>
7:43 am - Wednesday December 7, 2022

ኢትዮጵያ ወዴት?  ዘረኝነት: ተረኝነትና ስርዐት አልበኝነት!!! (ሀይለገብርኤል አያሌው)

ኢትዮጵያ ወዴት? ዘረኝነት: ተረኝነትና ስርዐት አልበኝነት!!!
ሀይለገብርኤል አያሌው
የበታችነት ስነልቦና  ያደቀቃቸውና የጥላቻ ስሜት የወጠራቸው እነዚሁ በታላቁ ኦሮሞ ሕዝብ ስም የሚነግዱ ጥቂት የእናት ጡት ነካሾች ዘመኑ ከደረሰበት የግሎባላይዜሽን ከፍታ ሃገራችንና ሕዝባችንን  ወደ ጋርዯሽ ዘመን ሊያወርዱ የጥላቻ ጉድጏድ በመቆፈር ተጠምደዋል!!!
ሃገራችን የምትጏዝበት የፖለቲካ ጎዳና የት እንደሚያደርሰን ከመቼውም ግዜ በላይ እርግጠኛ መሆን ያልቻልንበት ወቅት ቢኖር እሁን ነው:: ተስፉ የተጣለበት የለውጥ ጎዞ መስመሩን ስቶ ጽንፈኞች የነገሱበት ምዕራፍ ውስጥ ከቶናል::
ኢትዮጵያችን ወዴት እየተንደረደረች እንደሆነ የሚታይ ነው:: ከታላቅ ተስፋ ወደ አስፈሪ ስጋት! ከለውጥ ወደ ነውጥ!  ከአንድነት ወደ መንደርተኝነት ::
ዲሞክራሲ ሰላምና ኢኮኖሚያዊ ለውጥን ከመገንባት  ይልቅ ወደ ውድመት ዘረፋና ማህበራዊ ቀውስ ተሸጋግሯል::
እኛነት ጠፍቶ እኔነት ነግሷል::
የጋራ ራዕይ ብርቅ የፖለቲካው ሁኔታ ውስብስብ ሆኗል:: የተረኝነት ስሜት ገኖ ልጏሙን በጥሷል::
ጠቅላይ ሚንስትሩና ካቢኔያቸው ሃገር ሊመራበት የሚገባ ፍኖተ ካርታ ግልጽ ማድረግ አልቻሉም:: ሕግና ስርዐትን የማስከበር አቅም አጥተዋል አለያም ሁን ብለው ትተውታል:: አስቸኳይ መፍትሄ የሚያስፈልጋቸውን ብሄራዊ ጉዳዮች ችላ ሲሉ ተስተውሏል:; የመንግስትና የጠቅላይ ሚንስትሩ ትኩረት ተራ የገጽታ ግንባታ ላይ መሆኑ ይታያል::
በሃገር ውስጥ በሕወሃት መሪነት የትግራይ ሕዝብን ከአማራው ጋር ወደ ለየለት ጦርነት ለማስገባት ዝግጅቱን ጨርሷል:: የጥላቻና ተከበናል ፕሮፓጋንዳው በስፋት ቀጥሏል:: በኦነግ ድጋፍ የሚንቀሳቀሰው የሲዳማ እጀቶ የተባለ የሽብር ቡድን በክልልነት ጥያቄ ሽፉን ብሄር የለየ ጥቃትና ዘረፋ ፈጽሟል:: አብያተ ክርስቲያናትን አቃጥሏል:: በአዋሳ ከተማ ነዋሪዎችና በደቡብ ሕዝብ ላይ አስፈሪ ስጋት ደቅኗል::
ይህን የመሰለ ሃገር አውዳሚ ውጥረት በሚቻለውና በማንኛውም  አቅም አስቀድሞ ማስወገድ የነበረበት መንግስት ጉዳዩን በእርቀት ከማየት ውጪ ምንም ሲያደርግ አይታይም::ሃገሪቷ ይህን መሰል አደጋ ተሸክማ በምትቃትትበት ወቅት  “የእራሷ አሮባት የሰው ታማስላላች” እንዲሉ ጠቅላያችን  አንዴ አስመራ ሌላ ግዜ ካርቱም የሱዳን ተቃዋሚዎች አደራዳሪ መሆንን ቅድሚያ ሰጥተዋል::
በባህር ዳር በአማራ ክልል መሪዎች እና በአዲስ አበባ የመከላከያ ኢታማጆር ሹሙ ላይ የተፈጸመው ግድያ የበዛ  ግልጽነት ይጎለዋል :: ይህም በፈጠረው ክፍተት ጠቅላይ ሚንስትሩንና ቡድናቸው ሕዝቡ እንዲጠራጠር በር ከፍቷል:: በመሪዎቹ ላይ የተካሄደው ግድያ በነጻና ገለልተኛ አካል ምርመራ ተካሂዶ የጋራ መግባባት ላይ እንዳይድረስ መንግስት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል::
ይባስ ብሎም አደጋውን አስታኮ በአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ አባላትና አመራሮች : በጋዜጠኞችና : በአዲስ አበባ ም/ቤት (ባልደራስ) አባላት ላይ እራሳቸው ጠቅላይ ሚንስትሩ በፓርላማ ያወገዙት የሽብር ሕግ : አመት ሳይሻገር መልሰው ንጽሃንን ማጥቂያ አድርገውታል:: ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ቃል ማጠፍና ተቃዋሚን በሃሰት መፈረጅን ከቀጠሉ ጥፍር ነቃይ መርማሪዎችንም ወደ ስራ ላለመመለሳቸው ምንም ዋስትና የለም ::
ለጌታቸው አሰፋ የእዮብን ትግስት ያሳየ መንግስት ሕወሃትን መንካት የፈራ ወይም ያልፈለገ አመራር:: የኦነግ አሃድ ትጥቅ አልፈታም ማለቱን 20 ባንክ  መዘረፉን አላውቅም ያለ መሪ :  አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኞች መረን የለቀቀ አካሄድን መቆጣጠር ያልቻለ ወይም ያልፈለገ መንግስት ከብዕር ውጪ ምንም የአመጽ መሳሪያ የሌላቸውን ሰላማዊ ታጋዮች በሽብር ሕግ  ማሰሩ ብዙዎችን አሳዝኗል:: በጠቅላይ ሚኒስትሩና በለውጡ ሂደት ላይ መጥፎ አሻራ አሳርፉል::
 በአንጻሩ :  ከዶር አብይ ስልጣን ማግስት ከተደበቀበት ጎሬ ብቅ ያለው በሃምሳ አመት ታሪኩ አንዲት ጀብድ መስራት ያልቻለው ያነገበው ጠመንጃ  እላዩ ላይ እስኪዝግ ቁጭ ብሎ የኖረው ጨለምተኛና ጽንፈኛው የኦነግ መንጋ ሰማይና ምድሩን ጨረቃና ከዋክብቱ ሁሉ የኔ ለኔ በሚል ስስታም የኬኛ ዘመቻ የለውጡን ተስፋ አጨንግፎ የውጥረት አየር በሃግሪቷ ላይ እንዲነግስ የራሱን ሚና ተጫውቷል::
የበታችነት ስነልቦና  ያደቀቃቸውና የጥላቻ ስሜት የወጠራቸው እነዚሁ በታላቁ ኦሮሞ ሕዝብ ስም የሚነግዱ ጥቂት የእናት ጡት ነካሾች ዘመኑ ከደረሰበት የግሎባላይዜሽን ከፍታ ሃገራችንና ሕዝባችንን  ወደ ጋርዯሽ ዘመን ሊያወርዱ የጥላቻ ጉድጏድ በመቆፈር ተጠምደዋል::
በተዛባ የወራሪ ሰፋሪና መጤ የትርክት አሮጌ ጀልባ እየቀዘፈ ወሎ ለመድረስ የፈጠነው የኬኛ ሰራዊት በዚህ ግስጋሴው በስስት ንፋስ እየተገፋ ሕንድ ውቂያኖስ ገብቶ እንዳሰምጥ ሊመከር ይገባል::
ልክ ያጣው የተረኝነት ስግብግብ አጀንዳና መረን የለሽ ጥላቻ ያሳወረው የኦሮሞ ልሂቅ : ትላንት የኦሮሞ ሕዝብ ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው ስቃይ ሲፈጽሙ ከኖሩት የሕወሃት ፋሽስቶች ጋር ዳግም ለመሰልፍ አብቅቶታል::
ሕወሃቶች ላለፉት 28 አመታት እስር ቤቱን ኦሮምኛ ተናጋሪ ያደረጉበት ሃቅ ተዘንግቶ:: ትላንት ወለጋ ውስጥ ልጇ እሬሳ ላይ እንድትቀመጥ የተደረገችው እናት ሃዘን ሳይረሳ : እግራቸው በጭካኔ ተቆርጦ : የዘር ፍሬያቸው ፈርጦና : ጥፍራቸው ተነቅሎ በስቃይ ያሉት አያሌ ግፉዐን ወገኖቻችን  ቁስል ሳይደርቅ በኦሮሞ ሕዝብ ስም የሚምሉ ምሁር ተብዬ ጨለምተኞች ሕወሃት ጫማ ስር ተመልሰው ሃገር ለማፍረስና የብሄር ግጭት ለመፍጠር መሰማራታቸው የኦሮሞ ሕዝብን ክብር እጅግ የሚያወርድና  ታሪክ ይቅር የማይለው ወንጀል ነው:;
ኢትዮጵያ የሁሉ ናት የአንዱ የግል ለሌላው የጋራ የሆነ ግዛትም ድንበርም ልዪ ተጠቃሚነትም ኖሮ አያውቅም ወደፊትም አይኖርም:: ሰሜኑም ምዕራቡም ደቡቡም ሆነ ምስራቁ የሁላችን የጋራ ሃገር እንጂ የአንዱ ወይ የሌላው አይደለም:: ጀግኖች አባቶቻችን በአራቱም ማዕዘን ድንበሯ ላይ ውድ ሕይወታቸውን የሰውት ለመንደርና ጎጣቸው ሳይሆን ለታላቋ ኢትዮጵያ ልዕልናና ለሁሉም ሕዝቧ ክብር ነው::
ኦሮሞ ኢትዮጵያዊ ነው ፤ ኢትዮጵያም የኦሮሞ ናት! ይህን ሊፍቅና ሊያስቀር የሚችል ምንም ውሃ የሚቋጥር ምክንያት የለም። የኦሮሞ ልጆች ለኢትዮጵያ የግዛት አንድነትና ለወሰኗ ክብርና ለሉዓላዊነቷ ወደር የሌለው መስዋዕትነት ሲከፍሉ ኖረዋል። በአለም የጥቁር ሕዝቦች ታሪክ ውስጥ ብቸኛ የነጻነት ባለቤት የመሆን ከፍታ ላይ የደረሰ ዜግነት ያለው ኩሩ ሕዝብም ሆኗል::
የዛሬዎቹ የበታችነት ስነልቦና የተጫናቸውና ጥላቻ የተሞሉ የታሪክ ምሁር ተብዬዎችና ፖለቲከኞች
የኦሮሞን ሕዝብ ከተሰቀለበት የክብር ሰገነት አውርደው  የክብርና የኩራት ታሪኩን ንደው የባርነትንና የተገዥነትን የሃሰት ማቅ ሊያለብሱት ይራወጣሉ:: የኦሮሞም ሆነ ሌላው ሕዝብ ችግሩና ጥያቄው ሰላም ልማት መልካም  አስተዳድርና ዲሞክራሲ እንጂ የሕዝብ ለሕዝብ ግጭት አይደለም:: አንድ እግራቸውን ውጪ ያደረጉ አክራሪ ሃይሎች በሕዝብ ሰላምና በሃገር ሕልውና ላይ እያካሄዱ ያለውን አፍራሽ እንስቃሴ ኢትዮጵያዊው ኦሮሞ በግዜ ሊታገላቸው ይገባል::
ኢትዮጵያዊ እሳቤ ዛሬ ላይ ጠንክሮ የሚወክለው ወገን አጥቷል:: ትላንት በአንጋፉ ተቃዋሚነት ትግሉን ይመሩ የነበሩት የአሮጌው ፖለቲካ ሃይሎች ሕዝቡን ክደው ለገዥዎች አድረዋል:: ሚድያውም ሲቪክ ተቋማትም ከአደባባይ ጠፍተዋል አንዳዶቹም በአድርባይነት ተሰልፈዋል:: የአደባባይ ምሁራን ይባሉ የነበሩትም አድሃሪ ሆነዋል:: አንድነትን የሚሰብኩ አብሮነትን የሚያጸኑ ኢትዮጵያዊነትን የሚመሰክሩ ጉባዔዎች ነጥፈዋል:: በተለይ በውጭ ሃገራት ጨርሶ ተዳፍኗል::
ለዚህ ነው ኢትዮጵያ ወዴት የሚል የውይይት ፎረም ያስፈለገው:: ክፍተቱን ለማጥበብ ከማሰብ ነው::
ዛሬ በሃገራችን በመሆን ላይ ያለው የተረኝነት ስሜት የጥላቻ ቅስቀሳና የተዛባ ትርክት ዝም ከተባለ ሃገር ሊያፈርስና ሕዝብ ሊያጫርስ ወደሚችል ምዕራፍ እንዳይሸጋገር መሪዎቹን ለማሳሰብ ሕዝቡን ማንቃትና ማደራጀት አስፈላጊ በመሆኑ ነው:: ጭፍን ተቃውሞም ሆነ ጭፍን ድጋፍ ከሰለጠነ ማህበረሰብ የሚጠበቅ ባለመሆኑ በእውቀት በማስረጃና በሃቅ ላይ የተመሰረተ ሃገራዊ ግንዛቤ ለመፍጠር ነው:: ይህን መሰሉን ፎረም ወደፊት በተጠናከረ ሁኔታ በተለያዩ ርዕሶች ላይ ማካሄዳችንን እንቀጥላለን::
ኢትዮጵያን እግዚያብሄር ይጠብቅልን!!
ኢትዮጵያ ወዴት?
Filed in: Amharic