያ የተዋለበት አለመኖሩና ከጠላት ኃይል ጋር ያልተመጣጠነ ሁኔታ ላይ አመራራቸው፤ ጥንካሬያቸውና ከዘመቻ በፊት በበቂ ስልጠናና ወታደራዊ ትምህርት በአመራር ብቃት የተመረቁ የኮማንዶ አየርወለድ አዛዥ መሆናቸውን በተግባር አሳይተዋል። የሚገርመው ነገር፡፡በሰባተኛው ወር ላይ፡ ሻቢያ ያለ የሌለውን ኃይል ተጠቅሞ ከፍተኛ ማጥቃት በአየር ወለድና 15ኛ ሻለቃ ምሽግ ላይ ከፈተ።
የነበሩበት የኃይል ሚዛን ሲሰላ በጦር መሳሪያም ሆነ በሰው ኃይል ብዛት፡ የማይመጣጠን ከመሆኑም በላይ ከአየር ላይ ወርደው በነበረበት ወቅት ወዲያውኑ ማጥቃት አድርገው በአካባቢው ላይ የበላይነት ነበራቸው። ሆኖም ጠላት ሻቢያ በጎረቤት ሱዳን በኩል በአረቦች ረዳትነት እንደልብ የጦር መሳሪያ በማስገባት የበላይነት ነበረው። በዚያን ወቅት በምሥራቅ ኢትዮጵያ ሶማሊያ 750 ኪሎ ሜትር የገባበት ወቅት ነበርና ፤ ናቅፋ ለነበረው ጦር በምንም ዓየንት መልኩ ተጨማሪ ረዳት ጦር ለመላክ መንግስት ስላልቻለ ሁኔታው ከቁጥጥር ውጭ በመሆኑ ትኩረት ሁሉ ሶማሊያ ላይ በመሆኑ ከ6 ወር መራር ትግል በኋላ ባለው ወቅት ሻቢያ በሰው ኃይልም ሆነ በጦር መሳሪያ ብዛት የበላይነት ነበረውና ጥቂት በቀሩት በጀግናው የ 15ኛ ሻለቃ አዛዥ የሚመሩት ወታደሮችና በጀግናው ጄኔራል ተስፋዬ ኃ/ማርያም መሪነት የሚችሉትን ያህል ተዋግተው ያለው አማራጭ የተቃጣባቸውን ኃይለኛ የማጥቃት ዘመቻ በመልሶ ማጥቃት  በርግደው ሲጓዙ 5 ጊዜ የደፈጣ ውጊያ ተደርጎባቸው ደፈጣን በደፈጣ በመጋፈጥ በኢትዮጵያ ታሪክ ተድርጎ በማይታወቅ ጀብዱ  በታላቅ የጀግንነት ተጋድሎ ከሠራዊታችን ጋር ተቀላቅለዋል።  ጠላት ሻቢያም ያንን ቦታ ሳይወድ በግዱ፡ ” ተስፋዬ በር ” ብሎ በዘለዓለም ስያሜ እንዲጠራው ሆኗል፤ ተገዷል።
ጀግናው የ15ኛ ሻለቃ አዛዥ ሻለቃ ማሞ ተምትሜ በጦርነቱ ላይ እራሳቸውን በገዛ ሽጉጣቸው አጥፍተዋል።
–ጄኔራል ተስፋዬ ኃብተማርያም በቻሃ ወረዳ መወለዳቸውና የስመጥሩው የሃረር ጦር አካዳሚ ምሩቅና ከናቅፋው የጀግንነት ውሎ በኋላ፡ የአየር ወለድ ክፍለጦርን በአዲስ መልክ በማዋቀር በተለያዩ የጦር ግምባሮች ሲዋጉና ሲያዋጉ፡ አንድም ቦታ የማፈግፈግም ሆነ የመሸነፍ ሁኔታ እንዳልገጠማቸው ፡ከተለያዩ የቀድሞ ጦር ኃይሎች ጸሃፍት እንረዳለን። ሻቢያ ባድሜና ሽራሮ ሲወር ፡ የዘመቻውን እቅድና ፕላን የመሩት እኚሁ ጂኔራል ተስፋዬ ኃብተማርያም ናቸው።
በወቅቱ ለሠሩት ማንም መኮንን አድርጎ የማያውቀው ጅግንነትና የአመራር ብቃት እንዲሁም የጠላት ሻቢያን ተደጋጋሚ የደፈጣ  ማጥቃት በልበ ሙሉ ጀግንነት ሰብረው ከ72 ጀግና ወታደሮች ጋር በመውጣታቸው የደርግ ኢትዮጵያ መንግሥት የ5 ዓመት ወታደራዊ ማዕርግ ማለትም በዚያን ወቅት ሻለቃ ነበሩና የኮሎኔል ማዕርግና በኢትዮጵያ ታሪክ ለማንም ወታደርና መኮንን ወታደር ተሸልሞ የማያውቀውን ቀደም ብሎ በሠሩት ተወዳዳሪ ባልነበረው ጀብዱ ” ወደር የሌለውን የሕብረተሰባዊት ኢትዮጵያ ጀግና ወታደራዊ ሜዳሊያ ተሸልመዋል “
ውድ ብርጋዲየር ጂነራል ተስፋዬ ሃብተማርያም የኢትዮጵያ ታላቁ ጀግና የኢትዮጵያ አምላክ እግዚአብሔር በጤና ይጠብቆት፤ ረጅም ዕድሜ ከነቤተስብዎ እንዲሰጥዎት ከልብ እመኛለሁ።
Filed in: Amharic