>
5:13 pm - Friday April 19, 2368

ጋዜጠኛና ደራሲ ዳንኤል ገዛኸኝ ጤንነቱ አስጊ ደረጃ ላይ ደርሷ፤ ህይወቱን እንታደጋት!!!

ጋዜጠኛና ደራሲ ዳንኤል ገዛኸኝ ጤንነቱ አስጊ ደረጃ ላይ ደርሷ፤ ህይወቱን እንታደጋት!!!
ከሳባ ጴጥሮስ 
ብዙ ጊዜ የሚደነቁት፣የሚሞገሱት እና አንዳችም ነገር በገጠማቸው ጊዜ የምንደነግጥላቸው፣ “ከጎናችሁ አለን…አይዞዋችሁ” የምንላቸው የሚታዩትን  የአደባባይ ሰዎችን ብቻ ነው። ነገር ግን በህይወት አጋጣሚም ይሁን እዩኝ የማለት ዘዬ የሌላቸውን ያለፈ ታሪካቸው ያልተነገረላቸው የማይታዩትን ዘ-ኢንቪዝብል ማንም  የሚያስታውሳቸው የለም። ዳንኤል ዘኢንቪዝብል ከማይታዩት አንገታቸውን አቀርቅረው ከሚገኙት አንዱ ነው።
 የዳንኤል ገዛኽኝን መታመም ከሶስት ወር ተኩል ግድም ቀደም ብሎ ነው የተሰማው ። ጋዜጠኛ ዳንኤል ገዛኽኝ የሚኖረው ሳውዝ ዳኮታ ሁለተኛ ከተማ ሱፎልስ ነው። ዳንኤል በ ልዩ እና ከፍተኛ የህክምና ክትትል ስር የሚገኙ ህሙማን የሚተኙበት ክፍል ICU ውስጥ መንፈቅ ወር አሳልፎዋል። የሁለቱ ኩላሊቶቹ መጎዳት ክሮኒክ ኪድኒ ዲዝዝ፣ የስኩዋር ህመም ዲያቢትስ፣ ከፍተኛ የደም ግፊት ሀይ ብለድ ፕሬዥር፣ ሀይፐርቴንሽን፣ ኒሞኒያ የሳምባ ምች ህመም ተደማምረውበት መተንፈስ ወደ አለመቻል መድረሱን እና በመሳርያ እገዛ ይተነፍስ ነበር።
ዳንኤል ድጋፍ እንደሚያስፈልገው በማመን ከዳንኤል የነጻው ፕሬስ ወዳጆች ጋር በመምከር የጎፈንድ ሚ ዘመቻ ተደርጎ ነበር እንደታሰበው ለማሳካት ግን በታሰበው መጠን ለዳንኤል ልገሳው ሙሉ በሙሉ ግቡን ሊመታ አልቻለም። ግን ግን..በዘሃበሻ አዘጋጅ ጋዜጠኛ ሄኖክ አለማየሁ አማካኝነት 12ሺህ ዶላር ከለጋሾች ማግኘት ቢቻልም ለሚታሰበው የኩላሊት ንቅለ ተከላ kidney transplant ህክምና በቂ አልሆነም።.
ይሄ በአደገኛ የጤና እክል ውስጥ እንደሆነ የምንገልጸው ዳንኤል ገዛኽኝ ማን ነው ? እነሆ በወፍ በረር።
ዳንኤል ገዛኽኝ በነጻው ፕሬስ ውስጥ ነበር ቀደም ሲል በማህበራዊ እና በኪነ ጥበብ ላይ በሚያተኩሩ በርካታ ጋዜጣዎች ላይ በፍሪ ላንሰር ጽሁፍ አቅራቢነት ሲሰራ ቆይቶዋል። በሃረር ከተማ እና አካባቢው በስፋት በሚንቀሳቀሰው ብራና የኪነጥበባት ማዕከል የቴአትር ጥበብ ስልጠና፣ በሃረር ሬድዮ ጣቢያ ስልጠናዎችን መከታተሉ በነጻው ፕሬስ ውስጥ በጋዜጠኝነት እንዲሰራ አስተዋጽኦ ያደረገለት ሲሆን በተመሳሳይ በፍሬድሪክ ኤበርት ስቲፍቱንግ ፋውንዴሽን፣በብሪትሽ ካውንስል፣በስዊድን ኤምባሲ፣በአሜሪካ እና የጀርመን መንግስታቶች ድጋፍ በተሰጡ የመሰረታዊ ጋዜጠኝነት ስልጠናዎች የተከታተለ ሲሆን በኢትዮጵያ እና በትፍላሜ የጋዜጠኛዎች ማህበራት ተከታታይ በተለያዩ የጋዜጠኝነት ሞያ ዙርያ ትምህርት ቀስሞዋል።
የዳንኤል ገዛኽኝ የመጀመርያዋ የፓለቲካ ጋዜጣ ገመና ናት። እሱንም ለእስር ጋዜጣዋንም ለእግድ ያበቃት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን የደቡብ ጎንደር ሀገረ-ስብከት ከጊዜው ጠ/ሚ/ር ታምራት ላይኔ ጋር የተገናኘው የቡና ስርቆት የሙስና ዘገባ ነው። በዚህ ክስ ዳንኤልም ሆነ ባልደረባው የገመና ጋዜጣ ምክትል አዘጋጅ እና አሳታሚ ጋዜጠኛ ግሩም ተክለሀይማኖት በወረዳ 14 ታስረው ከክላሽን ኮቭ ሰደፍ ድብደባ እስከ ቅልብ ውሻ የመነከስ ሰቆቃ የደረሰበት ሲሆን በዚሁ ክስ ዳንኤል ወደ ትልቁ ከርቸሌ ወህኒም ተወርውሮዋል።
በማስከተል ከእስር በዋስትና ቢለቀቅም አዲስ በአዘጋጅነት ከሌሎች ባልደረባዎች ጋር ይሰራበት በነበረችው ሞገድ ጋዜጣ በተከታታይ በተከሰሰባቸው ልዩ ልዩ ክሶች የተለያዩ እስራቶች ተደራርበውበት የነበረ ሲሆን በጊዜው በኢህአዴግ ጽ/ቤት በቀረበበት ክስ በማእክላዊ ወንጀል ምርመራ ከፍተኛ ስቃይ ደርሶበታል። በሁዋላም ክሶቹ ወደ ስድስት ሲደርሱ ሀገር ጥሎ ለመውጣት በአንድ መንግስታዊ ባልሆነ ተቁዋም ድጋፍ በናይሮቢ ኬንያ በኩል ከሀገር ለመውጣት ሲሞክር በ ኢትዮጵያ ሞያሌ ጠረፍ ጋምቦ ላይ ተይዞ ለኢትዮጵያ ሚግሬሽን ተላልፎ በመሰጠቱ ከሞያሌ ሚግሬሽን ወደ ዲላ ፓሊስ አስከፊ እስር ቤት ከዚያም ዝዋይ፣ በማስከተልም በናዝሬት ምስራቅ ሸዋ ልዩ የምርመራ አንደር ግራውንድ የስቃይ ጨለማ ቤት፣ ለጥቆም ወደ አዲስ አበባ ወንጀል ምርምራ፣ በመጨረሻም ጉዳዩ የሚታየው በኦሮምያ ክልል በአርሲ ዞን ፍርድ ቤት ነው ተብሎ አዳማ እና አሰላ የተለያየ እስር ቤቶችን ከስቃይ ምርመራ ጋር አሳልፎ ያለፍርፍ በዋስትና ተለቆዋል።
ጋዜጠኛ ዳንኤል ገዛኽኝ በፕሬሱ ውስጥ እንዳይቀጥል ብዙ ወከባ የአካል እና የአይምሮ የስነ-ልቦና ቀውሶች ቢደርሱበትም ነገር ግን ከፕሬሱ ጋር በመቀጠል በሞገድ ጋዜጣ ላይ እየሰራ እስከ ምርጫ 97 /2005 ድረስ ሞያውን ሲተገብር ቢቆይም በወቅቱ ተደራርበው በተሰነዘሩበት ክሶች ከአዲስ አበባ ፓሊስ እስከ ወንጀል ምርመራ የሚገኙ እስር ቤቶች ደጃፎችን ለመርገጥ ተገዶዋል። በሁዋላም የኢትዮጵያ ነጻው ፕሬስ በይፋ በመንግስት ሲዚጋ የዳንኤል ክሶች ስምንት የደረሱ ሲሆን ለአዲስ ክስ የወንጀል ምርመራ  የፓሊስ ጥሪ ሲደርሰው በወቅቱ ከአስራ ሰባት በላይ ጋዜጠኛዎች ቃሊቲ እስር ቤት በመውረዳቸው ዳንኤል ሀገር ለቆ ለመሰደድ ተገደደ።
የዳንኤል የስደት አቅጣጫ ምርጫ የመን ሆነች ቢሆንም ግን ዳንኤል ማንነቱን ሰውሮ እንደ ስራ ፈላጊ እንደ ጎርፍ ከሚተመው በርካታ ሺህ ስደተኛ መሀከል ተቀላቅሎ ወደ ሰሜን ሶማሊያ ለመድረስ በህገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች በሚፈጽሙት እንግልት ሳቢያ በሰሜን ሶማሊያ የሰሀራ በረሀ ጠረፎች ያለ ምግብ እና ውሀ ግን በተስፋ ነፍሱን ለማትረፍ ሰባ ሁለት ሰአታት በእግሩ ተጉዞዋል። በሁዋላም ወደየመን ለመሻገር በአነስተኛዋ ከርካሳ ጀልባ ዶኒክ ከ አንድ መቶ ሀምሳ አምስት ከሚልቁ ወገኖቹ ጋር ያለ አንዳች ምግብ እና ውሀ ከሞት ጋር ቁማር እየቆመረ ግን ተስፋ ሳይቆርጥ የየመንን መሬት ረግጦዋል።
እረ ምኑ ቅጡ ይህንን እና መሰል ህይወቱን የተረከበትን መጽሀፉን ሲዋን ሲል አሳትሞ ለንባብ በማብቃት ዳንኤል ለራሱ ሰው ብርቱ ድመት ጠንካራ የተሰንኘ ተረት አስተርቶዋል።
ምን ይሄ ብቻ ያሳለፈው ስቃይ እንደ ቴዲ አፍሮ ያሉ ድንቅ የጥበብ ሰዎችን እንቅልፍ አሳጥቶ በመከራው የጥበብ ስራ አዋልዶዋል። ቴዲ አፍሮ የዳንኤልን ሲዋንን አንብቦ ስቃዩን በመንፈስ አብሮ ተሰቃይቶ”ኮርኩማ አፍሪካ” ሲል አቀንቅኖለታል።
የዳንኤል ስቃይ በሶማሊያ በረሀዎች፣በሀገሩ እስር ቤቶች፣ በስደት በየመን  አላበቃም ሞት ለሁለተኛ ጊዜ ፈትኖታል፣ ከሞት ጋር ለሁለተኛ ጊዜ ፍጥጫ ውስጥ ገብቶዋል። ተፈጥሮ የለገሰችውን አየር መተንፈስ አቅቶት ሰንብቶዋል ፣ አሁን ሆስፒታል ከቆየባቸው ጊዜያቶች የተሻለ የጤና ሁኔታ ውስጥ ቢሆንም የኩላሊት ልገሳ ለማድረግ የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት ከሰሞኑ የመጀመሪያ መጽሀፉን ትርጉም The Journey To Death ,72 Hours in Sahara Desert & 41 Hours on Red Sea በሚል ርእስ ለንባብ በማብቃት ከጥቂት ሳምንታት በሁዋላ በተለያዩ ስቴቶች በመንቀሳቀስ የBook Signing ለማካሄድ እየተዘጋጀ ነው።
ጋዜጠኛው ለሀገሩ ለከፈለው ይህ ያንስበት ይሆን ? ከዳንኤል ጋር  ስናወራ ሀላፊነት ወስደው ለኢትዮጵያ ህዝብ በማድረስ ድጋፍ እንዲጠይቁለት ሀሳብ ያቀረበላቸው ዝነኛዎች ፊት እንደነሱት ዳንኤል ነግሮኛል። ቢሆንም ግን ዳንኤል ገዛኽኝ  የሁላችንም ድጋፍ  ከመቼውም በላይ ያስፈልገዋል ።
በነገራችን ላይ የጋዜጠኛውን ውጣውረድ የሚተርከው የሲዋን ትረካ በቅርቡ በዩትዩብ ይቀርባል እንዲሁም ማቆሚያ የሌለው የጋዜጠኛው የህይወት ፈተናዎች በቅርቡ አልቃይዳን ስናቁዋርጥ በሚል ርእስ ሌላ አንድ መጽሀፍ ይዞልን እንደሚመጣ አጫውቶኛል። በቅርቡ ዳየለሲስ ይጀምራል። ፈጣሪ ጨርሶ ይማረው። ድጋፋችንም አይለየው። ሃምሳ ሎሚ ለሃምሳ ሰው ጌጥ ነውና! ልታገኙት ከፈለጋችሁ 404 610 6954 ደውሉለት።
Filed in: Amharic