>

ሃገሬን እፈራታለሁ፤ የሚታየው የሚሰማው ሁሉ በፍርሀት ልብ ያርዳል!!! (መስከረም አበራ)

ሃገሬን እፈራታለሁ፤ የሚታየው የሚሰማው ሁሉ በፍርሀት ልብ ያርዳል!!!
መስከረም አበራ
አዎ ሃገሬን እፈራታለሁ ፤ የዘር ፖቲከኞቿ የፅንፈኝነት ውድድር፣ የዜጎቿ መደናገር፣የመሪዎቿ ሙልጭልጭነት፣የኢህአዴግ የሽንገላ ፖለቲካዊ ባህል ሁሉ ተደማምሮ ሃገሬ አንድ ቀን ወደ እልቂት ማዕከልነት ትቀየር ይሆን ብየ እንድፈራት ያደርገኛል፡፡ፍርሃቴ የሚበረታው ደግሞ ብዙ ባይባልም በመጠኑ ስለ ሩዋንዳ ጥቂት ስለ ናይጀሪያ የዘር ዕልቂቶች፣በመጠኑ ስለ ህንድ የሃይማኖት ግጭት ወለድ መተራረድ ለማንበብ በመሞከሬ ነው፡፡ እናም የሃገሬ ሁሉመና ያስፈራኛል!ነፍስም እስከማይቀርልን የወደድነው የዘር ፖለቲካ ለወሬ ነጋሪ ሳይቀር ድምጥማጣችንን እንዳያጠፋ አብዝቼ እሰጋለሁ፡፡ አያያዛችን እንደ ባለ አእምሮ አይደለም…….
ከዘረኝነት በሽታ በመዋጀት ማንንም ለማመም እየተቸገርኩ ከመጣሁ ሰነበትኩ፡፡በዘር መንዘርዘርን በተመለከተ ፖለቲከኛን ቀርቶ ቄስ መነኩሴ፤ፓስተር ሼክም ቢሆን የመተላለቅ ፊሽካ ባለመንፋት አልተማመንበትም፡፡የስጋቴ መጠን ሲኖዶሱ ሰሞኑን በተጋረጠበት አደጋ ዙሪያ አንድ ሆኖ ይቆም ይሆን የሚል ስጋት ሳይቀር ሽው እንዲለኝ አድርጎኝ ሰንብቷል፡፡የሲኖዶስ አባል አባቶች በቤተክርስቲያናቸው ጥላስር ተሰባስበው በአንድነት ሲሞግቱ ሳይ ተስፋየ ልምልሟል፡፡
የዘር/ሃይማኖት መተራረድ በተከሰተባቸው ከላይ በጠቀስኳቸው ሃገራት መንፈሳዊ አባቶች መተላቁን መርቀው ሲከፍቱ የታየባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡በዚህ ምክንያት ፈተና የተጋረጠባት የሃገሬ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ አንድ ሆኖ መቆሙን እስክሰማ ድረስ ውስጤ ስጋት ገብቶት ነበር፡፡የዘር ፖለቲካን የመሰለ የሰውን ልብ የሚያውር ነገር የለምና ነው የእነዚህን አባቶች አንድ ሆኖ መቆም እስከ መጠርጠር ያደረሰኝ፡፡
እናም ቤተክርስቲያኗ የተደቀነባት ፈተና ቀላል የማይባል ቢሆንም የሲኖዶሱ አንድነት፣ሃይማኖት ያልለየው የኢትዮጵያ ህዝብ ከሞላ ጎደል ከቤተክርስቲያኗ ጎን መቆም ቀላል አድርገን መቁጠር የሌለብን በጎ ነገር ነው፡:ይህን ተስፋ አለምላሚ ነገር ተንተርሶ በአንድነት መበርታቱ የፈተናውን ጉልበት ያዳክማል፡: አንድ ላይ መቆም የድል ለመጀመሪያ ነው!
Filed in: Amharic