>
5:13 pm - Tuesday April 19, 7138

ሲኖዶሱ በጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔ የሚያሳልፍባቸው ወሳኝ አጀንዳዎች ተለይተዋል!!! (ታደሰ ወርቁ) 

ሲኖዶሱ በጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔ የሚያሳልፍባቸው ወሳኝ አጀንዳዎች ተለይተዋል!!!
ታደሰ ወርቁ 
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲኖዶስንና ጽንፈኛና አመፀኛ ቄሶችን በሽምግልና ሽፋን ለማደራደር መዘጋጀታቸው በቃል አቀባይቷ በኩል ተሰምቷል !!!
ራሱን ‹‹በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የኦሮሚያ ቤተ ክህነት አደራጅ ኮሚቴ›› ብሎ የሚጠራው ሕገ ወጥ ስብስብ÷ የቋሚ ሲኖዶስን እግድ በመተላለፍና የቤተ ክርስቲያንን ሕጋዊ ሰውነት በመጋፋት፤ በኦሮሞያ ክልላዊ መንግሥት የዕንባ ጠባቂ ቢሮ የሰጠውን የዛቻ መግለጫ ተከትሎ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ውሳኔ ሰጪና የመንበረ ሐዋርያት ወራሽ የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ፤ አስቸኳይ ስብሰባ እንዲካኼድ ለነሐሴ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ተጠርቷል::
የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት እንዳሳወቀው፤ በአስቸኳይ የተጠራው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በሁለት ዐበይት አጀንዳዎች ላይ በቁርጠኝነት ተነጋግሮና መክሮ ውሳኔ በማሳለፍ ዐቋሙን ያሳውቃል፡፡
1ኛ- በጽ/ቤቱ መረጃ መሠረት የመጀመሪያው አጀንዳ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እና በመንግሥት ቀጣይ ግንኙነት ላይ ቁርጠኛ አቋም መውሰድ ሲሆን፤ ቤተ ክርስቲያን የሚደርስባትን ጥቃት እና በደል መንግሥት በተጨባጭ መረጃና ማስረጃ እያወቀ ተገቢውን ሕጋዊ እርምጃ አለመውሰዱን በማስታወስ፤ ቤተ ክርስቲያኒቷ ከመንግሥት ጋር ሊኖራት የሚገባውን ግንኙነት ለመመርመር እንደተገደደችና ይህንም ውሳኔዋንና አቋሟን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድም በይፋ እንደምታሳውቅም የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት አሳውቋል፡፡
2ኛ- ሁለተኛው፤ ራሱን ‹‹በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የኦሮሚያ ቤተ ክህነት አደራጅ ኮሚቴ›› ብሎ የሚጠራው ሕገ ወጥ ስብስብ፤
• የቤተ ክርስቲያኒቷን ቀኖናዊና ሕጋዊ አሠራር ጥሶ የፈጸመውን ወንጀል፣
• ሉአላዊት የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን የጥቂት ብሔረሰቦች ብቻ አድርጎ መክሰሱ፣
• የሀገሪቷን ሕግና የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን አሠራር በመጣስ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስም ማኅተም ማስቀረጹ፣
• ማዕከላዊ አሐቲነቷን ለመናድ ከተለያዩ አካላት በስሟ ገንዘብ መሰብሰቡ፣
• በማን አለብኝነት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የዛቻ መግለጫ ማውጣቱን፣
• በክብረ ታቦት ላይ መሳለቁን፣
• የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሀገራዊ ሚና አኮስሶ የመሬት ወራሪ አድርጎ በማቅረብና ሕዝበ ክርስቲያኑ በሐሰት መረጃ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ እንዲነሣሣ ለማድረግ መሞከሩ፣
• የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ራሷ ሀገር መሆኗን በመካድና በኦሮሚያ መጻተኛ ተደርጋ እንድትታይ በመቀስቀሱ፣
• በጽንፈ ብሔርተኝነት በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ አህጉረ ስብከትን የማፍረስ እንቅስቃሴ በማድረጉ፣ እና
• የየሀገረ ስብከቶቹ ሊቃነ ጳጳሳትና ሠራተኞች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የጣለችባቸውን ሐላፊነት እንዳይወጡ እክል በመፍጠር የፈጸመውን ሕገ ወጥ ተግባር
በመመርመር የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባዔ ሕጋዊ እና ቀኖናዊ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ የምልዓተ ጉባኤ ስብሰባውን በሰላምና በአንድነት መክሮና ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅሙ ውሳኔዎችን እንዲያሳልፍ ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ፤ ከብፁዓን አበው ጎን መሰለፍ በእጅጉ ይጠበቅብናል፡፡ ዘመኑ ብቻ ሳይሆን ሰዎቹም ክፉዎች ናቸውና፡፡
የቤተ ክርስቲያን ራስ የሆነው መድኃኒ ዓለም መልካም የምልዓተ ጉባዔ ስብሰባ ያድርግልን፡፡
 
ከሌላ ምንጭ ባገኘነው መረጃ፦
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲኖዶስንና ጽንፈኛና አመፀኛ ቄሶችን በሽምግልና ሽፋን ለማደራደር እያሟሟቁ ነው !!!
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደራድሯቸው ዘንድ ይሸመግሏቹም ዘንድ ወደ ቤተክሕነት ጋብዟቸው የሚል ግፊት ከወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ተሰምቷል። ሲኖዶሱ ከጽንፈኛ ቀሳውስት ጋር ከተደራደረ ከተሸማገለ አቋም የለሽ ልፍስፍ መሆኑን ያሳያል የሚሉ በርክተዋል።
ከቤተክርስቲያን አፈንግጠው የወጡ ፖለቲከኞችና የፖለቲካ አላማ ያነገቡ ተራ ቀሳውስት( ቀውሶች) በየትኛው የሞራል ልእልናቸው ነው ከተዋሕዶ እምነት የበላይ ከሆነው ሲኖዶስ ጋር የሚሸማገሉት የሚደራደሩት ??? በውጪው አገር የነበረው ሲኖዶስ የተገፉ ፓትሪያርክና የጳጳሳት ስብስብ እንጂ ፖለቲከኛ ተራ ቄሶች የፈጠሩት የፖለቲካ መደስኮሪያ እንዳልነረ ማስታወስ ያስፈልጋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ የተባለች ሴትዬ ቤተክርሲያኒቱን ወደፊት ሊያፈራርስ የሚችል አደገኛ አካሄድ ከሲኖዶስ ጋር ለማሸማገል ለማደራደር ተቅላይ ሚኒስትሩ እያሟቁ እንደሆነ ነግራናለች። የሽምግልናውን ጉዳይ ስታንቆለጳጵሰው ሁለት ተከፍሎ የነበረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ወደአንድ እንዲመጣ ከፍተኛ ሚና የተጫወቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሁንም ለመሰል የሰላም ሚና ዝግጁ መሆናቸውን ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅዱስ ሲኖዶስና በኦሮሚያ ቤተ ክህነት አደራጅ ኮሚቴ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት እንዲሸመግሉ ይጋበዙ የሚል ጫና ተንፍሳለች።
ከመጀመሪያው አመጣጡ አካሔዱም ከጀርባው የመንግስት ሚና ከፍተና መሆኑ የተሰሩ ስራዎች ምስክር ናቸው። ሲኖዶስ ስልጣኑን ትቶ ከተራ ቀሳውስት ፖለቲከኞች ጋር ከተድራደረ ደካማ ልፍስፍስ ሆኗል ማለት ነው። ጠንካራ አቋም ይዞ ሆዳም ቄሶችን ካስወገደ ምእመናን ከጎኑ በመቆም ለሃይማኖታቸው መስእዋት እንደሚሆኑ የተረጋገጠ ነው።
Filed in: Amharic