>
5:13 pm - Saturday April 18, 3693

ታላቅና ታሪካዊ ሀላፊነት የወደቀበት ቅዱስ ሲኖዶስ!?! (አለማየሁ ማ.ወርቅ)

ታላቅና ታሪካዊ ሀላፊነት የወደቀበት ቅዱስ ሲኖዶስ!?!
አለማየሁ ማ.ወርቅ
የቄስ በላይ ጥያቄ ሙሉ ለሙሉ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ነው!!!
 

ይህች በደመ ክርስቶስ የታነጸች ቅድስት ስፍራ፣ ብዙ ማእበሎችን አስፈሪ ወጀቦችን አልፋ የጸናች ፤ ለትውልዱ ሁሉ በመንፈሳዊና በስጋዊ ህይወት ፤ በፈጣሪና በፍጡር መሀከል መሸጋገሪያ ድልድይ የሆነች ቤተክርስቲያን ነች።

 “በመካከላችሁ አድር ዘንድ ቤተ መቅደሴን ስራ”  ብሎ በቃሉ ያሰራትን፤ በደሙ ያነጻትን፤  አማናዊት ስፍራ ሊያጠፏት የተነሱ እነ ዮዲት ጊዲትን፣ ግራኝ መሀመድን ከዛም በየዘመኑ የተነሱ አላውያን ነገስታትን ሁሉ እንደየ አመጣጣቸው የሸኘች፤  በዘመናችንም በፕሮግራማቸው ሳይቀር ቀርጸው “እናጠፋታለን” ያሉትን ሁሉ በሞተ ስጋ በተለዩ ጊዜ በመቃብሯ እቅፍ አድርጋ ይዛ፤  በእብሪት ያበጡትንም ከእኛ በላይ ያሉትንም አንገታቸውን ሰብራ በየስርቻው እንዲወተፉ ያም ሆኖ ልጆቿ ናቸውና እንዲጠፉ ባለመፈለግ ለንስሀ እድሜ ሰጥታ  ያኖረችን እናት ቤተክርስቲያን ናት።

ክረምት ከበጋ የሚያፈራርቅ የዘመናት ባለቤት በደሙ ያነጻት እርሱ ክርስቶስ ሆኖ ሳላ በጎጥ እሳቤ ህሊናቸው የታወረ የክፋት አበጋዞች ብራና ፍቃ ቀለም በጥብጣ ፊደል አስቆጥራ ዛሬ ለሚታበዩበት ዱክትርና፣ አክቲቪስትነትና ቀሲስነት ያበቃቻቸውን ፤ ይህችን በሰማይም በምድርም የከበረች የቅዱስ ስጋውና ክቡር ደሙ የሚፈተትባትን ፤ እለት እለት ሰርክ ከነግህ ስለ አለም ሰላም ፣ ስለ ፍጥረት ሁሉ ደህንነት የምትማልድን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን  ከመመዝበር፣ ከማፍረስ እና ከማቃጠል አልፈው የጎጥ ከረጢታችን ውስጥ ከተን ይዘናት እንዙር የሚሉ የአእምሮ ድኩማኖች የሠይጣን የግብር ልጆች ተነስተውባታል።
ጥያቄያቸው በቋንቋችን ፈጣሪን እናምልክ ከሆነም ይህው ማስረጃው፦ 
የኦሮምኛ ተናጋሪ የተዋህዶ ልጆች በቋንቋቸው ፈጣሪን ማምለክ ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል። በዚህ ቪድዮ ላይ እንደምትመለከቱት ቀኖናውን በጠበቀ መልኩ መተርጎም የሚችለው የቅዳሴ ክፍል ወደ ኦሮምኛ ተተርጉሞ ምዕመናን በቋንቋቸው ፈጣሪን ሲያመሰግኑ ይታያሉ።
•°•
የኦሮምኛ ቋንቋ ሙሉ የቅዳሴ ስርዓት በድምፅ ከፈለጉ (ከሁለት ሰዓት በላይ) በሚከተለው የዩትዩብ ሊንክ ይገኛል።
የቄስ በላይ ጥያቄ የቋንቋን የመጠቀም ጥያቄ አይደለም። የቄስ በላይ ጥያቄ ከእምነታችንም ጋር የተያያዘ አይደለም። የቄስ በላይ ጥያቄ ሙሉ ለሙሉ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ነው የምንለው ለዚህ ነው።
በመሆኑም አነሳሳቸ ቤተክርስቲያኒቱን በየብሄር ና ጎጥ ከፋፍለውና አዳክመው ማጥፋት በመሆኑ ብጹአን አባቶች ልጆቻቸውን አሰልፈው ቤተክርስቲያኒቱን ከዚህ ጥፋት መታደግ ይኖርባቸዋል።
ፋሽስት ጣልያንን “እንኳን ሰው ምድሪቱም አትገዛልህ …”  ብለው ቃለ ውግዘታቸውን አስተላልፈው ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያና ስለ ሀገሪቱ አንድነት፣ ስለ ህዝቡ ነጻነት ሲባል መተኪያ የሌላት ህይወታቸውን አሳልፈው በሰጡት አቡነ ጴጥሮስ መንበር ላይ የተቀመጣችሁ ብጹአን የቅዱስ ሲኖዶሱ አባላት ይህችን በቅዱሳን ደምና አጥንት የቆመች ታላቅ ቤተክርስቲያንን ከጥፋት የመታደግ  ትልቅ እና ታሪካዊ ሀላፊነት አለባችሁ ።
የቤተክርስቲያናችን ችግር ምንጩ ቤተ መንግስት ነውና ከሀገሪቱ የፍትህ አደባባይ ርትእን ባታገኝ እንኳ አለም አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያን ነችና ጉዳዩን ወደ አለም አቀፉ ፍርድቤት ይዞ መጓዝ ያስፈልጋል ይገባልም።
Filed in: Amharic