>

በወንድማማች መሐል ጠብ እየጫሩ በጉባኤ መሀል  ግን  ቢየ ነጋዳ ሰበ ተኩማ ሜቃ ጎፍታ አሜን አሜንይላሉ .. (መስከረም አበራ)

በወንድማማች መሐል ጠብ እየጫሩ በጉባኤ መሀል  ግን  ቢየ ነጋዳ ሰበ ተኩማ ሜቃ ጎፍታ አሜን አሜንይላሉ .. 
መስከረም አበራ
 *  ለካ አስመሳይ ነጋዴ ፖለቲከኛ ድብቅ የሃይማኖት መንገዶችንም ያውቃል ኽም!!
 
ክርስቲያን ወይም ሙስሊም ነኝ ያለ ሰው የዘር ፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ሲገባ ይገርመኛል፡፡የክርስትና ሃይማኖት መርሆ ክርስቲያን ነኝ ባይ ከዘር፣ከቋንቋ ልዩነት ተዋጅቶ ከማይሞተው ዘር እንደተወለደ ይናገራል፡፡በእስልምናም ዘረኝነት ጥንብ ነች የሚል አስተምሮ እንዳለ ይነገራል፡፡ግን ደግሞ በእነዚህ እምነቶች ውስጥ ከፊት ከፊት የሚሉ ሰዎች በዘር የተቧደኑበት ፓርቲ ውስጥም ኮራ ብለው ተቀምጠው ጭራሽ መሪም ይሆናሉ፡፡ በዚሁ መሪነታቸው ሳቢያም በየሚያመልኩበት ቤተ-እምነተ ከፍተኛ የመንግተ ባለስልጣናት ተብለው ፊት ወንበር ላይ “Reserve” ይደረግላቸዋል፡፡
በየሚያመልኩበት የእምነት ድርጅት ስለፈጣሪ ትዕዛዛት ሲናገሩም ወፍ ያረግፋሉ-ከዘር ከቋንቋ ተዋጅተናል፣ከማይሞተው ዘር ተወልደናል የምትለዋንም ጥቅስ ደንቀፍ ሳያደርጋቸው አውርተው ነገ ጠዋት ደግሞ በዘራቸው መስርተው ባቆሙት ፓርቲ ውስጥ “ዋናው ተቆጣጣሪ” ሆነው ይሰየማሉ፡፡ከዘራቸው ያልሆነ ሰራተኛ ሰበብ ፈልገው አባረው ከዘራቸው የሆነ ሰው ይተካሉ፤የዘሬ ሰው ካልተሾመ ኢትዮጵያ ትፍረስ ብለው ትልቅ ተፋልሞ ሲያደርጉ ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ያልፋል፤እሁድ ቀን ያን የፈረደበት ፈጣሪ በልሳን ሳይቀር “ና ውረድ” ይሉታል፤”ማራናታ ጌታ ሆይ ቶሎና” ይላሉ! እንዲህ እንዲህ እያልን ነው በደብልቀው ውቃው መንገድ የምንጓዘው!
ከፓርቲ ፅ/ቤት ቤተ-እምነት  መመላለስ የሰለቸው ደግሞ ቤተ-ዕምነቷን ራሷን በዘር ያደራጅና ከቤተ-እምነት ወደ ፓርቲ ጽ/ቤት ከመመላለስ አረፍ ብሎ በአንድ ጣራ ስር በአንድ ልቡ ሁለቱንም ያስኬዳል፡፡እንዲህ ባለው ቤተ-እምነት ውስጥ የሚመለከው የትኛው አምላክ እንደሆነ ሁሌ የምጠይቀው ጥያቄ ነው፡፡ ማንኛውም እምነት ዋነኛ መርሆዎች አሉት፡፡ እዚህ መርሆዎች የእምነቱ ዋነኛ መግቢያ በሮች ይመስሉኛል፡፡ዘረኝነቱን ያላራገፈ ሰው የክርስትናን ዋና በር ገብቷል ማለት ይከብዳል፡፡ዋናውን በር ሳያልፉ የቤት ራስ መሆን አለ? ለመሆኑ ለአለም ሁሉ የሞተውን አምላክ የእንትን ቋንቋ ተናጋሪዎች ብቻ መጥታችሁ አምልኩት ማለት እንዴት ያለ መሳከር ነው? ወይስይህ መዋቅር   የአምላክ ለውጥም አድርጎ ይሆን?ከሆነ ያስኬዳል!
ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ከግራ ይሁን ከቀኝ ጎኗ አጎንቁሎ የሚወጣ የኦሮሞ ቤተክህነት የሚባል መዋቅር ሊሰይሙ እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡ይህ በክርስትናው መንፈሳዊ አለም ፍፁም ትርጉም አልቦ እንደሆነ ከላይ አይተናል፡፡የመዋቅሩ ትርጉም አልቦነት ግን በምድራዊው መዋቅርም ይደገማል፡፡የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር ከሰማኒያ አምስት ብሄረሰቦች ውስጥ ስምንቱን ብቻ አውቃለሁ በሚለው ህገ-መንግስት አከላለል መሰረት የተዋቀር አይደለም፡፡
የኢህአዴግ አስተዳደር በምን ክልል እንደሆኑ፣ ለምንም ክልል እንዳልሆኑ በማይታወቅ ዘጠኝ የብሄረሰቦች ክልል የተዋቀረ ሲሆን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከስሙ ጀምሮ በተለየ ሁኔታ ወደ ሃምሳ ስድስት በሚደርሱ ሃገረ ስብከቶች ተከልሎ ያለ ነው፡፡ በሌላ አባባል የሃገረስብከቱን መጠን በሲኖዶሱ አባል ጳጳሳት ብዛት ማመሳከር ይቻላል፡፡እና አሁን አዲስ ሊመሰረት ያለው የኦሮሞ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃገረ ስብከት እነዚህን ሃገረስብከቶች እንዴት አድርጎ ከልሎ፣በነማን ተወክሎ(በነባሮቹ ሊሆን አይችልም) ሊመሰረት እንደሆነ እየገረመን የምንጠብቀው ነገር ነው፤ከሁሉ የሚገርመኝ በዘር የተመሰረተ ቤተ-ክርስቲያን የትኛው አምላክ እንደሚመለክበት ነው!
Filed in: Amharic