>
12:19 am - Thursday December 1, 2022

የትግራይ ብሔረተኞች በአማራ ላይ ያላቸው ጥላቻ ከምን የመነጨ ነው?” (ጥናታዊ ጽሑፍ – በጌታቸው ረዳ)

የትግራይ ብሔረተኞች በአማራ ላይ ያላቸው ጥላቻ ከምን የመነጨ ነው?”
(ክፍል አንድአሰፋ ሃይሉ
 
(ጥናታዊ ጽሑፍ – በጌታቸው ረዳ)
 
ጥብቅ ቅድመ-ንባብ ማሳሰቢያ፦ 
የዚህ ጥናታዊ ፅሑፍ አቅራቢ ብዙዎቻችን በቲቪ መስኮት የምናውቀው የወያኔው ጌታቸው ረዳ አይደለም። ይሄኛው የምርምር ፅሑፍ አቅራቢ ጌታቸው ረዳ ሌላ የተከበረ ምሁር ነው። ይህ አሁን ጥናቱን የማጋራለት አስገራሚ ሰው – ይሄኛው ጌታቸው ረዳ – በእርግጥ የትግራይ ክፍለሀገር ተወላጅ ነው።
ነገር ግን ይህ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ጌታቸው ረዳ ካልተሳሳትኩ እስከ ቅርብ ግዜያት ኑሮውን በሀገረ አሜሪካን ያደረገ፣ ለዓመታት በሰብዓዊ መብት ተሟጋችነቱ የታወቀ፣ “ኢትዮጵያን ሠማይ” የተሰኘው የኢትዮጵያውያን የመወያያ  (http://ethiopiansemay.blogspot.com/) ድረገፅ አዘጋጅ፣ እና የሞረሽ ወገኔ መሥራች የተከበረ ኢትዮጵያዊ ልሂቅ ነው። እና ከዚህኛው ከወየነው (ከራያው) አቶ ጌታቸው ረዳ ጋር ስመ ሞክሼ በመሆኑ አንባቢዎቼን እንዳያምታታ በከባድ አደራ ማሳሰብ እወዳለሁ።
በመነሻዬ በማሳሰቢያዬ እንደጠቀስኩት – ይህኛው አሁን ጥናቱን በሶስት ክፍል ከፋፍዬ የማቀርብለት እውነተኛው ጌታቸው ረዳ –  ላለፉት ዓመታት – በኢትዮጵያ የተቃውሞ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ለሀቅ እና ለሀቅ ብቻ ፀንቶ በመቆም – የህወኀት/ኢህአዴግን ሥርዓት አስከፊ አምባገነናዊ ገፅታ በአደባቤይ ያጋለጠ ምሁር ነው።
ይህኛው ጌታቸው ረዳ – በተለይም ደግሞ – በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መንገድ – የዛሬ 20 ዓመታት ገደማ – የህወኀት የቀደሙ አመራሮች ከጎንደር ላይ የወልቃይት-ሑመራን መሬት እና ከወሎ ላይ የራያን መሬት ወደ ትግራይ “ክልል” በማካለል – ያደረጉትን ዓይን-ያወጣ የአደባባይ የመሬት ቅሚያ ወይም የመሬት ነጠቃ – ህገወጥነቱን እና በሁለቱ አጎራባች ሕዝቦች መካከል ጠብንና ጥላቻን ለመዝራት የታለመለትን አደገኛ ዓላማ – ለዓለም ሕዝብ በማጋለጡ – ለረዥም ዓመታት ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ዕገዳ የተጣለበት – ቢገባ ደግሞ ጥብቅ እርምጃ እንዲወሰድበት ሲታደን የኖረ – ሀቀኛ የኢትዮጵያ ልጅ ነው።
አንድ የማይረሳኝ ነገር – እንዲያውም – ከጥቂት ዓመታት በፊት – ያኛውን የህወኀት አፈቀላጤ በመሆን በሚናገራቸው ያልተገሩ ንግግሮች ባጭር ጊዜ የሕዝብ ጥላቻንና ንቀትን ያተረፈውን – የወያኔውን የህግ መምህር (እና የእውነተኛውን ጌታቸው ስመ ሞክሼ) ተጋዳላይ ጌታቸው ረዳን – ለመጀመሪያ ጊዜ በፖለቲከኛ ወንበር ላይ እንደተቀመጠ በቴሌቪዥን ጉብ ብሎ ስናየው፣ እና ኋላም የኮምኒኬሽን ሚኒስትር እስከመሆን ደርሶ ስንመለከተው፣ እንዲሁም ከዚያ በኋላ “ጌታቸው ረዳ” የሚለው የእርሱ ስም በሀገሪቱ ሁሉ የሚታወቅ እኩይ ብራንድ እንዲሆን በየአጋጣሚው በጥሩም በክፉም ስሙ በሚዲያ ፕሮሞት ሲደረግለት ስንመለከት – አንድ የማልረሳው እና አሁን ስሙን መጥቀስ የማልፈልገው ወዳጄ – የሰነዘረው ሀሳብ ነው። ያን ሀሳብ መቼም አልረሳውም።
ያ ራሱ የትግራይ ተወላጅ የሆነ ወዳጄ በወቅቱ የወያኔውን ስመ ሞክሼ ጌታቸው ረዳን በየሚዲያው መብዛት አስመልክቶ የሰነዘረልኝ ሀሳብ እንዲህ የሚል ነበረ፦ “ህወኀቶች እኮ የእውነተኛውን ጌታቸው ስመ ሞክሼ ይሄኛውን እኩዩን የመቀሌ የህግ መምህር ጌታቸው ረዳን ወደ አደባባይ ያወጡት – የዚያኛውን የእውነተኛውን ምሁር የጌታቸው ረዳን ስምና ማንነት ለማደናገርና ጨርሶ በሕዝብ ዘንድ እውነተኛ ማንነቱ እንዳይታወቅ ለማስረሳት (ወይም ለማስጠፋት) አልመው ሆነ ብለው ወደ አደባባይ ያወጡት “ኢምፖስተር” (ውሸተኛው አሳሳች ሞክሼ) ነው” ብሎ ነበረ የተነተነልኝ ያ ወዳጄ።
በወቅቱ የኛ ሀገር የህወኀት/ኢህአዴግ ሴረኞች ለዚህን ያህል ያፈጠጠ (እና ረዥም ያቀደ) የአደባባይ ሸፍጥ ያን ያህል ይተጋሉ ብዬ አስቤ ስለማላውቅ ሀሳቡን በፈገግታ ቸል ያልኩት ቢሆንም – አሁን ላይ ሳስበው ግን – በዚያ ወዳጄ አስገራሚ አርቆ አሳቢ አብርሆት እስካሁንም (ለሁልጊዜም) ደጋግሜ ስደመምበት እኖራለሁ።
ለማንኛውም ግን – አሁን በቀጥታ – ወደ ሀቀኛው ምሁር ወደ እውነተኛው ጌታቸው ረዳ የጥናት ፅሑፍ ልለፍ።
የጥናት ፅሑፉን ሙሉውን ማንበብ ለሚፈልግ አንባቢ በዚህ ፅሑፍ ግርጌ መገኛ አድራሻውን ትቼለታለሁ። በተረፈ ግን ካለው ብዛት አንፃር – በሶስት ክፍል ከፍዬ – የመጀመሪያውን አሁን አቅርቤዋለሁ። ይህን የጌታቸው ረዳን ጥልቅ ጥናት የሚያነብ ብዙ አዳዲስ ነገሮችን ያገኝበታልና ያላነበበው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ጊዜ ዝጥቶ ያንብበው። መልካም ንባብ።
የትግራይ ብሔረተኞች በአማራ ላይ ያላቸው ጥላቻ ከምን የመነጨ ነው?” (- ጥናታዊ ጽሑፍ )
በካሊፎረኒያ ስቴት በሳን ሆዘ ከተማ በሃያት ሪጀንሲ ሳንታክላራ ሆቴል በሰኔ 26/2006 (July 3/2014) በሞረሽ ወገኔ የአማራ ሲቪክ ማሕበር በተዘጋጀው ሕዝባዊ ስብሰባ በአቶ ጌታቸው ረዳ የቀረበ ጥናታዊ ጽሑፍ።
ጌታቸው ረዳ
የተከበራችሁ የመድረኩ አዘጋጆች እኔን ከእነዚህ የታወቁ ዓለም አቀፍ ምሁራን ጋር ሆኜ አገራችን በአሁኑ ሰዓት ስለ አለችበት ሁኔታ ለመነጋጋር ስለጋበዛችሁኝ፤ ምስጋናዬ የላቀ ነው። አመሰግናለሁ።
እንዲሁም እናንተ ክቡራን እና ክቡራት ኢትዮጵያዊያን ወንድሞች እና እህቶች፤ ስለ አገራችን ጉዳይ ከእኛ ጋር ለመወያየት በመምጣታችሁ እጅግ አማሰግናለሁ።
ከሁሉም አስቀድሜ አንድ ነጥብ ለማስረገጥ የምፈልገው ጉዳይ፤ በዚህ ስብሰባ በእንግድነት ስጋበዝ፤ የምሰነዝራቸው አስተያየቶች እና ትችቶች ማንም የፖለቲካ ቡድን ወይንም ድርጅት ወክዬ ሳይሆን እራሴን አንደ የኢትዮጵያን ሰማይ ድረግጽ አዘጋጅነቴ እንደ ጌታቸው ረዳ በግል የሚወክል ነው። ማንም ተቃዋሚ ወይንም ሚዲያ በምሰነዝረው አስተያየት የመከራከር የመተቸት መብቱ የተጠበቀ ነው።
ከዚህ በታች የማቀርበው ጽሑፍ ለመጀመሪያ ጊዜ በስፋት ያልተመረመረ ታሪክ በኔ በትግራያዊ ነገድ በኢትዮጵያዊ ዜጋ የተደረገ የመጀመሪያ ጥናት ስለሆነ፤ የታሪክ ምሁራን ለምርምር ሊጠቀሙበት ፈቅጃለሁ።
ይህ ካልኩኝ፤ ወደ ውይይታችን ልግባ
ከናንተው ጋር ለመወያየት መርጫቸው የነበሩ ሁለት ርዕሶች ነበሩ። ሆኖም ሁለቱን ርዕሶችን አንስቼ ለመወያየት ከጊዜ አንጻር ማብቃቃት ስላለብኝ፤ በአንደኛው ርዕስ ብቻ በማትኰር ከናንተው ጋር እወያያለሁ።
አሁን በመረጥኩት ርዕስ እና ከአዘጋጆቹ ተጠይቄ መልስ አንድሰጥበት ያዘጋጀሁትን “የትግራይ ብሔረተኞች በአማራ ላይ ያላቸው ጥላቻ ከምን የመነጨ ነው?” በሚል ጉዳይ አንስቼ ከናንተው ጋር እወያያለሁ። ትንታኔዎቼም አሁን ላለው ውዥምብር መሰረታዊ “ግንዛቤዎች” እንዲኖሩን ይረዱናል።
ወደ ዝርዝር ንግግሬ ከመግባቴ በፊት፤ አንድ ነገር ለማለት እፈልጋለሁ። የመድረኩ አዘጋጆች ቀደም ብለው እንደገለጹት የጎሳ ትውልዴ ትግራይ ውስጥ ነው። ወያኔ የኔን ፖለቲካዊ ክርክር ለማፍረስ እንዲመቸው ማንነቴን እያወቀም ቢሆን “ትግሬ” አይደለም፡ በማለት የኔን ትግሬነት ለመንጠቅ በተከታዮቹ በኩል በየኢንተርኔቱ ማንነቴን ለመንጠቅ ያልጐለጐለው የሃሰት ፕሮፖጋንዳ የለም።
ትግሬ ሆኖ ከአማራ ወይንም ከአገው ‘ነገድ’ ያልተዋለደ ወይንም ከሌሎች ነገዶች ያልተዋለደ ኢትዮጵያዊ የለም። ሁላችንም ተሳስረናል። በተለይም ትግሬ ሆኖ የገዛ ስሙ ወይንም የወላጆቹ እና የአያቶቹ ወይንም የቅድመ አያቶቹ ስም “የአማራ ስም” የሌለው ትግሬ በምንም መልኩ አይገኝም።
ይህ ብቻ ሳይሆን አንዳንድ ብሔረተኛ መሳፍንቶች ‘አማርኛም’ የትግሬዎች አይደለም በማለት አፄ ዮሐንስንም ጭምር ለማሳመን ተከራክረው “ተቀባይነት እንዳጡ’ የትግራይ ታሪክ ፀሐፊዎች ነግረውናል። የተባለው ቋንቋ በትግሬ ነገሥታቶች እና የትግሬ የጥንት ሊቃውንት ከትግርኛ ቋንቋ ይልቅ ከጥንት ጀምሮ በግዕዝ እና በአማርኛ መገናኛቸው ለምን አድርገው እንደመረጡትም ለታሪክና ለነገድ ተመራማሪዎች እተወዋለሁ።
ስለ እኔ ማንነት ይህ ካልኩኝ በኋላ። ትግሬ ሆኖ “ወያኔን የሚቃወም የለም” የሚል ወያኔዎችም ሆኑ ወያኔንም በሚቃወሙ ጭምር ይህ እምነት ስላለ ነው ይህንን ለመግለጽ የፈለግኩት። ትግሬዎች ለወያኔ ካለቸው ድጋፍ እና ብዛት አንፃር ስንመለከት ነገሩ እውነትነት አለው።
ለዚህም ነው፤ አንድ ታዋቂ ጸሐፊ ክርክርህ ስመለከት እውነት ከትግሬ ነው የበቀለው ስለምል “እውነት ከትግራይ ትውልድ አለህ?” ብለው በኢመይል የጠየቁኝ አንድ ታዋቂ ጸሐፊ ኣሉ፡፡ አንድ የወያኔ ብሔረተኛም ‘እውነት ትግሬ መሆንህን ታምናለህ? እንዲህ ያለ ግልጽ ትግሬ አይተን አናውቅም” በማለት ግትር እውነታየን አስገርሞታል።
የማከብረው ወዳጄ ዶ/ር አሰፋ ነጋሽም ያንተን ትግል ስመለከት “እስራላዊው ጋዜጠኛ “ገዴዎን ለቪ” ሆነህ ትታየኛለህ። ብሎኛል። ገዴዎን ለቪ ለማታውቁት ሰዎች፤ ገዴዎን ለቪ እስራኤላዊ ነው። እስራኤል የፓለስታይን ስቃይ ማቆም አለባት ብሎ የእስራልን ወንጀል ከሚያጋልጡ ታዋቂ ጋዜጠኛ እና ሰብአዊ ጠበቃ ነው።
ወያኔዎች እኔን እና መሰል ጓደኞቼን ትግሬነታቸው የከዱ ብለው “ሽዋውያን ተጋሩ” እያሉ አንደሚጠሩን ሁሉ በእስራሎችም ገዴዎንን “ሓማሳዊ ፕሮፓጋንዲሰት” (propagandist for the Hamas) የሚል ቅጥያ ተሰጥቶታል። አንዳንድ ወገኖች ደግሞ ገዴዎንን “እስራላዊ አርበኛ” ብለው ይጠሩታል። በዚህም የ2012 የኢንተርናሺናል ሚዲያ አዋርድ ተሸላሚ ሆኗል።
ትግሬዎች የጐንደሬዎች እና የወሎዎችን መሬት በጉልበት ቀምተው መኖርያቸው አንዳደረጉት ሁሉ፤ ገዴዎንም እስራሎችን የፓለስቲኒያን ‘ዌስት ባንክ’ መሬት ቀምተው ለሰፋሪ እስራሎች በመስጠታቸው፤ እዛው እየሰፈሩ ያሉት የእስራል ሰፋሪዎችም፤ “society’s of Moral Blindness” “የሞራል እውራን ማሕበረሰብ” ሲላቸው፤ የፓለስቲኒያን መሬት ነጥቆ የመኖርያ ህንፃ በመገንባት ለእስራሎች መኖሪያ ያደረገው የንጥቂያ ወንጀልም፤ the most criminal enterprise in ( Israel’s ) history ብሎታል።
በዚህ ምክንያት ገዴዎን ለቪ ከእስራል ወገኖቹ ብዙ የዘለፋ እና የስም ማጥፋት ዘመቻ ተካሂዶበታል። ብዙ መገለልም ደርሶበታል።
ወደ እኛው ታሪክ ስመልሳችሁ ደግሞ ብዙ ገዴዎኖች ባንኖርም፤ ወያኔን የምንቃወም ትግሬዎች ጥቂት መሆናችን እርግጥ ነው (ብዙ የቀራቸው መንገድ ቢኖርም አሁን አሁን የኔን ኮቴ ተከትለው የመጡ ጥቂቶች ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል።) እየተሰደብኩም ሆነ ከሕብረተሰቡ አንድነጠል እየተደረገም ቢሆን እዚህ ድረስ ተጉዤ አሁን በርካታ ተከታዮች በማፍራቴ ኩራት ይሰማኛል።
ወዳጄ ገብረመድህን እንዳለው “ባንተ ኮቴ ተከትለን እዚህ አንድንደርስ ያደረግከው የትግል አርአያ በትግራይ/የኢትዮጵያ የታሪክ መዝገብ ለወደፊቱ ይጻፋል።” ብሎ የጻፈልኝ የግል ደብዳቤ ሳስታውስ በትግሉ እንድቀጥል አበራታች ሆኖኛል።
ወያኔ ትግራይ በ1983 ዓ.ም ስልጣን ከያዘ በሗላ፤ ጥቃቱ ያነጣጠረው “እንደ ሕብረተሰብ” በአማራ ሕብረተሰብ ላይ እና “እንደ አገር” በኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠረ አንደሆነ ሃቅ ነው። በአማራ ላይ የደረሰው ጥቃት እዚህ ያሉ ክቡራን ሊቃውንቶች ስለገለጹት ወደ ዝርዝር ጥቃቱ አልገባም። ነገር ግን የትግራይ ብሔረተኞች በዚህ ሕብረተሰብ ላይ ጥቃቱን ለማነጣጠር ያነሳሳቸው ምክንያት ምንድ ነው? የሚለው ግን ለማብራራት እሞክራለሁ።
የትግራይ ብሔረተኞች የአማራ ጥላቻቸው ከሌሎች ጎሳዎች ይልቅ ለምንድነው የበረታው? የሚለው መመለስ አለብኝ? ይህ ብቻ ሳይሆን “የትግራይ ብሔረተኛ ስሜት” መመንጨት የጀመረው መቸ ነው? የሚለውም አብረን ከመለስን ለጥላቻው መንስኤ ምዕራፉ ከየት አንደጀመረ ለመረዳት ይረዳናል።
/ክፍል ሁለት … ይጥላል።/
ሙሉ የጥናት ጽሑፉን ከድረገፅ ላይ ለማንበብ ለምትሹ፥ በሚከተለው አድራሻ ይገኛል፦
የጥናት ጽሑፉን በpdf ለማግኘት ለምትሹ፥ በቀጣዩ አድራሻ ይገኛል፦
ለአሳሳቹ መምህር ሳይሆን – ለእውነተኛው ምሁር ጌታቸው ረዳ – አሁንና በሚቀጥሉት ሁለት ክፍሎች ለማቀርበው የጥናት ፅሑፉ እና ስለ ሀቅ ሲል ለተላበሰው የሕሊና ብርታት የከበረ ምስጋናዬንና አድናቆቴን በአክብሮት አቀርባለሁ።
ክፍል ሁለት ይቀጥላል።
እስከዚያው ቸር ሰንብቱልኝ።
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ።
Filed in: Amharic