>

ስለ "ቀሲስ" በላይ መኮንን እኛም እንናገር ....  በላይ ማነው? ከምንስ ተነስቶ የት ደረሰ?  (ባያብል ሙላቴ)

ስለ “ቀሲስ” በላይ መኮንን እኛም እንናገር ….
 በላይ ማነው? ከምንስ ተነስቶ የት ደረሰ?
 ባያብል ሙላቴ
(ክፍል ፩)
 

ምርጫ 1997ን ተከትሎ መንግሥት የወሰደውን የግድያ፣ እስራት፣ አካል ማጉደል ወዘተ እርምጃዎች እንዲያጣሩ ከተሾሙት ሰዎች መካከል አንዱ “መምሬ” በላይ መኮንን ነው። በተለይ በኦሮሚያ፣ አዲስ አበባ እና አማራ ክልል ላይ የተፈጸመው ድርጊት ማንም የሚያውቀው ቢሆንም “መምሬ” በላይ ግን የመንግሥት እርምጃ ትክክል/ተነጣጣኝ ነው ካሉት ውስጥ ዋናው ነው። ምርጫ 97ን ተከትሎ ኦሮሚያ ላይ የስንት ወጣት ነፍስ እንደጠፋ ግን አይደለም ቤተሰብ ይቅርና መንግሥትም (ቢያንስ እነ ዶ/ር አቢይ ከመጡ በኋላ) ያመነው ነው። ለኅሊናቸው የቆሙት የአጣሪ ጉባኤው ሰብሳቢ፣ ዳኛ አቶ ፍሬሂወት ሳሙኤልም “መምሬ” በላይ መኮንንም እኩል የኦሮሞ ልጆችን ሞት አጣሪ ነበሩ!!!

 
—-
ከቀሲስ በላይ መኮንን ጋር ከተዋወቅን ከ25 ዓመት በላይ ይሆናል።  ከአንድ ሳምንት በፊት ተገናኝተን ነበር። ስለ እወጃው ግን አንዳች አላነሳልኝም።
በነበረን መቀራረብ ገና ሃሳቡ ሳይገዝፍ በግልም በቡድንም  ውይይቶች ስናደርግ ቆይተናል። ሆኖም እሱ ወደማወጅ ከደረሰ፤ እኔም ከአሃቲ ቤተክርስቲያን የሚበልጥብኝ ነገር የለም።
አሁን የደረሰበትን ሲጀምረው እንዴት? መች? በምን ምክንያት እንደሆነ ከሞላ ጎደል የማስታውሰውን አካፍላችኋለሁ።
ቀሲስ በላይ ከ1997 ዓም ምርጫ ጋር ተያይዞ በኦሮሚያ ክልል ለተከሰተው የሰብአዊ መብት ጥሰትናን ለማጣራት በመንግስት ከተሰየመው አጣሪ ኮሚሽን ተሰይሞ ሲሰራ ቆይቶ ሲጨርስ በ2002 ዓም  በአዲስ አበባ ከተማ  ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ተመርጦ ነበር።
በአጣሪነት ሆነ በፓርላማ በነበረበት ጊዜ  በቤተ ክህነት የነበረውን ሃላፊነት ደርቦ እንደያዘ ስለነበር ከቄሳርም ከእግዚአብሄርም ከሁለቱም ደሞዝና ጥቅማ ጥቅሙን እያገኘ ነበር።
የቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በላይ የነበረበት መምሪያ ሥራ እየተበደለ ግን ደሞዝ እየወሰደ ስለሆነ አንድ መፍትሄ አምጣ ብለው አቅርበው ሲጠይቁት የፓርላማ ጊዜየን እስክጨርስ ይታገሱኝ በማለቱ በጊዜው የነበሩት ብጹእ አባት የዋህ ነበሩና በቸልታ አለፉት።
ምክትላቸው ግን ለተወካዮች ም/ቤት ስራም እየተበደለ ደምወዝም እየከፈለን እንዴት ይሆናል የሚል ደብዳቤ ጻፉ።
 ከፓርላማው ጽ/ቤት ለቤተክህነቱ ስልክ ተደውሎ አትንኩት ተባለ፤ ቤተክህነቱም ደሞዙን ሳይነካ ከሃላፊነቱ አንስቶ ወደ ሰዋሰው ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ከፍተኛ መንፈሳዊ ት/ቤት/ኮልፌ/ አዛወረው።
በላይም በወቅቱ ለነበረው  አፈ ጉባኤ  “ቄሶቹ የእናንተን መመሪያ ንቀው “ኦሮሞ በመሆኔ” ከቦታዬ አነሱኝ” ይለዋል።
አፈ ጉባኤውም ሃውልቱ አክሱም ላይ አቀባበል ሲደረግለት ከቀድሞውን ፓትሪያሪክ ጋር ሲገናኙ፤  አጋጣሚውን ተጠቅሞ “ምነው አባታችን ምንም እንኳ በእናንተ የሚመጥን እውቀት ባይኖረውም ለእኛ ግን ታዛዣችን ስለሆነ በላይ ወደ ነበረበት ቢመለስ?” የሚል ምልጃም መመሪያም የሚመስል ነገር ያስተላልፋል።
 ወደ ነበረነት መምሪያ ተመልሶ   ሳለ የአሁኑ  ፓትሪያሪክ  ከተሾሙ በኋላ አዲስ አበባ ሃ/ስብከት  ረዳት ሊቀጳጳስ ተመደበና ለሃ/ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ የሚሆን ሲፈለግ ፓትሪያሪኩም ረዳት ሊቀ ጳጳሱም ሳያምኑበት በሌላ አካል አቅራቢነት ቄስ በላይ እንዲሾም ታጨ።
ሹመቱ ውሳኔ በተሰጠበት ሰዓት ከፓትሪያሪኩ ጋር ረዳት ሊቀጳጳሱ የወቅቱ የቤተ ክህነቱ ዋና ስራ አስኪያጅና አራተኛ ሰው/ፀሀፊው ብቻ ነበሩ.።
በዚህ ስዓት ረዳት ሊቀ ጳጳሱ  ከአሁን ፊት አብሮኝ ስለሰራ አውቀዋለሁ፤  ባይሆን ጥሩ ነው፤ ሥራችን ይበላሽብናል ብለው ሞግተው ነበር፤ ፓትሪያሪኩም ከረዳት ሊቀ ጳጳሱ ጋር ተመሳሳይ አቋም በመያዝ ሌላ አማራጭ/የኦሮምኛ ተናጋሪ/  አቅርበው የነበረ ቢሆንም ሹመቱን ያስቆመው አልነበረምና ዋና ስራ አስኪያጁ የሹመት ደብዳቤ እንዲጽፉለት ታዘዙ። ታህሳስ (2006)
በላይ ከተሾመ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ከረዳት ሊቀጳጳሱ ጋር ውዝግብ ውስጥ ገባ። በወቅቱ ብጹእ ሊቀ ጳጳሱ የአአ ሃ/ስብከትን ኌላቀር አሰራር ዘመኑን በሚዋጅ ዘመናዊ አሰራር ለመለወጥ በታዋቂ ሙሁራን አስጠንተው ወደ ትግበራ ከመገባቱ በፊት ለአአ አድባራት ካህናት የተዘጋጀውን ስልጠና  እየመሩ ነበር።
በዚህ የለውጥ ውጥረት ስዓት በነበረው የሃይል አሰላለፍ የአዲስ አበባ አድባራት አስተዳዳሪዎች ከስምንቱ በስተቀር ለውጡን ደግፈው ሲንቀሳቀሱ ስምንቱ ግን ለውጡ ጥቅማችንን ያስቀርብናል በሚል ለመቀልበስ ግርግር የፈጠሩበት ጊዜ ነበር።
በላይ በዚህ ጊዜ ከረዳት ሊቀ ጳጳሱ በተቃራኒ ከቀልባሾቹ ጋር በመቆም  ማታ ማታ ስሜን ሆቴል እየተገናኙ ለውጡን በሚያከሽፉበት ሁኔታ ይመክር ነበር።
ለለውጡ መቀልበስ የአንበሳውን ድርሻ የተጫወቱት ግን በወቅቱ የነበረው የመንግስት ደህንነት ሃይልና የፌደራል ጉዳዮች ሚ/ር(Dr)  ነበሩ።እነዚህ አካላት ተቃዋሚዎቹን የሰው ሃይል መድበው ከማስተባበር ጀምሮ በቀጥታ ለፓትሪያሪኩ  ስልክ ደውለው ስልጠናውን እንዲቆም ያዘዙበት ቀንም እንደነበር አስታውሳለሁ። በላይ የዚህ ሃይልና የአማሳኞቹ ጉዳይ ፈጻሚ ነበር።
በላይ በዚህ አላቆመም ረዳት ሊቀ ጳጳሱን ከኃላፊነታቸው ለማስነሳት ከአማሳኞቹና ከደህንነቱ ጋር ሆኖ ፓትሪያሪኩን በእጃቸው አስገብተው ያለእረፍት ታገሉአቸው።
ረዳት ሊቀ ጳጳሱም (በግንቦት,2006) በሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቂያ አስገብተው አስረከቡ። ምልአተ ጉባኤው ግን እንዳይለቁ ለምኖ ነበር።
ከተወሰኑ ወራት በኋላ ግን በሰፈሩት ቁና መስፈር አይቀርምና በላይ ከአማሳኞቹ ጋር በጥቅም ተጣሉና አማሳኞቹ ለፓትሪያሪኩ በላይን አንፈልገውም ይነሳ ብለው ከሥራ አስኪያጅነቱ አስነሱት።
የሚገርመው ግን በላይ ከስንብተ በኋላ ልክ በቤተ ክህነቱ ግቢ ያለው ብቸኛ ኦሮሞ እሱ ብቻ ይመስል እንደለመደው ኦሮሞ በመሆኔ ተባረርኩ እያለ ማስወራት ጀመረ፤ ምንም እንኳ ቤተ ክህነቱ ከችግር ንጹህ ነው ብዬ ለአፍታ ባላስብም፤ በላይ ግን  በኦሮሞነቱ እንዳልተሰናበተ  የሚቀጥሉት ማስረጃዎች ያሳጡታል።
1. መቀየር በበላይ አልተጀመረም ከሱ በኋላ ለአዲስ አበባ ሃ/ስብከት ሥራ አስኪያጅነት አራት ሰዎች በተለያዬ ጊዜ ተቀያይረዋል፤ ብሄራቸውም ሁለቱ ከትግራይ ሁለቱ ደግሞ ከኦሮሞ ነበሩ።
2. በአሁኑ ሰዓት እንኳ በዋናው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በዋና ሥራ አስኪያጅነት  ቤተ  ክህነቱን እየመሩ ያሉት ብጹእ ሊቀ ጳጳስ ኦሮሞ ናቸው።
3. እሱ በነበረበት በአዲስ አበባ ሃገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሆነው እየመሩ ያሉት ቅን መነኩሴ/ቆሞስ/ ኦርሞ ናቸው።
4. እስከ አለፈው ግንቦት ድረስ ላለፉት ሶስት ዓመታት የቅዱስ ሲኖዶሱን በዋና ፀሃፊነት የመሩት ሊቀ ጳጳስ ኦሮሞ ናቸው።
5.በ6ኛው የፓትሪያሪክ ምርጫ ሂደትም ኦሮሞው የባሌው ሊቀ ጳጳስ ከእጩዎች አንዱ የነበሩ ሲሆን በሁለተኛነት ድምጽ አግኝተው እንደነበር አስታውሳለሁ።
*** እንዲህ ብሄር እየጠራሁ የተከበሩ ብጹአን አባቶችን እገለ እንዲህ ነው እያኩ ስጽፍ ግን እጅግ ህሊናዬን እየጸነነኝ እንደሆነ ልትረዱልኝ ይገባል። ሆኖም አንዲትም ነቭስ በዚህ ምክንያት ልትጠፋ ስለማይገባ በማስረጃ እገልጽ ዘንድ ግድ ሆኖብኛል።**
***የሚገርመው በላይ በተደጋጋሚ ጳጳሳት ሚስት ሊያገቡ ይገባል ይላል።
***እንዲሁም የጳጳሳት ስም አቡነ ጳውሎስ አቡነ ማቲያስ ወዘተ መባሉ ቀርቶ አቡነ ገመዳ፣ አቡነ ጨመዳ፣ መባል አለበት በማለት በኦሮምኛ ቋንቋ አሳትሞ እስከ ማሰራጨት ስሜታዊ ድፍረት የፈጸመ ነው።
♠♠ወገኖቼ ከላይ በአጭሩ የዳሰስኳቸውን የበላይ ፖለቲካን ከእምነት የደባለቀ ጉዞ የፈጠረውን ችግሮችና በዚህም ቤተክርስቲያን የአመለጣትን መልካም እድል ጠቅለል አድርጌ በአጭሩ ይህን ይመስላል።
1ኛ. በላይ  ከ1998 እስከ 2007 ዓም በመንግስት ከኦሮሚያ የሰባዊ መብት ጥሰት አጣሪ ኮምሽን(3 ዓመት) – ፓርላማ አባልነት(4 ዓመት) እየሰራ ቤተ ክርስቲያን ልጄ ብላ አክብራ የሰጠችውን ቁልፍ የሃላፊነት ቦታ ግን ሥራ በመበደል፣ ይባስ ብሎ ያልሰራበትን ደምወዝ እየወሰደ፣ አባቶች ማስተካከያ ሊያደርጉ ሲሞክሩ ደግሞ በባለስልጣናት እያሸማቀቀ መኖሩ።
2ኛ. በቤተ ክህነቱ የሰፈነውን ኋላቀር የአሰራርና የአስተዳደር ብልሹነት በመለወጥ ለቤተ ክርስቲያን ዘመኑን የሚዋጅ ለውጥ በማምጣት ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት በአዲስ አበባ ሃ/ስብከት ረዳት ሊቀ ጳጳስ ተነሳሽነትና አስተባባሪነት በታዋቂ ሙሁራን ጥናቱ ተጠናቆ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ፀድቆ ወደ ትግበራ ሊገባ ሲል የፈነጠቀውን የቤተክርስቲያን ብሩህ ተስፋ ለውጡ ጥቅማችንን ያሳጣናል ባሉ ጥቂት አማሳኞችና አላዊያን ፖለቲከኞች ጋር ሸርኮ የውስጥ አርበኛ በመሆን ለውጡን በማጨናገፍ የእናት ቤተክርስቲያንን ተስፋዋን በማጨለሙ ታሪክ የማይረሳው ጉዳት አድርሶባታል።
@እንዲህ አድርጎ የቤተክህነትን ተስፋ ያጨለመ ሰው ዛሬ በመልካም አስተዳደር እጦት የኦሮሚያ ምእመናን ወደ ሌላ እምነት እየፈለሱ ነው እያለ አይኑ በጨው አጥቦ ጣቱን ወደ አሃቲ እናት ቤተክርስቲያን ሲጠቁምና ተቆርቋሪ የለውጥ ሃዋሪያ መስሎ ሲናገር ስሰማ እጅግ አዝናለሁ። @
በመሆኑም ምእመናን ሳያውቁ ከሚያልቁ አውቀው እንዲጠነቀቁ ይህን ለማካፈል ውስጤ ይሉኝታውን አሸንፎ የማውቀውን እንዳካፍላችሁ አስገድዶኛል። ይህ መረጃ ግን ለማወቅና ለጥንቃቄ ይጠቅም ይሆናል እንጅ በራሱ የችግሮች መፍትሄ ሊሆን አይችልም።
♥በመሆኑም  እናት ቤተ ክርስቲያናችን ከመቼውም ግዜ ይልቅ በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደምትገኝ ግንዛቤ ወስደን  ከዚህ ችግር ፈጥና የምትላቀቅበት ዘላቂ መፍትሄ አባቶች ከልጆች አንድ ሁነን ብንፈልግ ይሻላል።
Filed in: Amharic