አቻምየለህ ታምሩ
«የኦሮምያ ቤተ ክህነት» እንቅስቃሴ የነፍስ አባት ሓጂ ጃዋር መሐመድ ነው። ሓጂ ጃዋር እ.ኤ.አ. በ2016 በኦሮምኛ ባደረገው አንድ ዲስኩሩ «ከአበሻ ጋር አንድ መስጂድና ቤተ ክርስቲያን አብረን መሄድ አንፈልግም፤ የኛ የራሳችን የኦሮምያ መስጂድና ቤተ ክርስቲያን እናቋቁማለን» ብሎ ነበር። የኦሮምኛውን ንግግር በኢትዮቲዩብ ፉገራ ዜና እያለ ያቀርብ የነበረው ልጅ ተርጉሞ አቅርቦት ነበር። «የኦሮምያ ቤተ ክህነት» የማቋቋም እንቅስቃሴ የሓጂ ጃዋርን ራዕይ ከማሳካት በስተቀር ሌላ ምክንያት የለውም።
በቅርቡ የተጀመረው «የኦሮምያ ቤተ ክህነት» እንቅስቃሴ ሓጂ ጃዋር «የኦሮምያ መስጂድና ቤተ ክርስቲያን እናቋቁማለን» ሲል የተናገረው ፍኖተ ካርታ ተግባራዊ እርምጃ ነው። የተጀመረው የኦሮምያ ቤተ ክህነት» እንቅስቃሴ የበላይ ጠባቂና አንቀሳቃሽም የቤተ ክርስቲያን ራስ የሆነው እየሱስ ክርስቶስ ሳይሆን ሓጂ ጃዋር መሐመድ ራሱ ነው። እንቅስቃሴውን እመራዋለሁ የሚሉት ቀሲስ በላይ መኮንን ውሎ አዳራቸው ከሓጂ ጃዋር መሐመድ ጋር ነው። ይህ እውነት በቪዲዮና በፎቶ የተደገፈ ነው።
ቀሲስ በላይ መኮንን እውነተኛ የሃይማኖት አባት ቢሆኑ ኖሮ እሳቸው እረኛ ሆነው የሚጠብቋቸውን ክርስቲያኖችን በሜንጫ አንገታቸውን እቀላለሁ ላለ ሰው የመንፈስ ልጅ መሆን አልነበረባቸውም። ቀሲስ በላይ የሚጠብቋቸውን እረኞች በሜንጫ እቀላለሁ ካለ የክርስቲያን አራጅና በሲዳሞ ቤተክርቲያንን ያቃጠሉ ወንጀለኞችን ካሰማራ ሰው ጋር በፍቅር የወደቁ የአለማችን የመጀመሪያው «የሃይማኖት አባት» እና «የክርስቲያኖች እረኛ» ይመስሉኛል።
በኦሮምኛ ለመስበክና ለመቀደስ አዲስ ቤተ ክህነት ማቋቋም አያስፈልግም። አሁን ባለው የቤተ ክርስቲያኒቷ መዋቅርና አደረጃጀት በኦሮምኛም ሆነ በተለያዩ የኢትዮጵያና የውጭ ቋንቋዎች ሳይቀር መስበክና መቀደስ ይቻላል። በታሪክም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እንኳን በኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ቋንቋዎች በአረብኛ ቋንቋ ጭምር የሚቀድሱና የሚሰብኩ ቀሳውስትና ጳጳሳት ያፈራች ጥንታዊት ተቋም ናት። አባ ጳውሎስ ግብጽ እየሄዱ በአረብኛ ይቀድሱ ነበር። የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጃማይካ ድረስ ሄደው በእንግሊዝኛ ቋንቋ ወንጌልን ያስፋፉና የቀፈሱ ልጆች ነበሯት።
የኦነጋውያንን ትርክት ሳይመረምር የሰለቀጠው የቁቤ ትውልድ ቤተክርስቲያንና ጠባቂዎቿ የነበሩት የኢትዮጵያ ነገሥታት በኦሮምኛ እንዳይሰበክና እንዳይቀደስ የከለከለች ይመስለዋል። ከመቶ ሰላሳ ዓመታት በፊት መጽሐፍ ቅዱስ ወደ አማርኛ ቋንቋ ሳይተረጎም በኢትዮጵያ ፊደል ወደ ኦሮምኛ እንዲተረጎም ያደረጉት ዳግማዊ ምኒልክ ነበሩ። በአናሲሞስ ነሲብ ወደ ኦሮምኛ እንደተተረጎመ የሚነገርለት መጽሐፈ ቁልቁሎ ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ በአለቃ ዘነብ አስተባባሪነት ያቋቋሙሙት የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር የተረጎመው ነው። ጀርመናዊው ዮዋን ክራምፍ እንደነገረን መጽሐፍ ቅዱሱን ወደ ኦሮምኛ እንዲተረም ማኅበሩን ያቋቋሙት፣ ለማኅበሩ የወር ደመወዝ የቆተጡትና የሚያስፈልገው ሁሉ ወጪ የሸፈኑት ዳግማዊ ምኒልክ ነበሩ። ሙሉ ታሪኩን ወደፊት እመለስበታለሁ።
ባጭሩ በኦሮምኛ ቋንቋ ለማስተማር «የኦሮምያ ቤተ ክህነት» መፍጠር አያስፈልግም። አሁን እየተሰራበት ባለው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መዋቅር የሰው ኃይል እስካለ ድረስ በሁሉም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች እንዲቀደስና እንዲሰበክ ማድረግ ይቻላል። ደግሞም ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በኦሮምኛ ማስተማርና መስበክ አዲስ ነግር አይደለም። ከዳግማዊ ምኒልክ ዘመን ጀምሮ እስካሁን ድረስ በኦሮምኛ ሲሰበክና ሲዘመር ነው የኖረው። ይህ ለዘመናት ሲደረግ «የኦሮምያ ቤተ ክህነት» ማቋቋም አላስፈለገምና ወደፊትም በኦሮምኛ ማስተማርንና መስበክን አጠናክሮ ለመቀጠል «የኦሮምያ ቤተ ክህነት» ማቋቋም አያስፈልግም።