>
5:13 pm - Saturday April 19, 7225

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን እንኳን ጥቂት ብሄርተኞች ቀርቶ ለፋሽስት ጣሊያንም አልተበገረችም!!! (አብርሀም ገብሬ)

ኢትዮጵያዊ ማንነት “የለም” ብሎ የካደው ጽንፈኛው ሃይል ቤተ-ክርስቲያኗ ላይ ተነስቷል!!!
አብርሀም ገብሬ
* የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን እንኳን ጥቂት ብሄርተኞች ቀርቶ ለፋሽስት ጣሊያንም አልተበገረችም!!!
አትጠራጠር ጦርነቱ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ላይ ነው የተከፈተው፡፡ ይሄ ጽንፈኛ ቡድን ኢትዮጵያዊ ማንነት የቆመባቸውን መሰረቶች ማናጋት፣ ከተቻለው ደግሞ የማፈራረስ ዕኩይ ተልዕኮ አንግቧል፡፡ ለዕኩይ ተልዕኮው ማስፈጸሚያነት ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ለመከፋፈልና አንጃ ለመፍጠር ነው የሚንቀሳቀሰው፡፡የኢትዮጵያ ቤተ-ክርስቲያን ትላንት በፋሽስት ኢጣሊያና በህ.ወ.ኃ.ት. ለመከፋፈል የተቃጣባትን ተልዕኮ ከሽፏል፡፡ ምንም እንኳን የማዳከም ስልቱ መጥፎ ጠባሳ ትቶ ቢያልፍም፡፡ ዛሬ ደግሞ የጎሳና የቋንቋ አጥር ሳያግዳት፣ በብዙ ፈታኝ ሁኔታዎች ተፈትና እዚህ የደረሰችው ቤተ-ክርስቲያን በጎሳ የመከፋፈል እንቅስቃሴ ነው የተጀመረው፡፡ በየቦታው ቤተክርስቲያናትን በማቃጠል፣ ምዕመኑን በማሳደድ የተጀመረው ዕኩይ እንቅስቃሴ እዚህ ደርሷል፡፡
የኢትዮጵያ ቤተ-ክርስቲያን ለምን የፅንፈኛ ብሄርተኞች ዒላማ ሆነች?
ከሁሉም በላይ የጎሰኞች ዒላማ የሆነችበት ምክንያት ኢትዮጵያውያንን በ“ስውር ስፌት” ሸምነው የገመዱ ጥልቅ የባህል ዕሴቶችን አበልጽጋ፤ ማህበረሰቡን ኮትኩታ ማሳደጓ ነው፡፡ የባህልና የቋንቋ አብዝሃነት ባለባት ኢትዮጵያ የቱንም ዓይነት ልዩነቶችን ተሻግረው ህዝቡን መገመድ የሚያስችሉ አስተሳሳሪ ማንነት ያበጃጀች በመሆኗ ነው፡፡ እሁድ ጠዋት ከሲዳማ እስከ ትግራይ፤ ከጉራጌ እስከ ጋሞ፤ከጎንደር እስከ ወለጋ፤ ከጅግጅጋ እስከ አርባ ምንጭ…ቤተ-ክርስቲያናት ብትጓዝ ቋንቋና ጸሎታቸው አንድ ነው፡፡አምላካችን ሆይ፣ የድንግል ማርያም የአስራት ሃገር የሆነችው ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ጠብቅ ነው-የወል ቋንቋቸው፡፡ ከሁሉም በላይ ግን የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ዋንኛ ምንጭ በመሆኗ ነው፡፡
የጽንፈኛ ብሄርተኞች ዓላማ ደግሞ ህዝብን ማቀራረብ ሳይሆን ማለያየት ነው፡፡ አስተሳሳሪ ዕሴቶችን ማጉላት ሳይሆን አለያይ ስንጥቆችን መፈልፈል ነው፡፡የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ደግሞ አስተሳሳሪ ማንነት አበልጽጋ ያቆየች ታላቅ ተቋም ነች፡፡ለዚህ ነው ጽንፈኛው ሃይል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን የቆመችበትን መሰረት ማናጋት ከተቻለም የማፈራረስ ዕኩይ ተልዕኮ ይዞ የሚንቀሳቀሰው፡፡ ቤተ-ክርስቲያኗን የማዳከምና የመከፋፈል ስልት መዳረሻ ግቡ ግን ቋንቋ ዘለል አስተሳሳሪ ማንነቶችን መበጣጠስ ነው፡፡
 Donald Crummey, “Priests and Politicians” በተሰኘው መጽሃፉ (በገጽ፣93)፣ ማርካኪስ ደግሞ፣ “National and Class Conflict in the Horn of Africa” በተሰኘው መጽሃፉ (በገጽ፣17)፣ ፕ/ር መሳይ ከበደ ደግሞ፣ “Survival and Modernization, Ethiopia’s Enigmatic Present: A Philosophical Discourse” በተሰኘው መጽሃፋቸው ውስጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን በመቅረጽ በኩል ያደረገቸውን ታላቅ ሚና አጽንኦት ሰጥተው ጽፈዋል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን ለማዳከም፣ የቤተ-ክርስቲያኗን አገናኝ ድልድይነት መስበር ወሳኝ መሆኑን ጽንፈኛ ሃይሎች ስለተገነዘቡ ነው፡፡
እመነኝ ይህች ቤተክርስቲያን አይደለም ለጎጠኞች ቀርቶ በመርዝ ጋዝ ኢትዮጵያውያንን እየፈጀ ለመጣው ለፋሺስት ጣሊያንም አልተበገረችም፡፡ ፋሽስቶች የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ለመከፋፈል ያላደረጉት ጥረት አልነበረም፡፡ ከአንድ የማህበረሰብ ክፍል ጋር አዛምደው ያልነዙት የፕሮፓጋንዳ ጥላቻ የለም፡፡
ይሄ ሁሉ አልሳካ ሲላቸው በየካቲት 12 በግራዚያኒ ላይ የተሞከረውን ግድያ ከከሸፈ በኋላ ፋሽስቶች ሊያጠፏት ቆርጠው ቢነሱም፣አልተሳካላቸውም፡፡ ከዚያ ይልቅ በግራዚያኒ ላይ ቦንብ የወረወሩት የእነ አብርሃ ደቦጭ…ቤተሰብ አስጠልላችኋል በሚል ከ400 በላይ የደብረ ሊባኖስ መነኮሳት በመረሸን የፈሪ በትሩን አሳርፎባታል፡፡ ቤተ-ክርስቲያናችን ግን ሳትከፋፈል ክፉው ጊዜ አልፋለች፡፡ ከአፍንጫቸው ደፍ በላይ ማየት የማይችሉና ሃላፊነት የማይሰማቸው ጽንፈኞች ትላንት በኢትዮጵያ ጠላቶች ተሞክሮ የከሸፈውን መንገድ እየሞከሩት ነው፡፡ ለዚህ ነው ጦርነቱ ከኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ብቻ ሳይሆን የሃገራቸው ጉዳይ ከሚያንገበግባቸው ዜጎች ጭምር እንጂ፡፡
Filed in: Amharic