>
5:18 pm - Friday June 16, 6282

መንግሥትን የሚመራው ማነው !? (ህብር ራድዮ)

መንግሥትን የሚመራው ማነው !?
ህብር ራድዮ 
 “… ኢትዮጵያ ካልፈረሰች ኦሮሚያ አትመሰረትም!!!”
ኦቦ ዋቆ ሊበን
የሰሞኑ የአገራችን ጉዳይ አሳሳቢ ብቻ ሳይሆን አርቆ ላየ ሰው አስጨናቂ ነው። ኢትዮጵያ በዘመናት የልጆቹዋ መስዋዕትነት የተገነባ አገር ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መምጣት የፈሰሰው ደም ሁሉ ዛሬም ዋጋ ማጣቱ ግራ ያጋባል። ክህደት በሕዝብ እና አገር ላይ እየተፈጸመ ወደ አደገኛ ጎዳና እየተገባ ነው።
ቅኝ ገዢዎች ሞክረው ያልተሳካላቸውን ሕወሓት እና ኦነግ በዱላ ቅብብል አገሪቱን ሙሉ ለሙሉ በማፍረስ የተከፈለው መስዋዕትነት ተከፍሎ በየራሳቸው የትግራይ እና የኦሮሞ አገር ለመገንባት ሩጫ ይዘዋል።ስለዚህ በግራ እና በቀኝ በሰሜን እና በደቡብ ፣በምሥራቅ እና በምዕራብ በየፈለጉት ቦታ ግጭት በመቀፍቀፍ አገር ለማፍረስ መንገዱን ይዘዋል።ትላንት ታላቅ አገር እገነባለሁ ሲል የነበረው ቡድን ስልጣን ከያዘ በሁዋላ ክህደት መፈጸሙ ብቻ ሳይሆን ይህን ድብቅ ዓላማ ለማሳካት በዜጎች ሕይወት ላይ ጭምር ከመጫወት የማይመለስ መሆኑን በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተነሱትን ግጭቶች እና የጠፋውን የንጹሃን ሕይወት መለስ ብሎ ማስታወስ በቂ ነው።
 ኢትዮጵያን የትርምስ አገር በማድረግ ከዚህ ጥፋት በሁዋላ የፈለግነውን አገር እንገነባለን ብለው በአደባባይ የሚናገሩ ፖለቲከኞች ተፈጥረዋል።የለንደን የኦሮሞ የህግ ባለሙያዎች ጠርተውት የነበረው ጉባዔ ላይ አቶ ዋቆ ሊበን በግልጽ ኢትዮጵያ ካልፈረሰች ኦሮሚያ አትመሰረትም ብለዋል።እየተሄደበት ያለው መንገድ ከዚህ የራቀ አይደለም።
በወቅቱ ትንሽ ተቃውሞ ተሰማ በዚያው ተረሳ ነገር ግን ያ ዛሬ በተግባር ደረጃ በደረጃ እየተተገበረ ነው።
ኢትዮጵያን እንደ አገር እንድትቀጥል የማይፈልጉ ብዙ የውጭ ሀይሎች አሉ።በቅርቡ ከችሎት ወድቀው ሕይወታቸው ያለፈው የግብጹ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሙሐመድ ሙርሲ የአባይን ግድብ በመቃወም በጉዳዩ ላይ በቤተ መንግሥታቸው በተጠራ ውይይት ላይ በተለይ ኢትዮጵያን ለማዳከም የኦሮሞ ተቃዋሚዎችን ማገዝ እንደሚያስፈልግ በይፋ አንድ የአገሪቱ ፖለቲከኛ በግልጽ ተናግረዋል።የኦሮሞ ሕዝብ እንደ ሌላው ወገኑ ደሙን ያፈሰሰላትን አገር ጠላቶቻችን እንዳሰቡት ለማፍረስ እንደማይተባበር ትላንት ዛሬም እናምናለን።ነገር ግን የፖለቲካውን ሂደት እንመራለን የሚሉ በተለይም ተሰሚነታቸው እና ያልታወቀው የገንዘብ እና የፖለቲካ ጡንቻቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ ያበጠ ወገኖች በእርግጥም አገሪቱን በሀይማኖት እና በጎሳ ግጭት ጠምደው ለማፈራረውስ በየተገኘው አጋጣሚ ግጭት ቀስቃሽ አጀንዳዎችን ይዘው ብቅ ይላሉ። ይህን ስጋት እነዚህ ወገኖች አያደርጉም ብሎ መዘናጋት አይገባም። ይልቅ በፖለቲካ ስካር ላይ ናቸው።ሕዝብ ይህን ማስቆም።አለበት።
ከወራት በፊት አንድ የቱርክ ኩባንያ ከተፈቀደለት ተልዕኮ ውጭ ሲንቀሳቀስ ተይዞ ከአገር እንዲወጣ ተደርጉዋል።በሕወሓት የስልጣን ዘመን ለበጎ አድራጎት በሚል ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የገባ አንድ የፓኪስታን ድርጅት ሌላ ሲያስተምር ተገኝቶ እንዲወጣ ተደርጉዋል።ይህ የሚያሳየው ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተለያዩ ወገኖች የየራሳቸው ፍላጎት መሰነቃቸውን ነው።
መንግሥት ለሕዝቡ ተቁዋማት ጥበቃ ማድረግ አለበት።ግዴታውም ነው።ሕዝቡ በሀይማኖት እና በጎሳ የሚያጋጭ አጀንዳ ከማራመድ አልፈው ወደ ግጭት ለመምራት የሚጣደፉ ወገኖች አደብ ሊገዙ ይገባል።በተደጋጋሚ መንግሥት አቅመ ቢስ ሆኖ ከጀርባ መንግሥትን ይዘውራሉ የሚባሉ ነውጠኞች የፈለጉት ሲፈጸም እያየን ነው።ሕጋዊም ባይሆን ያሉት ይፈጸማል።ይህም ተጨማሪ ጥርጣሬ ይፈጥራል።
የኦሮሞ ሕዝብ ሰላማዊ ተጋድሎ አገር ማፍረስ አይደለም ጥያቄው።አገር መገንባት ስለነበር ደግፈናል።የማስተር ፕላኑ መስፋፋት እና ራሱን በራሱ ማስተዳደር ።የዲሞክራሲያዊ መብትን ተግባራዊ ማድረግ ነበር።ዛሬ እየተንጸባረቀ ያለው አጀንዳ በስሙ የሚምሉ ወገኖች የተለየ እና ሕዝባዊ መሰረት የሌለው አገር የማፍረስ አጀንዳ ነው።ይህን የትኛውም ሕዝብ ፍላጎት አይደለም።አገር አፍርሰው አገር ለመገንባት በሚል አደገኛ አካሄድ ጀምረዋል።ለዚህ አገርን የሚያስተሳስሩ ተቁዋማት ላይ መዝመት ግንባር ቀደም ሚና ነው።የሆነውም ይኸው ነው።
ሕወሓት የሙስሊሙ ማህበረሰብን በጉልበት ለማስገበር በመጅሊሱ ውስጥ የደህንነት አባላቱን ሰግስጎ ፣አህባሽ የተባለ መጤ ሀይማኖት ለመጫን ሲሞክር በሰላማዊ ትግላቸው እየሞቱም እየታሰሩ፣እየተደበደቡ የሚያደርጉት ትግል በክርስቲያን ወገናቸው እና በክርስትና የሀይማኖት መሪዎች ጭምር አይዙዋችሁ ከጎናችሁ ነን፣መንግስት እጅህ ከሙስሊሙ ማህበረሰብ ላይ አንሳ መባሉ የኢትዮጵያን አንድነት የታየበት ገዢዎችንም ያስደነገጠ ተግባር ነው።
ዛሬም ከህግ እና ስርዓት ውጭ የኦርቶዶክስ ሀይማኖት እና ተቋሙ እንደ ተቋም ለማጥፋት የሚደረገውን ሩጫ ኢትዮጵያውያን የኔ እምነት አልተነካም በሚል ብቻ ሊያዩት አይገባም።የአገርን ተቁዋማት እየናዱ ካሰቡት ግብ ለመድረስ የሚደረግ ሩጫ አካል ነው። ይህ ዛሬ እዚህ ከተጀመረ ነገም ይቀጥላል።
በተለያዩ ጊዜያት ኢትዮጵያን ለማፍረስ እንቅፋት ሆነዋል ተብለው ዒላማ ከተደረጉ  መካከል የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አንዱዋ ነች።አድዋ አብራ ዘምታለች።ይህ ለጠላቶችዋ ለሽንፈታቸው አንድ ምክንያት አድርገው ቆጥረዋል። በርካታ ጸሐፊያ ሆነ በፋሺስት መኮንኖች እና ባለስልጣናት ጭምር ሕዝቡን በሀይማኖት እና ብብሄር ልዩነት ለመክፋል መሞከሩ ተመስክሯል።
በጊዜው አልተሳካላቸውም።ነገር ግን በብሄር ማንነት መከበር ስም እርስ በእርስ ሕዝቡ እንዲፋጠጥ የተሄደበት መንገድ የሚያሳየው ሀቅ ትላንት እነ ጣሊያን ሞክረው ያልተሳካላቸው የቤት ስራን ባለፉት ሃያ ስምንት ዓመታት በየደረጃው እየተተገበረ ነው።የዚህ መጨረሻ አገሪቱን መበተን መሆኑ ቢያንስ ዛሬ ለብዙሃኑ ግልጽ ሆኗል።
አሁን ለወቀሳም፣ለቁጣም ሆነ ለቁጭት ጊዜ የለም።አማራጩ በፍጥነት አገርን ለማዳን ሁሉም የበኩሉን ማድረግ፣በዝምታ ተባባሪ እየሆነ ያለውን የማዕከላዊ መንግሥት ስልጣን የጨበጠው አካል ሀላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ መጠየቅ ነው። ይህ ካልሆነ አቁዋምን አስተካክሎ አገር እና ሕዝብን ለመታደግ ከወሬ ያለፈ የተጠናከረ የተግባር እርምጃ ይፈልጋል።ይህ ካልሆነ በስተቀር አገር አፍርሰው አገር ለመገንባት ከቆረጡ ሀይሎች ጋር መግባባት አይቻልም።
አገሪቱዋን እንመራለን የሚሉ ወገኖች በዝምታ የጥፋት ድርጊት ተባባሪ መሆናቸውን አውቀው ወይ ሀላፊነትን መወጣት አለበለዚያም ለሕዝቡ ቁርጡን መንገር እና የራሱን አማራጭ እንዲወስድ አገሩና ወገኑን ከከፋ ጥፋት እንዲታደግ ይሁን።የተያዘው መንገድ አገርን ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ ማሻገር ሳይሆን ወደ ትርምስ አጣብቂኝ ውስጥ መክተት ነው። መንግሥት ሀላፊነቱን ይወጣ ያለበለዚያ በአስቸኳይ አገሪቱን የሚታደግ ግልጽ የሆነ አገርን መምራት እና ወደ ቀጣዩ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመሔድ የሚያስችል ሰላም እና መረጋጋት የሚያመጣ ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግሥት ይቁዋቁዋም።
Filed in: Amharic